ከደ/አፍሪካ- ኢትዮጵያ፡ አፓርታይድ ሰው “ጨፍጭፎ” ይመጣል፣ ሕዝብ “አጨፋጭፎ” ይሄዳል!

ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ የዘረጋው የአፓርታይድ ስርዓት እና በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ከአመሰራረታቸው ጀምሮ ፍፁም ተመሳሳይ ናቸው። በሁለቱም ሀገራት የአፓርታይድ ስርኣት የመሰረቱት የፖለቲካ ቡድኖች “የሰቆቃ ልጆች” ናቸው። እነዚህ የሰቆቃ ልጆች ከዚህ ቀደም በህዝባቸው ላይ የተፈፀመን አሰቃቂ ጭፍጨፋ መነሻ በማድረግ ሌሎችን በብሔር፥ ቋንቋ፥ ጎሳ፥ … በመከፋፈል የራሳቸውን የስልጣን የበላይነት እና የኢኮኖሚ ብዝበዛ ለማስቀጠል ጥረት የሚያደርጉ ናቸው። የአፓርታይድ ስርዓት በደቡብ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ ከአመሰራረት እስከ አወዳደቅ ያላቸውን ተመሳሳይነት አንዳንድ ማሳያዎችን በመጥቀስ እንመለከታለን።

ክፍል-1፦ ሰዎች ጨፍጭፎና አስጨፍጭፎ የመጣ መንግስት!

በሁለቱም ሀገራት አፓርታይድን የመሰረቱት የፖለቲካ ቡድኖች በመጀመሪያ ሽምቅ ተዋጊ አማፂያን ነበሩ። የደቡብ አፍሪካ ነጮች 500ሺህ ጦር አስከትሎ ከመጣው የእንግሊዝ ጦር ጋር የሽምቅ ውጊያ ሲያካሂዱ የትግራይ አማፂያን ደግሞ ተመሳሳይ ቁጥር ካለው የደርግ ሰራዊት ጋር ተዋግተዋል። የእንግሊዝ እና የደርግ መንግስት ስለ አማፂያኑ የነበራቸው አቋምና አመለካከት ተመሳሳይ ነበር። እንግሊዞች የደቡብ አፍሪካ ነጭ አማፂያንን “ኋላቀር ሽፍቶች” ሲሏቸው ደርግ ደግሞ “ገንጣይ ወንበዴዎች” ይላቸው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱም መንግስታት እያንዳንዳቸው ግማሽ ሚሊዮን ወታደር በማሰማራት ነገሩን ሁሉ በጦርነት ለመፍታት እቅድ ነበራቸው።

በዚህ መሰረት የእንግሊዝ ጦር በአማፂያኑ ላይ በከፈተው ሁለት ተከታታይ ዘመቻ አሳፋሪ ሽንፈት ደረሰበት። በተመሳሳይ የደርግ መንግስት በኤርትራና በትግራይ ባካሄዳቸው ሁለተኛ እና ሦስተኛ አብዮታዊ ዘመቻዎች ያልተጠበቀ ሽንፈት ደረሰበት። የእንግሊዝ ጦር እ.አ.አ. ከ1899 – 1901 ዓ.ም ባሉት አመታት 27 ሺህ ከሚሆኑ የደቡብ አፍሪካ ሽምቅ ተቃጊዎች ባደረገው ጦርነት 22ሺህ የሚሆኑ ወታደሮቹ ተገድለውበታል። ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው የትግራይና ኤርትራ አማፂያን እ.ኢ.አ ከ1979 – 1981 ዓ.ም በተካሄደው ጦርነት 22ሺህ የሚሆኑ የደርግ ወታደሮች ተገድለዋል። የእንግሊዝና ደርግ መንግስት የደረሰባቸውን ያልተጠበቀ ሽንፈት ተከትሎ አማፂያኑ በሚንቀሳቀሱበት አከባቢ ላይ አሰቃቂ የሆነ እርምጃ ወስደዋል።

22ሺህ ወታደሮች የተገደሉበት የእንግሊዝ ጦር ሽምቅ ተዋጊዎቹን ለመደምሰስ በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች ላይ “መሬቱን በእሳት መለብለብ” (Scorched-earth) የሚል ፖሊሲ አማፂያኑ በሚንቀሳቀሱባቸው አከባቢዎች ያሉትን መኖሪያ ቤቶች በእሳት አወደመ። ይህን ተከትሎ ሕፃናት፣ እናቶችና አዛውንቶችን በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ አስገብቶ አጎራቸው። በእነዚህ የማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ብዙ ሺህ ህፃናትና እናቶች በርሃብና በሽታ አለቁ። በተመሳሳይ፣ 22ሺህ ወታደሮች የተገደሉበት ደርግ መንግስት “ዓሳውን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ” በሚል ሃውዜን ላይ በፈፀመው የአየር ድብደባ በአንድ ቀን ብቻ 1800 ንፁሃን ዜጎችን ተገድለዋል።

የእንግሊዝ ጦር የደቡብ አፍሪካ ነጮችን በወታደራዊ ጉልበትና የበላይነት ለመቆጣጠር መሞከሩ ከ22ሺህ በላይ ወታደሮቹን ለሞት ዳርጓል። በተመሳሳይ የደርግ መንግስት የትግራይና ኤርትራ አማፂያንን በወታደራዊ ጉልበትና የበላይነት ብቻ ለመቆጣጠር በመሞከሩ ከ22ሺህ በላይ ወታደሮቹን ለሞት ዳርጓል። የደቡብ አፍሪካ አማፂያን ሕዝቡ ውስጥ ተሸሽገው በእንግሊዝ ጦር ላይ አስከፉ ጥቃት በመፈፀማቸው “መሬቱን በእሳት መለብለብ” በሚለው መርህ የሰላማዊ ዜጎች መኖሪያ ሰፈር በእሳት እንዲቃጠል ምክንያት ሆነዋል። የህወሓት ታጣቂዎች ሕዝቡ ውስጥ ተሸሽገው ድርግ ላይ አስከፊ ጥቃት በመፈፀማቸው “ዓሳውን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ” በሚል መርህ የአከባቢው ሕዝብ በቦንብ እንዲደበደብ ምክንያት ሆነዋል።

የደቡብ አፍሪካ አማፂያን እ.አ.አ. ከ1899 – 1901 ዓ.ም ባሉት አመታት በእንግሊዝ ወታደሮች ላይ የፈፀሙት ጭፍጨፋ በተመሳሳይ ወቅት እንግሊዞች ከገደሉት ብዙ እጥፍ ይበልጣል። በተመሳሳይ የትግራይና ኤርትራ አማፂያን እ.ኢ.አ ከ1979 – 1981 ዓ.ም ባሉት አመታት የጨፈጨፉት የወታደር ብዛት የደርግ መንግስት በአከባቢው ከገደላቸው ሰዎች ብዛት ብዙ እጥፍ ይበልጣል። ስለዚህ የእንግሊዝም ሆነ የደርግ መንግስት አማፂያኑ በሚንቀሳቀሱባቸው አከባቢዎቸች በሚኖረው ሕዝብ ላይ ጭፍጨፋ ከመፈፀማቸው በፊት በወታደሮቻቸው ላይ አስከፊ ጭፍጨፋ ተፈፅሞባቸዋል። ይህን መነሻ በማድረግ የእንግሊዝና ደርግ መንግስት በሰላማዊ ዜጎች ላይ አስከፊ ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። ነገር ግን፣ የእንግሊዝና ደርግ ወታደሮች አስከፊ ጭፍጨፋ ሲፈፅሙ በሰላማዊ ዜጎች ውስጥ ተሸሽገው የነበሩት አማፂያን “አስጨፍጫፊ” እንደነበሩ ሊሰመርበት ይገባል። ምክንያቱም አማፂያኑ በሕዝቡ ውስጥ ተደብቀው በፈፀሙት ጥቃት እያንዳንዳቸው 22ሺህ ወታደር ባይገደልባቸው ኖሮ የእንግሊዝም ሆነ የደርግ መንግስት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጅምላ ጭፍጨፋ የሚፈፅሙበት ምክንያት የለም።

