“ነገር ሲሞትም ሲድንም የማያውቁት ደኢህዴኖች… ዛሬም እዛው ናቸው!” በዳንኤል ሺበሺ

በአርባምንጭ ከተማ ሰኞ ሐምሌ 2ቀን፡ 2010 ዓም ታላቅ የዴሞክራሲና የለውጥ ድጋፍ ሰልፍ ተደርጓል፡፡ በዚህ ጉዳይ ትላንት ቀንጨብ አድርጌ በፌስቡክ ገፄ ላይ አቅርቤ የተቀረውን በሌላ ግዜ በዝርዝር “እመለስበታለሁ” ብዬ ነበር።

ለሰልፉ ሲባል (1) ፦
የተደረገው አቀባበል፦ የአርባምንጭ ህዝብ ያደረገልኝ አቀባበል ድንቅ ነው፡፡ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርት መስከረም አበራ እንዳለችው “አርባ ፍቅር” በላይ ነበር፡፡ ያንን ብዙ የተባለለትን ስጋትና ፍርሃት (በዝርዝር ቀጥሎ በማነሳው ይሆናል) ጥሼ ወደ አርባምንጭ AirPort ስደርስ በቁጥር የበዛው ሕዝብና ተሽከርካሪ እየጠበቀኝ ነው፡፡ ከላንድንጉ ቀጥሎ የገብ መንገደኞች መግቢያ በማቋረጥ የፍተሻ ጣቢያውን አልፌ ወደ በረንዳ ክልል እንደደረስኩ ታላቅ ጩሄት፣ ፉጨትና ጭብጨባ ጠበቀኝ፡፡ ለስጦታ በተዘጋጀው ረጅሙና ቀጭን ጣውላ ላይ የተንጣለለው ልሙጡን የአባቶቻችን ባንድራ በክብር ተሰጠኝና ከሕዝቡ ጋር ጭፈራ ጀመርኩ፡፡ በአይሮፕላን ማረፊያ ከተቀበሉኝ ሕዝብ ጋር የተወሰነ ቆይታ ከተደረገ በኀላ ወደተዘጋጀልኝ መኪና ውስጥ እንዲገባ ተደረኩኝ፡፡ ከዚያም በብዙ ተሽከራካሪዎች በከተማው አውራ ጎዳናዎች መዞር ተጀመረ፡፡

ከአውሮፕላን ሲወርድ ለዳንኤል ሺበሺ የተደረገለት አቀባበል

ለሰልፉ ሲባል (2)፦
በከተማው ወጣቶች ጫና ምክንያት በዕለቱ ከተወሰኑ የጤናና ፀጥታ ተቋማት በስተቀር ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተዘግቷል፤ የግልና የሕዝብ የንግድ፣ የትምህርት ወዘተ ተቋማትና ድርጅቶች በራሳቸው በባለቤቶቹ ይሁንታ ተዘግተዋል፡፡ ሰልፉ ከተጠናቀቀ በኀላ ከሰዓት 8፡00 ገደማ ጀምሮ ከተማው ሪቺት ሆኗል፡፡ ነዋሪው በደስታና በጭፈራ ድብልቅልቁን ወጥቶ ነበር፡፡ ሁሉም በየአከባቢው በሰቀለው ልሙጡ ባንድራ ስር ቁጭ ብለው ፈታ ዘና ሲሉ ተመልክችያለሁ፡፡ ስለ ውሎው ይተረካል ይጨፈራል፤ የጋሞ፣ የጎፋ እና የአከባቢው ባሕል ሙዝቃዎች፤ የቴዲ እና የማድንጎ አፈወርቅ አልቤሞች የድሮ እና የአሁኑ ተራበተራ በቅርብና በርቀት ጆሮዬን ሰንጥቀው ያልፉታል፡፡
በአንዳርጋቸው ፅጌ ግጥም የተቀመመው “ላንቺ ነው ኢትዮጵያ” የሚለው ዘፈን መንደሩን አድምቋል፡፡ እኔም የአርባምንጭ ወጣቶቹ ባዘጋጁልኝ በከፊል ጠቁር መስተዋት መኪና ውስጥ ሆኜ ዋናውን አስፋልት እና የውስጥ ቅያስ መንገዶችን እየዞርኩ መቃኘት ጀመርኩ፡፡ ሼቻ፣ ሲቀላ፣ በቀለሞላ፣ ልማት፣ የትነበርሽ፣ ስቴዲየም፣ ኮንሶ ሰፈር፣ ዜሮ ሶስት፣ ውሃና ፍሳሽ፣ መናሃሪያ አከባቢ፣ እንደ ዮር-ዳኖስ ወንዝ ብቅ ጥልቅ እያልን የተራጨንባትን ኩልፎ ወንዝ ወዘተ እየዞርኩ መቃኘት ጀመርኩ፡፡ ያ! ያሳለፍኩት የህፃንነቴንና የወጣትነት ትዝታዬም ብቅ፤ ጭልጥ እያደረገኝ፡፡

