የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የማረሚያ ቤት አመራሮችን ከሃላፊነት ማንሳቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 27 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የማረሚያ ቤት አመራሮችን ከሃላፊነት ማንሳቱን አስታወቀ።

የማረሚያ ቤት አስተዳደር ህገ መንግስታዊ ግዴታውን በተገቢው ሁኔታ መወጣት ባለመቻሉ እና ሰብዓዊ መብቶችን ከማክበር አንጻር ሰፊ ክፍተት በመኖሩ፥ ለውጥ መደረጉን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ተናግረዋል።

በዚህም ነባሮቹን አመራሮች በማንሳት አዳዲስ አመራሮች መመደባቸውንም ነው ጠቅላይ አቃቤ ህጉ የተናገሩት።

አዳዲሶቹ አመራሮችም የሚነሱ ቅሬታዎችን በመፍታት በህገ መንግስቱ የሰፈሩ ሰብዓዊ መብቶችን እና ህጎችን ባከበረ መልኩ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

አመራሮቹ ከሃላፊነት የተነሱት በህግ ታራሚዎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ህገመንግስቱን ለማስከበር በማሰብ መሆኑም ተገልጿል።

ህግ የጣሱ አካላት ማጣራት እየተደረገባቸው ወደ ፍትህ እንደሚቀርቡም ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገልጿል።

በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ላይ እየደረሱ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ጣቢያችን ዜናዎች መስራቱ ይታወሳል።

በወቅቱም ታራሚዎቹ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸውና መንግስት ጉዳዩን እንዲመለከተው መጠየቃቸውም የሚታወስ ነው።


ምንጭ፦ FBC