ለውጡን ለማስቀጠል ኃይላችንን ማቀናጅት አለብን

ለውጡን ለማስቀጠል ሃይላችንን ማቀናጀት የለውጥ ማዕበል አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ሰተት ብሎ ይግባ እንጂ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የተተበተበውን የሙስናንና የኢሰብዓዊ ድርጊት መረብን በጣጥሶ፣ መላው የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አውታሮች እስኪቆጣጠርና የታገልንለት ነጻነትና እኩልነት ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ያለገደብ እስኪረጋገጥ ድረስ የንቁ ኢትዮጵያውያንን ክትትልና ድጋፍ ይፈልጋል::

ይህ እንግዲ ለውጡን የማጠናከር ተቀዳሚ ተግባር ነው:: ምሁራን ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመተንተን፣ ወጣቱ እስካሁን ሲያደርግ እንደቆየው በየአካባቢው በመደራጀትና የህዝብ በደልና ጥያቄን ወደፊት ይዞ በመውጣት፣ አባቶችና እናቶች ለውጥ ፈላጊው ሃይል በስሜታዊነት እንዳይነዳ በመምከር፣ የሚድያ ተቋማት የህብረተሰቡን ሞራል በመገንባትና በአልሞት ባይ ተጋዳይነት የሚጠነሰሱ ሴራዎችን በማጋለጥ፣ ተራማጅ ሆነው ለውጡን የሚመሩ ኃይሎች ደግሞ የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት በሳል እርምጃዎችን በመውሰድ፣ የሚድያ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን እና ሌሎችም አካላት የለውጡ አስተሳሰብ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሙሉ ለሙሉ ድል እንዲመታ ለማስቻል አንደበታቸውን፣ ካሜራቸውን፣ ማይክራፎናቸውን፣ ስልካቸውን፣ ኪሳቸውን፣ ብእራቸውናና የኮምፕዩተር ኪቦርዳቸውን እንደሰላ ሰይፍ ሊጠቀሙበት ይገባል::

ይህን በማድረግ ሁለት ግቦች ማሟላት ይቻላል::

  • አንደኛ ለውጡን እየመሩና እየተገበሩ ላሉ የቁርጥ ቀን ልጆች የስነልቦና ስንቅ ማስታጠቅ ሲሆን
  • ሁለተኛው ደግሞ እየከሰሙና ከሀገራችን ፖለቲካ መድረግ ላይመለሱ እየፈረጠጡ ላሉ ነገር ግን ይህንን እውነታ አንድም ለዘመናት ከተዘፈቁበት የእብሪት ጀልባ መውረድ ባለመቻላቸው ሁለተኛም የሚቀርባቸውን የምቾትና የበላይነት ሕይወት ከማጣት ይልቅ ሀገር ማመስን ሥራዬ ብለው ለያዙ የፖለቲካ ጡረተኞች ሕዝባዊ መሠረት እንደሌላቸውና ጊዜው ላይመለስ እንዳለፈባቸው አስረግጦ ለመንገር ይጠቅማል::

የለውጡ ጠላቶች ጥቂቶች ቢሆኑም ባለፉት ዘመናት ከደሃ ገበሬ በመዝረፍ ያጋበሱት ሃብት እና አኩይ ተግባራቸውን ባደባባይም በጓዳም የሚፈጽምላቸው ህሊናውን የማያማክር ቅጥረኛ እንዳላቸው ግን ልንረሳ አይገባም:: ብርታታቸው ዘርና ብሄርን መሰረት ያደረገ ጥቃትን ማቀናበርና እርስ በእርስ አናክሰው ህዝብን በፍረሃት እንዲዋጥ ማድረግ ቢሆንም ድክመታቸው ግን የለውጡ ሃይል ሲተባበር የሚመልሱለት መልስም ሆነ ስር ድረስ የሰደደውን ህዝባዊ እምቢተኝነት የሚቋቋም ብርታት የላቸውም:: ክብራቸው በነውራቸው የሚባለው አይነት::