አርባምንጭ በነበርኩበት ወቅት፣ ለፕ/ት መንግሥቱ ኃ/ማ አበባ ያሳቀፍንባትን፤ ከህወሓትና ከአሽከሮቹ ጋር አንገት-ለአንገት የተተናነቀንበትን ስፍራዎችን፤ ደንነቶች ክፉኛ ደብድቦኝ የወደኩበትን ሥፍራ እያስታወስኩ ፡፡ በአንድ ወቅት ወንድሜ ሀብታሙ አያለው እንዳለው “ደስታዬ በ7ኛው ሰማይ” ሆኖ ያ! ሁሉ ክፉና ደጉ ዘመን አልፎ ዛሬ ባሳደገኝ፣ ለወግ ማዕረግ ባበቃኝ፣ ባከበርኩትና ባከበረኝ ሕዝብ ፊት ላቆመኝ አምላክ ከነፍሴ የመነጨ ምስጋናዬን እያቀረብኩ ነገሮቹን መታዘብ ተያያዝኩ፡፡

ለሰልፉ ሲባል (3) ፦

ከ1,700 በላይ አንፀባራቂ ሽርጥ የለበሱና ያልለበሱ ሲቪል ወጣት የፀጥታ ኮሚቴ አባላት በአራቱም ከተማ መግቢያ ላይ ተሰማርቷል፡፡ ከዚያም አልፎ የስቴዲየሙ ዋናው መግቢያ በርም በእነርሱ ቁጥጥር ስር ነው፡፡ እኔ ካለሁበት መኪና ውጭ የማንም መኪና ወደ ውስጥ መግባት ክልክል ነበር፡፡ የፖሊስ መኮንኖች፤ የክልልና የዞን ባለሥልጣናት በወጣቶቹ ተፈትሸውና ትጥቅ ካላቸው ፈትተው ከአጥር ውጭ ባቆሙት መኪናቸው ላይ አስቀምጠው ነው ወደ ስቴዲየሙ ውስጥ የሚገቡት፤ አልፈታም አልፈተሽም የሚል ካለ ቀኝ ኀላ ዙር ይባላል! እሣት በላሱ ወጣቶች፡፡ “ለምን? እንዲህ ታደርጉታላችሁ?” ብዬ ጠይቂያቸው ነበር፡፡ “በአዲስ አበባ ከተማ ሰኔ 16/2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በተካሄደው ሰልፍ ላይ በዶ/ር አቢይ ላይ የተወረወረው ቦንብ የገባው በፖሊስ መኪና አይደለም እንዴ!?” በማለት ጥያቄዬን በጥያቄ መልሰውልኛል፡፡

በአርባምንጭ የተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ በከፊል

አዎን! እግዚአብሔርም በመለኮቱ ኃያል ነው! ሕዝብም በተቸረለት ሥልጣን ታላቅ ነው!

