“የመደመር ጉዞ”፡- ሐምሌ 10/2010 ዓ.ም 500 ሰዎች በመኪና ወደ አስመራ ይጓዛሉ!

የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በኤርትራ ያደረጉት ጉብኝት ስኬታማ መሆኑን በመጥቀስ ለኤርትራ ፕረዜዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የምስጋና ደብዳቤ ፅፈዋል። ከዚህ በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉታሬዝን ጨምሮ የጎረቤት ሀገራት መሪዎች እና ድርጅቶች ድጋፋቸውን ገልፀዋል። በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረመው የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ጦርነት በይፋ በማስቆምና አዲስ የግንኙነትና ወዳጅነት ምዕራፍ መጀመሩን አብስሯል። በዚህ መሰረት ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካ፥ ኢኮኖሚ፥ ማህበራዊ፥ ባህላዊና የጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ በትብብር እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በሁለቱ ሀገራት መካከል ተቋርጦ የነበረው የአየርና የየብስ ትራንስፖርት፥ የስልክ ግንኙነት እና የንግድ እንቅስቃሴ ዳግም ማስጀመር የስምምነቱ አካል መሆኑ ተገልጿል። ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጣይ ሳምንት ሐምሌ 11/2010 ዓ.ም ወደ አስመራ በረራ እንደሚጀምር የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል። አየር መንገዱ ቦይንግ 787 አውሮፕላን የመደበ ሲሆን 250 ሰዎችን ያሳፍራል። በዘገባው መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገዱ ትኬት መሸጥ የጀመረ ሲሆን የደርሶ መልስ ትኬት ዋጋም 8944 ብር እንደሆነ ተገልጿል። በአዲስ አበባ የሚገኙ የኤርትራ ዲፕሎማቶች ወደ ኤርትራ ለጉብኝት የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያን አስመራ ሲደርሱ ቪዛ ማግኘት እንደሚችሉ የገለፁ ሲሆን ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ግን የፓስፖርት ኮፒ ቀድሞ ወደ አስመራ መላክ እንዳለበት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሐምሌ 11/2010 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ላይ ወደ አስመራ የሚያደርገው በረራ ታሪካዊና ሊበረታታ የሚገባ ነው። ነገር ግን፣

  • 1ኛ) በሁለቱ መሪዎች የተፈረመው የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት በህዝብ-ለህዝብ ግንኙነት አማካኝነት በተግባር መረጋገጥ ስላለበት፣
  • 2ኛ) የየብስ ትራንስፖርት የህዝብ-ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ከአየር ትራንስፖርት የተሻለ በመሆኑ፣
  • 3ኛ) በስምምነቱ መሰረት በሁለቱ ሀገራት መካከል የአየር ብቻ ሳይሆን የየብስ ትራንስፖርት ጭምር እንደሚጀመር በመገለጹ፣
  • 4ኛ) ብዙ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ታሪካዊ ጉዞ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም በአውሮፕላን የሚጓዙት 250 ሰዎች ብቻ ስለሆነ፣
  • 5ኛ) አየር መንገዱ ለአንድ የደርሶ መልስ ትኬት የሚያስከፍለው 8944 ብር ለብዙዎች ውድ በመሆኑ፣

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ጎን-ለጎን “የመደመር ጉዞ” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀ የጉዞ ፕሮግራም አምስት መቶ (500) ኢትዮጵያዊያን በአስር (10) አውቶብስ መኪኖች ወደ አስመራ ከተማ ለመጓዝ ቅድመ-ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ለዚህም አምስት አባላት ያሉት “የመደመር ጉዞ አስተባባሪ ኮሚቴ” የተዋቀረ ሲሆን በዛሬው ዕለት ተገናኝቶ ሊደረግ ስለሚገባው ቅድመ-ዝግጅት ተወያይቷል። በዚህ መሰረት አስተባባሪ ኮሚቴው በሀገር ውስጥ ካሉ የትራንስፖርት ድርጅቶች በመነጋገር፣ እንዲሁም ከምግብና መኝታ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚያስፈልገውን ወጪ ደግሞ በአስመራ ከሚገኙ አስተባባሪዎች ጋር በመነጋገር የትኬት ዋጋውን ለመተመን በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የትኬቱ ዋጋ እና ለዚህ አገልግሎት የሚከፈተው የባንክ ሂሳብ ቁጥር ለህዝብ ይፋ የሚደረግ ይሆናል።

ከላይ በተጠቀሰው የባንክ ሂሳብ የትኬቱን ዋጋ ቀድመው የከፈሉ 500 ሰዎች “የመደመር ጉዞ” የመጀመሪያ ተጓዥ በመሆን ሐምሌ 10/2010 ዓ.ም ወደ አስመራ ይጓዛሉ። በማግስቱ ሐምሌ 11/2010 ዓ.ም ረፋዱ ላይ አስመራ ከተማ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። በቀጣዩ ሙሉ ቀን በአስመራ ከተማ ቆይታ ካደረገ በኋላ ሐምሌ 13/2010 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የመልስ ጉዞ ይጀመራል። ከአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የሚጀምረው ጉዞ በመቐለ-አስመራ ሲሆን የመልስ ጉዞው ደግሞ ከአስመራ-ጎንደር-ባህር ዳር-አዲስ አበባ እና ከአስመራ-አሰብ-ሰመራ-አዲስ አበባ በአንዱ ይሆናል። በመሆኑም የመደመር ጉዞ ፕሮግራም ከኤርትራና ኢትዮጵያ ሕዝቦች በተጨማሪ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልል መካከል ያለውን የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል።

ከላይ በተገለፀው መሰረት የመደመር ጉዞ ፕሮግራም በኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች የተፈረመውን የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት በተግባር ለማረጋገጥ ያስችላል። በሁለቱ ሀገራት መካከል የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነት ከመጀመር በተጨማሪ በኢትዮጵያዊያን መካከል ያለውን የአንድነትና አብሮነት መንፈስ ያጠናክራል። ይህ የጉዞ ፕሮግራም በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስት አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር እንደሚደረግለት አስተባባሪ ኮሚቴው ያምናል። በመሆኑም በተለይ የኢፊዲሪ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራ ዲፕሎማቶች ለዚህ ታሪካዊ ጉዞ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉ ይጠይቃል። በዚህ ታሪካዊ ጉዞ መሳተፍ የሚሹ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ አስፈላጊውን ቅድመ-ዝግጅት በማድረግ እንዲጠባበቁ እናሳስባለን።

“የመደመር ጉዞ” አስተባባሪ ኮሚቴ