የአንድ ብሔር የበላይነት መለኪያዎች: የተቋማት ሚና

ጥያቄዎች፡ ትግራይ/ሕወሀትና ኢትዮጵያ ሲመዘኑ!

(የዚህን ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ)

የአንድ ቡድን/ብሔር የበላይነት እንዴት ይፈጠራል? ቡድኑ እንዴትስ የበላይነቱን ያረጋግጣል? እዚህ ዉስጥ ማህበረሰቡ ወይም ግለሰቦች ሚና አላቸዉ? ኃይልን መጠቀምና ሰዎችን ማሸማቀቅ የተለመዱ የቡድን/የብሔር የበላይነት መፍጠሪያና ማቆያ ዘዴዎች ናቸዉ፡፡ በዋናነት ግን አንዱ ሌሎች ላይ የበላይነትን የሚጎናጸፈዉ ዘርፈ ብዙ አድሎአዊ (discrimination) ዘዴዎችን ስራ ላይ በማዋል ነዉ፡፡ በጥቅሉ ሶስት መሠረታዊ የማግለያ/አድሎአዊ ዘዴዎች ያሉ ሲሆን እነዚህም ስራ ላይ ሲዉሉ አንድም አድሎዉና የበላይነቱ ቡድናዊ/ብሔር ተኮር ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የቡድኑ/ብሔሩ ልሂቃን ብቻ ሳይሆኑ አባላቱም ተጠቂነትን በወል ይጋራሉ፡፡

በዚሁ መሔረት አንደኛዉ ዘዴ የመንግሥትና በሱ ተጽእኖ የሚያርፍባቸዉ ተቋማት ተልዕኮና አሠራር ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ በግለሰቦች ደረጃ የሚሰጡ ዉሳኔዎች ሆኖ ወሳኞቹ ተቋም ዉስጥም ሆነ ከተቋም ዉጪ የሚሰጡት ዉሳኔዎች በአድሎ የተሞሉና ከቡድኑ የበላይነት ጋር የተጣመሩ ሲሆን ነዉ፡፡ የመጨረሻዉ በሁለቱ ቡድኖች (የበላይና የበታች) መካከል ያለዉ የግንኙነት ሂደቶች ዉስጥ የሚፈጸሙ ተመጣጣኝ ያልሆኑ አድልኦዎች ናቸዉ፡፡ ስለሆነም የቡድን/የብሔር በላይነት ማለት ሶስቱ ድምር ዉጤት ነዉ፡፡ (ቡድን ማለት ብር ዘር ጾታ ና ሌሎችን ሲያመለክት በኢትየጵያ ሁኔታ በይበልጥ ብሔርን ይገልጻል)

1. ተቋማዊ አድሎበዚህ አተያይ ተቋማት ለሁለት ይከፈላሉ፡፡ እነሱም በቡድኖች መካከል ያለዉን የደረጃ ልዪነት የሚያጠናክሩ ተቋማት (Hierarchy-enhancing institutions, HEI) እና የደረጃ ልዪነት የሚያዳክሙ ተቋማት (hierarchy-attenuating institutions, HAI) ይባላሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ተቋማት HEI በቡድኖች መካከል ያለዉን መበላለጥ ማሳደግና ማቆየት ስራ የሚሰሩ ናቸዉ፡፡ ለስኬቱም ሲባል በዛ ያሉ አዎንታዊ ማህበራዊ እሴቶች (positive social values ) እና አነስ ያሉ አሉታዊ ማህበራዊ እሴቶች (negative social values ) ከዝቅተኛዉ ማኅበረሰብ ክፍል ይልቅ የበላይነትን ለተጎናጸፈ ቡድን በመስጠት ነዉ፡፡ በቀላል አባባል ከበታቾቹ ጋር ስናወዳድር መንግሥታዊ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎቶች ዉስጥ የበላይነት የተጎናጸፈ ቡድን/ብሄር የተሻለ ተጠቃሚና ያነሰ ተጎጂ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ የበላዮቹን ያማከለ ተቋማዊ አድልኦ ይደረጋል፡፡ ይሄኛዉ ብሔር በፖለቲካ ስልጣን፤ በሀብት፤ በደህንነት፣ በምግብ፣ በቤት አቅርቦት፤ በጤና፤ በትምህርትና በመሳሰሉት ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ የስርዓቱ አስፈጻሚ ከሆኑት ዉስጥ ትርፍን የሚጨምሩ የፋይናንስና ባንኪንግ ፣ ትላልቅ (ድንበር ዘለል) ኩባንያዎች፤ የገቢና ወጪ ንግዶች፣ የተፈጥሮና የመንግስት ሀብት፤ የገቢና ጉምሩክ፣ የፍትህና የወንጀል ስርዓትና፤ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ዋነኞቹ ናቸዉ፡፡ ተቋማቱ ለሴራዉ ስኬቱ ላንድ ወገን ያደላ ስርዓት በመዘርጋትና፤ መመሪያ፤ እቅድና ህግ በማዉጣት ሴራዉ ተቋማዊና ህጋዊነትን እንዲላበስ ያደርጋሉ፡፡

ለምሳሌ የፍትህና የወንጀል ስርዓቱ ዋነኛ የአንድ ብሄር የበላይነትና ቁጥጥር ማረጋገጫ ሚና አለዉ፡፡ ምክንያቱም ከበላዮቹ ጋር ስናወዳድር የተጋነነ ቁጥር ያላቸዉ የበታት ብሄሮች አባላት በእስር ቤቶች ፣ በማሰቃያ ማዕከላትና መግደያ ቀጠናዎች ዉስጥ ይወከላሉ፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት ተጨቋኞቹ ብሄር አባላት ከጨቋኞቹ ብሄር አባላት ጋር ስናነጻጽር በእጥፍ እጥፍ የሚታሰሩ ሲሆን በህይወት ዘመናቸዉ የመታሰር እድላቸዉም እንዲሁ የሰፋ ነዉ፡፡ ከነዚህ ዉስጥ የተወሰኑቱ ወንጀል ዉስጥ በመሳተፍ የሚታሰሩ ሲሆን ብዙሀኑ ግን በተቋማዊ አድሎ ወይም በማንነታቸዉ ብቻ የሚታሰሩ ናቸዉ፡፡

በኢትዮጵያ ዉስጥ በተመሳሳይ ምክንያቶች ቃሊቲ፣ ቂሊንጦ ማዕከላዊና ሌሎች ቦታዎች ሲያስሩና ሲታሰሩ የነበሩና ያሉትን በማስታወስ ሀሳቡን መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ኦሮሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ወይም ከደህንነት/ከመከላከያ ይልቅ በነዚህ እስር ቤቶች የተሻለ ዉክልና እንዲኖረዉ ሲደረግ ተጋሩዎች ባንጻሩ ከእስር ቤቶቹ ይልቅ በተጠቀሱት ተቋማት ሲወከሉ ቆይተዋል፡፡ ሌሎች ተጎጂዎችም ራሳችሁን እዚህ ዉስጥ መፈለግ ይችላሉ፡፡

በተጨማሪም የአድሎዉን ዉጤት ያየን እንደሆነ የበታቾቹ ማህበረሰብ አባላት ለበለጠ ስራ አጥነት የገቢ መቋረጥ የቤተሰብ መበተን የተአማኒነት ማጣት ና አጭር የእድሜ ጣሪያ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡
ሁለተኛዉ የደረጃ ልዪነት የሚያዳክሙ ተቋማት (hierarchy-attenuating institutions, HAI) በቡድኖች መካከል ያለዉን መበላለጥ ለማጥበብና ወደ መሀል ለማምጣት የሚሰሩ ናቸዉ፡፡ በተለይም የተጨቆኑት ቡድኖችን የሚረዳ ሲሆን በበላዮቹ ያልተያዙትን ሀብቶች እንዲያገኙም እድል ይከፍትላቸዋል፡፡ ከነዚህ ዋነኞቹ የሰብዓዊ መብቶች የሲቪል መብቶች የበጎ አድራጎትና የሀይማኖት ተቋማት ናቸዉ፡፡ ሆኖም ተቋማቱ በቂና ዘላቂ ፈንድና አቅም እንደዛዉም ህጋዊ ማስፈጸምና ሌሎች የሀይል መሰረቶች የላቸዉም፡፡ HAI ከ HEI የሚለየዉ አሉታዊ እሴቶችን ክጨቋኙ ቡድን ጋር የሚያስተሳስር አለመሆኑ ሲሆን ይሄንን ከፈጸመም ይዘጋል ወይም ህጋዊ ሰዉነቱን ያጣል፡፡ ይህ በHEI እና HAI መካከል ያለዉ የአቅም አለመመጣጠን በቡድኖች መካከል ያለዉ የበላይነትና የበታችነት ጸንቶ እንዲቆይ ያደርጋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ በተቋማት (Hierarchy-enhancing institutions, HEI) ዉስጥ የሚያደረጉ አድሎዎች ዋነኛዉ የቡድን/ብሔር የበላይነት ማረጋገጫ መሳሪያ ነወ፡፡ ለዚህም አምስት ምክንያቶች አሉ፦