በሰልፉ ላይ የፀጥታ ችግር ሊኖር እንደምችል አስቀድሞ መረጃ ያገኘው ጓደኛዬና ethiothinkthank ድረ-ገፅ አዘጋጅ አቶ ስዩም ተሾመ ዕሁድ ሐምሌ 01 ቀን፡ 2010 ዓም ጧት ለእኔ በላከልኝ “Text message” ከባድ የፀጥታ ችግር እንዳለ በመጥቀስ የአርባምንጭ ጉዞውን መሰረዙን እንዲህ ሲል ነገረኝ፡-

“I boldly criticized the local officials, literally by their name, the security is extremely high and its beyond the control of our guys out there. Thus I cancelled my travel to Arbaminch. I am really Sorry…”

ከዚያ በኋላም በስልክም የነገረኝ ይህኑን የሚያረጋግጥ ነበር፡፡ የእኔ ቤተሰቦቼ፣ አንዳንድ ጓደኞቼና በኢህአዴግ ዙሪያ ያሉ ወዳጆቼ በተመሳሳይ ሁኔታ አስጠነቅቀውኝ ነበር፡፡ ብሰማቸውም ግን ማዳመጥ አቃተኝ፡፡ የትንሿ ኢትዮጵያ ሕዝብ እየጠበቀኝ ነው፡፡ እናም ወደ አርባምንጭ ጉዞዬን ደስ እያለኝ ቀጠልኩ፡፡

እውነቱን ለመናገር ከተወራው አንፃር የወሰንኩት ውሳኔዬ ትንሽ ከበድ ያለ ነበር፡፡ እኔ ብሞት እንኳ በአርባምንጭ ሕዝብ መሀል ነው፡፡ በትንሿዋ ኢትዮጵያ፡፡ ከፈጣሪ ቀጥሎ ያ! ጭቁን ህዝብ ጋሻ ይሆንልኛል የሚል ፅኑ እምነት ነበረኝ፡፡ “እመኑኝ!” ፈጣሪንና ሕዝብን የያዘ ምንም አይሆንም፡፡ ችግር ብገጥመን እንኳ 1000 ዓመት አንኖርምና ለህልናችን፣ ለሕዝብ ሁለንተናዊ ጥቅምና ለቆመንለት ዓለማ ኖሬን ማለፍ ክብር እንጂ … !!! በዕለቱም ሆነ አሁን ላይ ሆኜ ወደኀላ ሳስበው ውሳኔዬ ትክክል ነበር፡፡

ለሰልፉ ሲባል (4) ፦
ሰልፉ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ ያለፈው የከተማው ወጣቶች በሰልፉ ላይ የተሰጉ ውጥኖችን ቀድመው በመረዳት ስለተቆጣጠሩት ነው ወይስ?፤ የህወሓቶች ረጅሙ ጣት ሲላልነበረ ነው ወይስ?፤ የሕዝቡን ስሜት በደንብ አጥነውት በራሳቸው ጊዜ ውጥኑን ሰርዘውት ነው ወይ? የሚለውን ነጥቦችን ለጊዜው ልተውና ደኢህዴን’ም እንደ አቂሚቲ ሴራ ቢጤ ተለማምዳለች፤ “ከአህያ ጋር የዋለች ግደር …” የሚባለውን ብሂል ይዤ ልነሳ፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው ፦
ሰልፉ ከመካሄዱ በፊት፤ ለሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ሊኖር እንደሚችል ጠቅሶ ሰልፉ እንዳይካሄድ የጋሞጎፋ ዞን አስተዳደርና የዞኑ ፖሊስ መምሪያውገልጿቸው ነበር ፡፡ ለዚህም ማሳያው ህገወጥ ጦር መሣሪያ ሲዘዋወር ይዘናል የሚል ያረጀ የገረጀፈ የህወሓት ቋንቋ ተጠቅመው አስቀድመው አውጀዋል፡፡ ወሬውን አሰራጭተው ነበር፡፡ የእርስበርስ ግጭት ይነሳል ወዘተ በማለት ያስፈራሩትም ነበር፡፡ … በኀላም ለሰልፉ ሁለት ቀን እስቀረውና በተወሰነ መልኩ ከአስተባባሪዎቹ ጋር ከመግባባት ላይ እስኪደረስ ድረስ በአርባምንጭ ዙሪያ ያለው ሕዝብ በዕለቱ (ሰኞ ሐምሌ 2ቀን) ወደ ከተማ እንዳይመጡ እየዞሩ ያስጠነቀቁም ፤ ያስፈራሩም እንደነበረ በሰፊው ተወርቷል፡፡
እንዲህ አይነት ነገር በፊት በአርበኞች ግንቦት 7፤ በኦነግ እና በሌሎች በሽብር በፈረጇቸው ይላከክ ነበር፡፡ አሁን በማን ላይ? ድል ለትግል፤ ምስጋና ለፈጣሪ ይግባውና ጦር መሣሪያ ለዳር ድንበርና ለእርሻ ማረሻነት እንዲሆን ተወስኗልና፡፡ ታዲያ ለምን?