የለውጥ ፍላጎት በአንድ ብሄር ወይም በአንድ አካባቢ ብቻ የሚሰማ ድምጽ አይደለም:: ይልቁንም በመላው የሀገራችን ህዝቦች በግልጽ እየተራመደ የሚገኝ የጊዜው ዋነኛ አጀንዳ ነው:: ለውጥ ጠያቂውም ሆነ መሪዎቹ በተለያየ የማህበረሰብ ክፍል ውስጥ የሚገኙና የተለያየ የትግል ስልት የተከተሉ ቢሆንም ዳሩ ግን የጋራ ራዕያቸው ሰብዓዊ መብት ጥሰት የማይፈጸምባት፣ የብሄርና የመደብ የበላይነት የማይታይባት፣ ሁሉን እኩል የምታስተናግድ የጋራ ሀገር መገንባት እንደሆነ አምናለው:: አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታም ያረጀ ያፈጀውንና ባማናለብኝ ስሜት የተቃኘውን አሮጌ አስተዳደራዊ ስርዓት ገርስሶ በምትኩ ሌላ በዝባዥና ልዩ ተጠቃሚ ቡድን የመፍጠር ፍላጎት ቦታ ያለው ጉዳይ አይደለም::

የለውጥ አራማጁ ሃይልና የሚወክለው ሕብረተሰብ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ሊኖረው ቢችል አስገራሚ ጉዳይ አይደለም:: በሕገመንግሥታዊ ማሻሻያ ነጥቦች፣ በታሪክ አተረጓጎም፣ በባንዲራ አጠቃቀም እና መሰል ነጥቦች ላይ ሁሉም ሕብረተሰብ የተስማማበት የጋራ ድምዳሜ ያለ አይመስለኝም:: እነዚህ እና ሌሎች የልዩነት ነጥቦችን ነቅሶ በማውጣት፣ ሀሳብን አንሸራሽሮ የመደራደር ስራ ወደፊት ይጠብቀናል:: ምናልባትም ይህን አይቀሬ የቤት ስራ ካሁኑ መጀመር አስፈላጊ ሊሆን ይችላል::

የጋራ ሀገራዊ መግባባትና አስፈላጊም ከሆነ ብሄራዊ እርቅ ለመፍጠር መንቀሳቀሻ ጊዜው አሁን ነው:: ላለፉት 27 አመት ሀገሪቷን ሲበዘብዝና ህዝቦቿን ሲያሰቃይ የነበረውን አስተዳደር ለማስወገድ ከሚደረገው ትግል ጎን ለጎን መገንባት ስለምንፈልጋቸው ሀገራዊ ማንነቶችና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲሁም ሊኖር ስለሚችለው ይቅርታ፣ ምህረት እና ቅጣቶች የለውጡ መሪዎች ተቀራርበው መነጋገር መጀመር ይኖርባቸዋል:: የቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ እና ሌሎች የወጣት ተራማጅ መሪዎች በክልላቸው ያፋፋሙትን ትግል ከማስቀጠል ባሻገር እርስ በርሳቸው ተቀራርበው መምከርና በቀጣይ እርምጃቸው ዙርያ የመቀናጀት መንገድን ቢከተሉ የለውጥ ሂደቱን ከማፋጠን ባሻገር የሚቃጣባቸውን ጸረ አብዮት ጥቃት በቀላሉ ለመመከት ያስችላቸዋል:: በጋራ ጠላት ላይ አብሮ መዝመት ብቻ በቂ የትግል ስልት አይደለም በተለይም የምንታገለው አካል ከፋፍሎ መሰባበርን የተካነበት እንደመሆኑ የለውጥ ሃይሎች ከጋራ ጠላት ባሻገር የጋራ ራእይና አቅጣጫ እንዲኖራቸው የሚሰሩበት ወቅት አሁን ነው::

ሱራፌል ተሾመ (ዶ/ር)

ከኔዘርላንድስ

One thought on “ለውጡን ለማስቀጠል ኃይላችንን ማቀናጅት አለብን

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