በአጠቃላይ የደቡብ አፍሪካ ነጭ አማፂያን ሆኑ ህወሓቶች የሚወክሉት ሕዝብ መጨፍጨፉን በፀፀትና ቁጭት ያነሳሉ። የሟቾችን ቁጥር ያለቅጥ ያጋንናሉ። ዘወትር የአዞ አንባ ያነባሉ። ይሁን እንጂ፣ በህዝቡ ላይ ጭፍጨፋ ሲፈፀም እነሱ አስጨፍጫፊ እንደነበሩ አያወሱም፣ አይናገሩም። ሌላው ቀርቶ ለሰከንድ እንኳን ማሰብ ሆነ ማስታወስ አይሹም። ከዚያ በተጨማሪ፣ ከተጨፈጨፈው ወታደር ያልተናነሰ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች መግደላቸውን በኩራት ይናገራሉ። እነዚህ ወታደሮች እንደ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ፍጡር መሆናቸውን ማሰብ ሆነ ማስታወስ አይሹም።

ሰዎችን በመጨፍጨፍና በማስጨፍጨፍ ወደ ስልጣን የመጣ የፖለቲካ ቡድን ሀገርና ሕዝብን ለማስተዳደር የሚያስችል የሞራል ልዕልና የለውም። እንዲህ ያለ የፖለቲካ ቡድን ስልጣኑን የያዘው የመጣበትን ማህብረሰብ በማስጨፍጨፍ፣ ሌሎችን በጭካኔ በመጨፍጨፍ ስለሆነ ሀገርና ሕዝብን ለማስተዳደር የሚያስችል የሞራል ልዕልና የለውም። ይህ ቡድን የመጣበትን ማህብረሰብ የስልጣን መወጣጫ ያደርገዋል። ሌላውን ማህብረሰብ ደግሞ በጠላትነት ፈርጆ ከቀድሞ የባሰ በደልና ጭቆና ይፈፅማል። በደቡብ አፍሪካ የነበረውና አሁን በኢትዮጵያ ያለው የአፓርታይድ ስርዓት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።

በመሰረቱ “አፓርታይድ” (Apartheid) የሚለው ቃል “መለየት” (Separatedness) ወይም “መለያየት” (the state of being apart) ማለት ነው። ዜጎች የሚከፋፈሉት በዘር ሆነ በብሔር በመካከላቸው የሚኖረውን ልዩነት አይቀይረውም ወይም መለያየቱን አያስቀረውም። ስለዚህ፣ “አፓርታይድ” ማለት የአንድ ሀገር ዜጎችን በዘር/ብሔር በመለየትና በመለያየት የሚያስተዳድር ፖለቲካዊ ስርዓት ነው።

በእርግጥ የእንግሊዝ ጦር ከነጮች እኩል በደቡብ አፍሪካ በጥቁሮች ላይ አስከፊ ጭፍጨፋ ፈፅሟል። ከነጮች የሚበልጡ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በርሃብና በበሽታ አልቀዋል። ነገር ግን፣ ደቡብ አፍሪካ እስከ 1948 (እ.አ.አ.) ድረስ በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ስርዓት ስር በነበረችበት ወቅት ጥቁሮች እና ነጮች በጋራ ታግለዋል። በተመሳሳይ የደርግ መንግስት በአማራ፥ ኦሮሞ፥ ሲዳማ፥ ጉራጌ፥… ወዘተ ብሔር ተወላጆች ላይ አስከፊ ጭፍጨፋ ፈፅሟል። በተለይ ደርግ በቀይ-ሽብር ዘመቻ የጨፈጨፋቸው የሌላ ብሔር ተወጆች ቁጥር በትግራይ ከገደላቸው ብዙ እጥፍ ይበልጣል። ነገር ግን፣ የደርግ መንግስትን ከስልጣን ለማስወገድ በተደረገው ትግልም የሌሎች ብሔር ተወላጆች ከትግራይ ተወላጆች ጋር አብረው ታግለዋል።