  • የመጀመሪያው ምክንያት፦ ዓላማውም ግልፅ ነበር፤ ሕዝቡ ፈርቶ ሰልፉን እንዳይወጣ ለማድረግ፡፡
  • ሁለተኛው ምክንያት የክልሉ፣ የዞኑና የደኢህዴን አመራሮች የበሰበሰ ጉዳቸውና ነውራቸው በሰልፉ እንዳይገለጥ ስለፈሩት ነው፡፡
  • ሶስተኛው እንደ ህወሓቶች ሁሉ ደኢህዴኖችም በአዲሱ ጠ/ሚ አካሄድ ብዙም ያልጣማቸው ነገር አሏቸው፡፡ ሰውዬው ህወሓትን እያፈረሰ/እያዳከመ ነው፤ እንዲህ ከሆነ ኢህአዴግ እና ደኢህዴንም ፈራሽ ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡
  • በመጨረሻም እኛም እንደ ግለሰብ ፈራሾች ነን የሚል ግንዛበ አላቸው፡፡ ይህም ደግሞ የእንጀራ ገመዳቸው ከፖለቲካው ጋር ለተያያዘ አካል በርግጥም ከባድ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡

ለሰልፉ ሲባል (5)፦ የሚዲያ ሽፋንን በተመለከተ

አዎን! ሰዎቹ ዛሬም እዛው ናቸው፡፡ ስለ ድጋፍ ሰልፉ በተለይ ኢቴቪ እና የደቡብ ቴሌቪዥን ሰፊ ሽፋን ለመስጠት ብዙም ፈቃደኛ አልነበሩም ፡፡ የተሰጠው ሽፋን ሕዝቡንና ትግሉን የሚመጥን አይደለም፡፡ በሰልፉ ሕዝቡ ያንፀባረቃቸውን መፈክሮችን፣ ጥያቄዎችንና ንግግሮችን ሳይሆን ገበናቸውን ለመሸፈን ነው ጥረት የተደረገው፡፡ በድረገፃቸው ማየት ይቻላል፡፡

ለዚህ እንደ የመጀመሪያ ምክንያት የምሰማኝ፦ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ እና ከአዲሳባ የተባረረውና እየተባረረ ያለው አፈና መዋቅሩ (ኃይል) በትግራይና በደቡብ የመሸገ ይመስለኛል፡፡ በጥቅሉ ደኢህዴንና ህወሓት እየተናበቡ እንደሚጫወቱ ነው የተረዳሁት፡፡ ፕሮግራሙን በቦታው ተገኝተው የቀረጹ የኢቴቪ ጋዜጠኞች ቢሆኑም አሁን ካለው ከክልሉ/ዞኑ አስተዳደር በኩል በልዩ ልዩ ተፅዕኖ የወደቁ ይመስለኛል፡፡ የአንዳንዶች ምክንያት ደሞ የተቀረጹበት ልማታዊ ጋዜጠኝነት ሰመመን እንዳልለቀቃቸው ከዚሁ መረዳት ይቻላል፡፡ ሌላውና ሁለተኛው ምክንያት የጋሞ ጎፋ ዞንና የደቡብ ክልል የቆሸሸ ድርጊታቸው ላለማጋለጥ ስለፈለጉ ነው የምል እምነት ነው ያለኝ፡፡ በዕለቱ ህዝቡ በአደባባይ ሲናገር የተሰማው “የአርባምንጭ ሕዝብ ጨዋ ነው፤ ባለጌን እንጂ የጨዋ አክባሪ ነው!” እያለ

