የማህበራዊ የበላይነት ጽንሰ ሀሳብ (Social Dominance Theory):- ክፍል 3

መግቢያ
የማህበራዊ የበላይነት ጽንሰ ሀሳብ (ማበጽ) የማህበበረሰብና የቡድኖች የርስበርስ ግንኙነት ንድፈ ሀሳብ ሲሆን ሰዎች ተቋማዊ የበላይነትን እንዲደግፉ ተዋረዳዊ (የስልጣን) ዉቅር የሚደግፍ የአስተሳሰብ መዋቅርን እንዴት እንደሚገነቡ ያትታል፡፡ ቡድን-መራሽ ማህበራዊ የበላይነት እንዴት እንደሚፈጠርና እንደሚጸና ያጠናል፡፡ እንዲሁም አንድ የበላይ የሆነ ቡድን ሌሎች ላይ ተጠቃሚነቱን እንደሚያረጋግጥበትን መንገድ ይተነትናል፡፡ ከቡድኖቹ መካከል ትኩረት የሚደረግባቸዉ የዘር የጾታ የብሄርና የሌሎች መበላለጦች ይገኙበታል፡፡ ለየት የሚያደርገዉ የቡድኖችን የእርስበርስ ግንኙነት ማህበራዊ ስነልቦና ጽንሰ ሀሳብን ከማህበራዊ ርዮተ ዓለምና ከማህበራዊ መበላለጥ ተገቢነት አጣምሮ ማጥናቱ ነዉ፡፡

ሀተታ
የመንግስት ቅርጽ አስተሳሰብና የኢኪኖሚ ስርዓቱ ምንም ይሁን ምን ስዎች ቡድን ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ እርከን የመመስረት ዝንባሌ አላችዉ፡፡ ይህ ሲሳካ አንዱ ቡድን በማህበራዊ ደረጃም ሆነ ስልጣን ከሌሎች የተሻለ መልኩ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በዚህ እይታ ያንድ ሀገር ህዝብ የበላይና የበታች ተብሎ ሊከፈል ይችላል፡፡

የበላይነትን የተጎናጸፈ ቡድን ያልተመጣጠነ አዎንታዊ ማህበራዊ እሴቶች (positive social value ) ተጠቃሚ ሲሆን እነዚህ አዎንታዊ ማህበራዊ እሴቶችም የፖለቲካ ስልጣን፣ ሀብት፣ የጉልበት ከለላ (protection by force)፣ የተመጣጠነና የተመረጠ ምግብ፣ የተሻለ የቤት አቅርቦት፣ የጤና፣ የመዝናኛ ጊዜና ትምህርት ናቸዉ፡፡ በሌላ በኩል ያልተመጣጠነ አሉታዊ (Negative ) ማህበራዊ እሴቶች – ማለትም ዝቅተኛ ደረጃ ቤቶች፤ በሽታ፤ ዝቅተኛ ስራ እድል፤ አደገኛና የተናቁ ስራዎች፤ ያልተመጣጠነ ቅጣት፤ መጥፎ ስምና ፍረጃ -ደግሞ በዉዴታም ይሁን በግዴታ የበታች የሆኑ ቡድኖች ላይ ይጫናሉ፡፡

Social Dominance Orientation

እንደ ማበጽ ቡድን-መራሽ ማህበራዊ የበላይነት የሚፈጠረዉ በዘርፈ ብዙ የማግለል ዉጤቶች ምክንያቶች ነዉ፡፡ እነዚህም ግለሰባዊ፤ ተቋማዊና በቡድኖች መካከል ያለዉ የትብብር ሂደቶች ናቸዉ፡፡ዘርፈ ብዙ ማግለሎቹ የሚከናወኑትና የሚዋቀሩት የበላየነትን የተጎናጸፈን ቡድን ከበታቹ ቡድን ላይ ለማንገስ ሲሆን ይህም የሚፈጸመዉ የዉገና ድርሰቶችን ተገቢነት በማረጋገጥ (Legitimising myths) ነዉ፡፡ የዉገና ድርሰቶችን ተገቢነት ማረጋገጥ (Legitimising myths) አንድ ህዝብ በመግባባት ያቆያቸዉ እሴቶች፤ ጠባዮች፤ እምነቶች፤ የተዛቡ አመለካከቶችና ባህላዊ ርዮተ ዓለማት ማለት ነዉ፡፡