ደቡብ አፍሪካ ከእንግሊዞች ቅኝ አገዛዝ ነፃ ስትወጣ ብሔራዊ ፓርቲ (National Party) ስልጣኑን በመረከብ የአፓርታይድ ስርዓት መሰረተ። ከዚያ በመቀጠል የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮችን በብሔር፥ ጎሳ እና ቋንቋ በአስር (10) ራስ-ገዝ ክልሎች ከፋፈላቸው። እ.አ.አ. በ1950 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ያወጣው የሕዝብ ምዝገባ አዋጅ (Population Registration Act) የሀገሪቱን ዜጎች “ነጭ፥ ጥቁር፥ “ከለርድ” (colored) እና ህንዳዊያን” በማለት ለአራት ይከፍላቸዋል። ይህን የማድረጉ ዓላማ ጥቁሮች የጋራ የፖለቲካ አቋም እንዳይዙና የተደራጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ለማድረግ ነው። በዚህ መልኩ የተመሰረተው የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ እንግሊዞች ከነጮች እኩል ሲበድሏቸው እና ሲገድሏቸው የነበሩትን ጥቁሮች መግደልና መጨቆን ጀመረ።

በተመሳሳይ ህወሓት/ኢህአዴግ ደርግን አስወግዶ ስልጣን እንደተቆጣጠረ ሀገሪቱን በብሔር፥ ጎሳ እና ቋንቋ ለዘጠኝ (9) ራስ-ገዝ ክልሎች እና ሁለት የከተማ መስተዳደሮች ከፋፈለ። የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት በአንቀፅ 39(5) የሀገሪቱን ዜጎች በቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድና ስነ ልቦናን መሰረት በብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ ይከፋፍላቸዋል። ይህን የማድረጉ ዓላማ አብላጫ ድምፅ ያላቸው ሕዝቦች የጋራ የፖለቲካ አቋም እንዳይዙና የተደራጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ለማድረግ ነው። በዚህ መልኩ የተመሰረተው የህወሓት አፓርታይድ የደርግ መንግስት ከትግራይ ተወላጆች እኩል ሲበድሏቸው እና ሲገድሏቸው የነበሩትን የሌላ ብሔር ተወላጆች መግደልና መጨቆን ጀመረ።

ክፍል-2፦ ህዝብ አጨፋጭፎ የሚሄድ መንግስት!

በደቡብ አፍሪካና ኢትዮጵያ የነበረው የአፓርታይድ ሰርዓት የወደቀበት ሂደት ልክ እንደ አመሰራረቱ ሁሉ ተመሳሳይ ነው። በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት የፖለቲካ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችን፣ የሃይማኖትና የሲቭል ማህበራት መሪዎችን ለእስራት፥ ስደት፥ ሞትና እንግልት በዳረገ ቁጥር ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ እየተስፋፋ ሄዷል። በተመሳሳይ የህወሓት አፓርታይድ የዜጎች መብትና ነፃነት፣ እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ጥረት ያደረጉ ወገኖች በሙሉ ለእስር፥ ስደት፥ ሞትና እንግልት ተዳርገዋል። ነገር ግን፣ ለእኩልነትና ፍትህ የሚደረገውን ትግል በኃይል ለማፈንና ለማዳፈን ጥረት ባደረገ ቁጥር ሕዝባዊ ንቅናቄው እየተስፋፋ ሄዷል።

የአፓርታይድ ስርዓት የትግሉን መሪዎች ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት ብዙ ታጋዮችን እየፈጠረ ሄዶ በመጨረሻ ህዝብ ራሱ የትግሉ መሪ ይሆናል። ይህ ደግሞ በሁለቱም ሀገራት በተግባር ተረጋግጧል። ህዝቡ የትግሉ ባለቤት ሆኖ በአመፅና ተቃውሞ ሀገሪቱን መናጥ ሲጀምር የአፓርታይድ ስርዓት መፍረክረክ ይጀምራል። እ.አ.አ. ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ወደጎን በመተው የመብትና ነፃነት ጥያቄያቸውን በጋራ መጠየቅ ሲጀምሩ የአፓርታይድ መንግስት የወሰደው እርምጃ አሁን በሀገራችን ለሚስተዋለው የፖለቲካ ቀውስና አለመረጋጋት መንስዔን፣ እንዲሁም በሁለቱ ስርዓቶች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት በግልፅ ይጠቁማል።