በመጨረሻም የደኢህዴንና የጋሞጎፋ ዞን አገዛዝ ትላንት እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም አጠናክረው ቀጥለውበታል፡፡ ትላንት የኢሳትና የሌሎች ሚዲያ መቀባበያ ዲሾችን ከጣሪያ አውርዱ ብለው ሕዝቡን ቁም ስቅሉን ያሳዩን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ነዋሪዎች በየቤታቸውና በየበረንዳቸው የሰቀሉትን ባንድራ አውርዱ በማለት እያስፈራሩት ይገኛሉ፡፡ በሕዝቡን በይፋ እያሸበሩት ይገኛል፡፡ ባጠቃላይ ደኢህዴን ለለውጡ በግልፅ እንቅፋት እየሆነ ይገኛል፡፡ ስለሆነም የደኢህዴን ባለሥልጣናት በሙሉ ሳይዋረዱ በራሳቸው ፈቃድ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ እሠክራለሁ፡፡

በተረፈ የጋሞጎፋ ዞን ብሎም ደኢህዴን የተፈጠረውንና ሊፈጠር ያለውን አዝማሚያ አይተው በአንዳንድ ጉዳይ እንነጋገር ይላሉ ብዬ ጠብቂያቸው ነበር፡፡ ባለፈው ሣምንት ከአማራ ብ/ክልላዊ መንግሥት ጋር (የክልሉ ፕሬዚዳንትና ምክትላቸውን ጨምሮ አብዘኞቹ ካቢኔ አባላት በተገኙበት) በክልሉ አብረን መሥራት ሲለሚገባን ጉዳዮች ዙሪያ መክረን መመለሳችን ይታወቃል ፡፡

ከዚህ አይነት መቀራረብ የሚገኘውን ትርፍ ምን እንደሆነ ደኢህዴንም ልምድ ይቀስማል የምል ግምት ነበረኝ፡፡ ይሁን እንጂ ከመነጋገር ይልቅ ጥርስ እየነከሱብን ነው፡፡ አሁንም በትዕብታቸው እንደቀጠሉ ነው፡፡ በእነርሱ ዙሪያ ካሉትና ከሌሎች ወዳጆቼ የሚሰማው ነገር ጭራሽ ቀፋፊና ነውረኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ ዛሬም እዛው ስለመሆናቸው ሌላው ማረጋገጫ ነው፡፡ እኔንና በከተማው ውስጥ ያሉ የነፃነት ታጋይ ወጣቶችን ለማሰር፣ ማሳደድና ለመጉዳት እያሴሩ ነው፡፡ እነርሱን ያባረረውም፤ እኛንም የተቀበለው ያው ራሱ ሕዝቡ መሆኑን እንኳ የሚረዱበት አቅም አጥተዋል፡፡

እንግዲህ በዚህ ስሜት የሚቀጥሉ ከሆነ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደምችል አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ በእኔ በኩል ግን ነፍስ ይማር! በካፒታል ፊደል “RIP” ብያቸዋለሁ። ሀሳቤን ልቋጭ፡፡ ክቡር ጠ/ሚ አቢይ አህመድ በአንድ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ “አንዳንድ ፖለቲከኞች ሲሞቱም ሲድኑም አያውቁም” ያሉት ነገር ደኢህዴኖችን ነው የሚያስታውሰኝ፡፡ በእርግጥም “ሰዎቹ እዛው ናቸው” ሰላም!