በዚህ መሰረት ማበጽ እንደሚለዉ የአንድ ቡድን የበላይነት የሚረጋገጠዉ ጉልበትን በመጠቀምና በማስፈራት ብቻ ሳይሆን ከዛ ህዝብ በሚወጡ ግለሰቦች ዉሳኔዎችና ፀባይ፤ አዲስ ማህበራዊ ተግባራትን/ድርጊቶችን በመፍጠርና በተቋማዊ አሰራር ናቸዉ፡፡ እነዚህም በበኩላቸዉ የሚቀረጹት የዉገና ድርሰቶችን ተገቢነት በማረጋገጥ ነዉ፡፡ የጭቆና ድርጊቶችን ተቋማዊ ማግለሎችንና፤ ግለሰባዊ አድሎዎችን ተገቢነት ለማረጋገጥም ሆነ ለመኮነን “Legitimising myths” ጠቃሚ ነዉ፡፡ የዚህ መገለጫዎች ዉስጥ ከምርጥ ዘር መፈጠር፤ የታሪክ የበላይነት፤ ጦርነት ማሸነፍ፣ ዉርስ፤ የትግል አስተዋጽኦ፣ ስልጣኔ፣ ወዘተ ናቸዉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ህወሐት ደርግን በጦርነት ማሸነፉን እንደ “Legitimising myths” ይጠቀምበታል፡በመሆኑም የግለሰቦች የተቋማትና አዲስ የሚፈጠረዉን ማህበራዊ ድርጊቶች አስተሳሰብና አሰራር ከዚህ አኳያ እንዲቃኝ አድርጓል፡፡

በተያያዘ “Legitimising myths” ለሁለት አላማዎች ይዉላል፡፡ 1ኛ- ማህበራዊ የደረጃ ልዪነት የሚያጠናክር “Hierarchy-enhancing legitimising myths” (HE-LMs) ሲባል አላማዉም ለቡድን-መራሽ ማህበራዊ ጭቆናና መበላለጥ ተገቢነት ሞራላዊና እዉቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ እጣ ፋንታ፤ በእግዜር ፈቃድ፤ ምርጥ ዘር፤ ድል አድራጊ፤ ልማታዊ፤ ህግ አክባሪ፤ ታታሪ፤ ምርጫ ያመጣዉ መሆኑን ያስተምራል፡፡ በተጨማሪም HE-LMs አንዱ ከሌላዉ የበለጠ ተጠቃሚ መሆኑ ተገቢ ፍትሐዊ ተፈጥሯዊና ሞራላዊ እንደሆነ ያትታል፡፡ ግለሰቦችን ቡድኖችንና ተቋማዊ አሰራርን ሲያደራጅ ያንዱን የበላይነትን ከማስቀጠል አኳያ ብቻ ሳይሆን ጭቆናዉ ለማስቀጠል እንዲረዳ የበታች የሆኑ ቡድኖችም እንዲተባበሩ ያደርጋል፡፡ ለዚህ አላማ ከሚዉሉት ዉስጥ ሽብርተኞችን መዋጋት የሀይማኖት አክራሪነት የወንጀል ህግ ብሔራዊ ጥቅም ሉአላዊነት ብሔራዊ ደህንነት ቡድኖችን ፍረጃ የተዛቡ አመለካከቶችን በማሰራጨት… ወዘተ በዘዴ ስራ ላይ ማዋል ናቸዉ፡፡ የበላይነት የተጎናጸፍ ቡድን እነዚህን ተገን አድርጎ ሌሎች ቡድኖችንና ግለሰቦችን ያሸማቅቃል፤ ድጋፍ ያገኛል፤ ይወነጅላል፤ ያስገድላል፤ ያፈርሳል፤ ሀብት ይወርሳል፤ ከጥቅም ዉጪ ያደርጋል፡፡

