የለውጥ  እርምጃ  እንዳይቀለበስ

ሱራፌል ተሾመ (ዶ/ር)

በዘመናት ህዝባዊ ብሶት የተለኮሰው የለውጥ ባቡር ይገሰግሳል:: ባንድ በኩል የህዝብ ድምጽ ከመሪ አፍ ሲወጣ እየሰማን ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ በአፋኝነት በተደራጀ ሙስና እና በማን አለብኝነት ዘመናቸውን የፈጁ የያለፈው ዘመን አዋካቢዎች የለውጡን ባቡር በቻሉት መጠን ለመግታትና የለውጡን አራማጆች ከፋፍሎ እየተሰበከ ባለው አንድነት ላይ ጥላሸት ለመቀባት ጊዜ እያባከኑ አይደለም::
ይህን ጥረታቸውን ስልጣኑንና መላው የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ አውታር እንደ ርስት ተቆጣጥረው በነበረበት ወቅት አሳይተው ቢሆን ኖሮ ሀገራችን ከድህነት ወጥታ ህዝቦቿም ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችንን ተጎናጽፈን በተገኘን ነበር:: የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነበር መንግሥታዊ ስልጣንን ለዝርፊያ፣ የሀገር ሀብትን ለግልና ቡድን ጥቅም፣ የመብት ጥያቄን ደሞ ወደ ቃሊቲ እና ቂሊንጦ::

ሀሳባቸውን በነጻነት ስላራመዱ ብቻ እስር ቤት ተወርውረው፣ በየሀገሩ ተሰደውና በየበርሃው መሽገው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ሀይሎች አዲሱ የፖለቲካ አስተሳሰብ በፈጠረላቸው ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው የነጻነትን አየር መተንፈስ ሲጀምሩ፤ የአፈናው ተዋናዮች ደግሞ የለመዱትን ዛቻ ማስፈራሪያ እና አሻጥር (sabotage) የሙጥኝ ብለው ባልሞት ባይ ተጋዳይነት ለመጽናት መምረጣቸው አሳዛኝ ክስተት ነው::

መዶሻን ብቻ የሚያውቅ ባለሙያ ሁሉም ችግር ሚስማር መስሎ ይታየዋል” የሚባል ተረት አለ:: ማፈን መምታት ማስፈራራትና መጨቆን የለመደ ስርዓትም እንዲሁ ሁሉም ህዝባዊ ጥያቄ በማሰርና በመግፋት የሚዳፈን ይመስለዋል:: አሁንም ቢሆን ከዚህ አስተሳሰብ ያልተላቀቁ ባለመዶሻዎች በየድጋፍ ሰልፉ የሚወጣውን ወጣት፣ የሚውለበለበውን ባንዲራ፣ የሚያነሳውን መፈክር እንደ ሚስማር ቆጥረው ሊመቱት እንጂ ስህተታቸውን የሚገነዘቡበትና ጊዜ እንደከዳቸው የሚያስተውሉበት የመንቂያ ደውል አድርገው መውሰድ አልቻሉም::

ለነጻነት ፍትህና እኩልነት የተጀመረው እርምጃ በተለያዩ ጊዜ በለስ ቀንቷቸው ስልጣን የተቆናጠጡ መሪዎችና ከኋላቸው ያሰለፉት ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሃይል የህዝብን ድምጽ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለታቸው ምክንያት የሀገራችን ሁለንተናዊ ችግር እየተባባሰበትና ጽንፈኝነቱም በዛው ልክ አይሎ ከውጤት ሳይደርስ አሁን ያለንበት ደረጃ ደርሰናል:: አዲሱ መሪና ከኋላቸው ያሰለፉት ህዝባዊ ድጋፍ ሀገሪቷን ከዚህ የፖለቲካ ቁማር አውጥቶና የተጋረጠበትን የ ቅልበሳ አደጋ መክቶ ሀገሪቷን ወደ አዲስ የፖለቲካ አቅጣጫ እንዲመራ እንጂ በ መሰናክሎች እንዳይደናቀፍ፣ ለውጥ ፈላጊው ሃይል የመቀናጀትና የመቀራረብ ስራ ሊሰራ ይገባል::

በኔ ግምት ለውጥ መምጣቱ ግድ ነው። ለውጡ ሁሉን ያሳተፈና ማንንም ያላገለለ መሆኑ ደግሞ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነገር ነው:: ሀገራችን ብዙ ያልተፈቱ ውስብስብ ጥያቄዎች ያሉባት እንደመሆኑም ችግሮቻችን በአንድ ጀምበር ብን ብለው የሚጠፉ አይደለም:: ዋናው ነገር ለለውጥ የምንራመድበት አቅጣጫ ትክከለኛ ነው? ወይስ እንደቀድሞቅው አዙሪት ወስዶ ምንም ፈቀቅ ሳያደርገን የጥቂት ባለጊዜዎችና ባልንጀሮቻቸው መበልጸጊያ የሚሆን የይስሙላ እርምጃ ነው የሚለው ጥያቄ ነው::

አሁን የምናየውን ለውጥ ካለበት ደረጃ እንዲደርስ መስዋእትነት ጭምር በመክፈል የመሩት የቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ እና መሰል የለውጥ ሃይሎች የተጀመረው ጉዞ ግቡን እስኪመታና ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትህና እኩልነት በመላው ኢትዮጵያ ያለገደብ እስኪረጋገጥ ድረስ የህዝብ ድምጽን በሰላማዊ መንገድ በማሰማትና ኃይላቸውን በማስተባበር ጭምር መቀጠል አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው::