የኦሮሚያ ክልል የስነ ምግባር ጉድለት የታየባቸው 11 ዳኞችን አሰናበተ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል የስነ ምግባር ጉድለት ያሳዩ 11 ዳኞች ከስራቸው መባረራቸው ተገለፀ።

ይህ የተገለፀው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ደሳ ቡልቻ የክልሉን ፍርድ ቤት የ2010 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2011 በጀት ዓመት እቅድ ሪፖርትን ለጨፌ ኦሮሚያ ባቀረቡበት ወቅት ነው።

በሪፖርታቸውም ከፍተኛ የስነ ምግባር ጥሰት ፈፅመዋል በሚል ለክልሉ የዳኞች ጉባዔ የቀረቡ 11 ዳኞች እና 8 የፍርድ ቤት ሰራተኞች ከስራቸው እንዲሰናበቱ መደረጉን አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በፍርድ ቤት ውስጥ በተለያዩ የስራ ሀላፊነት ላይ ሲያገለግሉ የነበሩ እና የስነ ምግባር ጥሰት የፈፀሙ የተለያ ግለሰቦች ላይም እርምጃ መወሰዱን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

በዚህም መሰረት 4 ሰዎች ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ፣ 43 ሰዎች ከደሞዛቸው ዝቅ እንዲሉ እና 12 ሰዎች ደግሞ አሁን ከሚገኙበት ደረጃ ዝቅ ብለው እንዲሰሩ መደረጉንም አቶ ደሳ ገልፀዋል።

በሰርካለም ጌታቸው

ምንጭ፦ FBC