እ.አ.አ. በ1984 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ አመፅና ተቃውሞ ተቀሰቀሰ። ልክ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች እንደታየው እ.አ.አ. በ1984 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ አመፅና ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር። በሁለቱም አጋጣሚዎች የመንግስት እርምጃ አንድና ተመሳሳይ ነበር። የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማዳፈን ያለማቋረጥ ጥረት ተደርጓል። በዚህ ምክንያት፣ የሕዝቡ ተቃውሞ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እያመራ ሄደ። ይህን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መሪ የነበሩት “Pieter Willem Botha” ልክ እንደ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ቃል ገቡ።

ይሁን እንጂ, የሁለቱም ሀገራት መንግስታት ስር ነቀል ተሃድሶ ማምጣት ተሳናቸው። ከዚያ ይልቅ፣ የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማፈን ጥረት ማድረግ ቀጠሉ። ሆኖም ግን፣ የሁለቱም መንግስታት እርምጃ የሕዝቡን ቁጣና ተቃውሞን ይበልጥ እንዲባባስ አደረገው። በዚህ ምክንያት፣ እ.አ.አ. በ1986 በደቡብ አፍሪካ ፣ በ2009 ዓ.ም ደግሞ በኢትዮጲያ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታወጀ። ይህን ተከትሎ የመከላከያና ድህንነት ኃላፊዎች በሕቡዕ ሦስተኛው ኃይል (The third Force) የሚባል ፀረ-ለውጥ የሆነ የሽብር ቡድን አቋቋሙ።

“ሦስተኛው ኃይል” የተሰኘው ህቡዕ ቡድን ከክልል ሚሊሺያዎች እና ልዩ ፖሊስ ኃይል የተወጣጣ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ ጦር ሰራዊት ስልጠና እና የትጥቅ ድጋፍ እየተደረገለት የፀረ-አፓርታይድ ትግሉን ለማጨናገፍ የሚንቀሳቀስ ነው። ይህ ቡድን በተለይ “KwaZulu Natal” በሚባለው ክልል በዜጎች ላይ የፈፀመው ግድያና ማፈናቀል ከባለፈው አመት ጀምሮ የሶማሊ ክልል ልዩ ኃይል በምስራቅ ኦሮሚያ ከፈፀመው አንድና ተመሳሳይ ነው። በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ በተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ጎሳዎችና ብሔሮች መካከል የእርስ-በእርስ ግጭት ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ዛሬ ላይ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ እና አፋር ክልሎች ከሚታዩት ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው።

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርዓት በተለያዩ ብሔሮችና ጎሳዎች መካከል ግጭትና ሁከት በመፍጠር የነጮች የበላይነትና ተጠቃሚነትን ለማስቀጠል ካደረገው ጥረትና ካስከተለው ውጤት ዛሬ ሀገራችን ኢትዮጲያ ያለችበትን ሁኔታ በግልፅ ይጠቁማል። በደቡብ አፍሪካ በተለይ እ.አ.አ. ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የጥቁር ጎሳዎችና ብሔሮች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍጠር በሕቡዕ የተሰራው ስራ እ.አ.አ. ከ1990 – 1994 ዓ.ም ባሉት አራት አመታት ውስጥ ፍሬ አፍርቷል። በመጨረሻዎቹ አራት አመታት ውስጥ ብቻ በብሔርና ጎሳ ግጭት 14,000 የደቡብ አፍሪካ ዜጎች ለሞት ተዳርገዋል። የአፓርታይድ ስርዓት ከ1990 – 1994 ዓ.ም ባሉት የመጨረሻ አራት አመታት ባስነሳው የብሔር ግጭትና ብጥብጥ የተገደሉት ጥቁሮች ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አራት አስርት አመታት ከገደላቸው ሰዎች ብዙ እጥፍ ይበልጣል።