ወደ አሥመራ ለመጓዝ ምን ያስፈልጋል?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሃያ ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የአሥመራ በረራውን ማክሰኞ ሐምሌ 17/2010 ዓ.ም ሊጀምር መሆኑን አሳውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በኤርትራ ያደረጉትን ይፋዊ ጉብኝት ተከትሎ የሁለቱ አገራት መሪዎች ከደረሱባቸው ስምምነቶች መካከል አንዱ የሆነው የአየር ግንኙነትን የመጀመር ውሳኔን ተከትሎ ነው ይህ ይፋ የሆነው።

“ዛሬ ትግርኛ የለ፣ አማርኛ የለ! ቋንቋው ጠፍቶብኛል” ዐብይ አሕመድ

ኢትዮጵያና ኤርትራ፦ ከእራት በኋላ ምን ተወራ?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳሳወቀው ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ለሚያደርገው ለዚህ በረራ በአሁኑ ወቅት ተጠቃሽ ከሆኑት ዘመናዊ አውሮፕላኖቹ መካከል አንዱ የሆነው ቦይንግ 787ን እንደሚያበር አሳውቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አዲስ ምዕራፍ

በአሁኑ ወቅት ወደ ኤርትራ ለመጓዝ ያሰበ ሰው ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?

ቪዛ

ኢትዮጵያዊያን ወደ ኤርትራ ለመጓዝ ቪዛ ስለመጠየቃቸው እሰካሁን ይፋዊ የሆነ መረጃ ባይወጣም፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ የኤርትራ ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ለጉብኝት የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያን አሥመራ ሲደርሱ ቪዛ ማግኘት ይችላሉ ብለዋል። ጨምረውም ከጉዞ በፊት የተጓዦች የፓስፖርት ኮፒ ወደ አሥመራ ይላካል።

የአውሮፕላን ቲኬት

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጀመሪያ በረራው ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከጠዋቱ 3 ሰዓት በመነሳት በቀጥታ ወደ አሥመራ ጉዞ ያደርጋል።

ለምሳሌ ሐምሌ 13 2010 ዓ.ም ጉዞውን ወደ አሥመራ አድርጎ ሐምሌ 18 ወደ አዲስ አበባ የሚመለስ ተጓዥ ለአየር ቲኬት 7106 ብር እንዲከፍል ይጠየቃል።

የጉዞ ቲኬት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የሞባይል መተግበሪያ አሊያም ከአየር መንገዱ ድረ-ገጽ ላይ አሁን መግዛት ይቻላል።

1 ሰዓት ከ 10 ደቂቃ በሚፈጀው በረራ ጥቅም ላይ ይውላል የተባለው 787 ድሪም ላይነር ከ250 መንገደኞች በላይ የማሳፈር አቅም አለው።

የገንዘብ ምንዛሬ

አሥመራ ላይ በብር መገበያየት አይቻልም። የኤርትራ መገበበያ ገንዘብ ናቅፋ ይባላል። 1 የአሜሪካን ዶላር በ15 ናቅፋ ይመነዘራል።

ሆቴል

ከአዲስ አበባ ጋር ሲነጻጻር በአሥመራ በርካታ የሆቴል አማራጮች ላይገኙ ይችላሉ።

በአሥመራ መሃል ከተማ ለአንድ ቀን አዳር በአማካይ ከ45 – 70 የአሜሪካን ዶላር ሊጠየቁ ይችላሉ። ይህን ያህል ዋጋ የሚጠየቅባቸው አብዛኛዎቹ ሆቴሎች ቁርስ የተካተተባቸው ሲሆን ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎትም የሚሰጡ ናቸው።

ከላይ ከተጠቀሰው ዋጋ የሚያንሱ የአንግዳ ማረፊያዎች (ፔኒሲዮኖች) በአሥመራ ከተማ ውስጥ ይገኛሉ።

ምግብ እና መጠጥ

አማካይ በሆነ የአሥመራ ምግብ ቤት ውስጥ አንድ ጥብስ ከ100-125 ናቅፋ (6-8 የአሜረካ ዶላር) ድረስ ሊሸጥ ይችላል።

የለስላሳ መጠጦች 8 ናቅፋ ገደማ ይጠየቅባቸዋል።

በኤርትራ ”አሥመራ ሜሎቲ” የሚባል አንድ የቢራ አይነት ብቻ ነው ያለው። ለአንድ አሥመራ ሜሎቲ ቢራ 18 ናቅፋ ይከፍላሉ።

የትራንስፖርት አገልግሎት

ከአሥመራ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እሰከ መሃል ከተማ ለመጓዝ የህዝብ አውቶብስ ወይም ታክሲዎችን መጠቀም ይችላሉ። የህዝብ አውቶብስ ከተጠቀሙ 2 ናቅፋ ብቻ የሚከፍሉ ሲሆን 4 ሰው የምትይዘውን ታክሲ ከመረጡ ግን 20 ናቅፋ ይጠየቃሉ።

በኤርትራ ቆይታዎ ከአሥመራ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 113 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘውን ምፅዋንም መጎብኘት የሚሹ ከሆነ የህዝብ አውቶብስ በመያዝ ከሁለት ሰዓት ጉዞ በኋላ መድረስ ይችላሉ።

ከላይ የተጠቀሱት ዋጋዎች አማካይ ግምት ወይም ከሦስተኛ አካል የተገኙ ናቸው። ዋጋዎቹ ግብር ያካቱት ቢሆንም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የዋጋ ልዩነት ሊኖር ይችላል።

ምንጭ፦ BBC|አማርኛ

One thought on “ወደ አሥመራ ለመጓዝ ምን ያስፈልጋል?

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