  1. ተቋማት ከግለሰቦች የበለጠ ሀብት መመደብና ማንቀሳቀስ ስለሚችሉ፣
  2. ትላልቅ ተቋማት የተቀናጀ ተጽዕኖ ለማድረሰ የሚያስችል መዋቅር ስላላቸዉ ከላይ እስከ ታች ህዝቡ ጋር የመድረስ የተሻለ እድል ስላላቸዉ፣
  3. ተቋማት በዘላቂነት ራሳቸዉን ማቆየት የሚችሉ ስለሆኑ (ቋሚ በመሆናቸዉ) እነሱ የሚፈጽሙት አድሎ ትዉልድን የሚሻገር በመሆኑ፣ እንዲሁም ግለሰቦች/ቡድኖች ይሄን አሰራር ሲቃወሙ የተቋሙን ህልዉና ለመጠበቅ በሚል ሰበብ ተቋማት አድሏዊ አሰራሩን ከመጥፋት ስለሚታደጉት፣
  4. ተቋማት የዉስጥ ሰራተኞቻቸዉን የሚያቀናጅና ልዩነቶችን ወደ አንድነት የሚያመጣ የራሳቸዉን ባህል የሚመሰርቱ በመሆናቸዉና፣
  5. ተቋማት ልዩ የህግ ከለላ ስላላቸዉ ግለሰቦች በተቋሙ ተልዕኮ ስም (ለምሳሌ ወታደራዊ፣ ደህንነትና ካምፓኒዎች) ለሚያደርሱት ጥፋት ተጠያቂ ስለማይሆኑ ነዉ፡፡

ለማጠቃለል ያህል በሀገራችን ዉስጥ ለአመታት ሲደረግ የነበረዉን በዉል ካጤንን ይህ ጽንሰ ሀሳብ በሚገባ ይገልጸዋል፡፡ የነበረዉ ስርአት ዋነኛ ግቡ ሉሉንም ወይም ቁልፍ የመንግስት ተቋማትን በመጠቀም የአንድን ብሔር ተጠቃሚነትና የበላይነት ማረጋገጥ ነበር፡፡ በተለይም የአንድን ብሔር የበላይነት ለማረጋገጥ የሚረዱ የግለሰቦችና የቡድን ደህንነት ለማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ ንግድ ግብር ተፈተሮ ብትና ባንኪንግ ተጠቃሚነትን ለማስፈን፤ የዉጭ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ለመምራት፤ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ ዉሳኔ ሰጪነትን ለመምራት፤ የፍትህ ሥርዓትን ለራስ አላማ ለማዋል፣ ማኅበራዊ እሴቶች ላይ ተጽዕኖ ለማድረስ፣ ክልሎች አካባቢ ተሰሚነትን ለማጉላት የሚረዱ ተቋማትን በመፍጠር በመምራትና በመቆጣጠር እዉን ይደረጋል፡፡ የሀገራችንን እዉነታ የባሰ የሚያደርገዉ ጉዳይ ዉስጥ የደረጃ ልዪነት በማዳከም ለእኩልነት የቆሙትንና የተጨቆኑት ቡድኖችን የሚረዱ ተቋማትን- HAI-ጭምር መንግስት ጠምዝዞ ለራሱ አላማ ማሳኪያ ማድረጉ ንወ፡፡ በተለይም የሰብዓዊ/የሲቪከ መብቶችን የሚያስከብሩና የበጎ አድራጎት ስራ ላይ የተሰማሩትን በህግ ያዳከመ ሲሆን የሀይማኖት ተቋማት ዉስጥ ጣልቃ በመግባት ለአላማዉ አዉሏቸዋል፡፡ ለዚህ ጽሁፍ ማሳያ መጥቀስ ሳያስፈልግ እያንዳንዱ ሰዉ የነበረዉን ሁኔታ በማስታወስ እዉነቱም መረዳት ይችላል፡፡

…. ይቀጥላል

በቀጣዩ ክፍል “ግለሰባዊ አድሎን” በዝርዝር እንመለከታለን!

ለፀሃፊ ገመቺስ አስፋው በፌስቡክ ገፁ ሃሳብና አስተያየት መስጠት ይቻላል፡፡

One thought on “የአንድ ብሔር የበላይነት መለኪያዎች: የተቋማት ሚና

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