“Hierarchy-enhancing legitimizing myths” ሚና በዚህ ይወሰንም፡፡ ማናቸዉም ህጎች አዋጆች ድንጋጌዎች አሰራሮች መመሪያዎች ወዘተ በስርዓቱ ዉስጥ ሲወጡ መመዘኛቸዉ የበላይነት የተጎናጸፈን ቡድን ጥቅምና ደህንነት ማስከበሩ ነዉ፡፡ ለምሳሌ መንግስት ከመሰረታዊ እቅዱ እስከ ጥቃቅን መመሪያዎች ያሉትን ሲቀርጽ- የመሬት አዋጅ ሲያወጣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲቀርጽ መዋቅር ሲገነባ የግዢና ጉምሩክ አዋጅ ሲያዉጅ የመኖሪያ ቤቶች ሲገነባ የንግድ ስርዓት ሲዘረጋ ወዘተ- በህዝብና በሀገር ስም ቢሆንም ቁምነገሩ የአንድን ቡድን የበላይነት በሚያረጋግጥ መልኩ ይፈጸማል፡፡ በተለይም ደግሞ የበታች ቡድኖችን ለመጥቀም የሚሰጡት ዉሳኔዎችም ሲወሰኑ ጭምር የበላዮቹ በተለየ እቅድ እንዲጠቀሙ ያደርጋል፡፡ አንድ ማሳያ ለማየት ያህል የመንግስትን የግዢ ዝርክርክነት ለመቅረፍ የግዢ ኤጄንሲ ሲቋቋም በተመሳሳይም ኤጀንሲዉ የበላይነት ከተጎናጸፈ ቡድን ብቻ ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ የበላይነታቸዉን ሲያጠናክር ሌሎች ነጋዴዎች ከንግዱ እንዲወጡ ያስገድዳል፡፡

ሁለተኛ ማህበራዊ የደረጃ ልዪነት የሚያቀጭጭ (hierarchy-attenuating legitimizing myths (HA-LMs)) ቡድን-መራሽ ማህበራዊ መበላለጥን የሚቀንስና በህዝቦች መካከል እኩልነት እንዲመጣ ይደግፋል፡፡ ለምሳሌ ሰብአዊ መብቶች መረጋገጥ ማህበራዊ ፍትህ ዲሞክራሲ “affirmative action” ወዘተ መገለጫዎቹ ናቸዉ፡፡ የዚህ አስተሳሰብ ጭብጥ ፍትሀዊ የሀብትና የደህንነት ስርጭትን በማስፈን የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲሆን እግረ መንገዱንም የተዛባዉን ጭቆናና መበላለጥ ይከልሳል ይቀንሳል፡፡ በሌላ በኩል የበላይነት የተጎናጸፈ ቡድን ለዚህ አይነት አስተሳሰብና አሰራር ሁሌም እንቅፋት ሆኖ መቅረቡ አይቀርም፡፡ ሆኖም ህግ አዉጭዉና ህግ አስፈጻሚዉ አካል እንዲ ካለ ቡድን ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ መስራት ከቻለ ጭቆናዉንና መበላለጡን መቀነስ ይቻላል፡፡

ይቀጥላል…
ቀጣዩ ጽሁፍ፡ “የአንድ ቡድን/ህዝብ የበላይነት አለን? አንድ ቡድን እንዴት የበላይነቱን ያረጋግጣል?” የሚሉትን ጥያቄዎች በዝርዝር እንመለከታለን፡፡


ፀሃፊው Gemechis A Duguma በፌስቡክ ገፁ ሃሳብና አስተያየት መስጠት ይቻላል፡፡

2 thoughts on “የማህበራዊ የበላይነት ጽንሰ ሀሳብ (Social Dominance Theory):- ክፍል 3

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