የአንድ ብሔር የበላይነት መለኪያዎች: ክፍል 3፦ “ግለሰባዊ አድሎ”

(የዚህን ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ለማንበብ ይህን ሊንክ፣ ሁለተኛ ክፍል ለማንበብ ደግሞ ይህን ሊንክ ይጫኑ)

2. ግለሰባዊ አድሎ
አንድ በብሔር ወይም በሌላ የተደራጀ ጨቋኝ ስርአት ሲመዘን/ሲወቀስ ስርዓቱንና ግለሰቦችን መለየት የተለመደ ነዉ፡፡ ሆኖም ይሄ ጥናት እንደሚያመለክተዉ የጭቆና ስርዓት ጸንቶ መቆየት የሚችልበት ሁለተኛ ምክንያት በግለሰቦች በሚደረግ አድሎ ነዉ፡፡ ስርአቱ በተቋማት አድሎ ላይ ብቻ በመመስረት የጭቆና አገዛዝንም ሆነ የአንድ ቡድን የበላይነት መተግበርና ማቆየት አይቻለዉም፡፡ ስለሆነም የበላይነት ካለዉ ቡድን የሚወጡ ግለሰቦች ሚናም ለስርዓቱ መኖር ዋስትና ናቸዉ፡

ግለሰባዊ አድሎ የሚፈጠረዉ በስራ ቦታ በግል ተቋም በድርጅቶች ወይም በፖሊስ በአቃቤ ህግና ሌሎች ዉስጥ ባሉ ሰዎች ነዉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ቀጣሪ ሰንድን ሰራተኛ በብሔሩ ምክንያት ቅጥር ወይም እድገት ሲነፍገዉ፣ አንድ ቤት አከራይ ቤቱንም ሆነ ሱቁን በብሔሩ ምክንያት ለሌላዉ አላከራይም ሲል፣ አንድ ፖሊስ/አቃቤ ህግ አነስተኛ ወንጀል/ደንብ መተላለፍ ዉስጥ የተሳተፈን ሰዉ በብሔሩ ምክንያት ብቻ ሊከሰዉ ሲወስን፤ አንድ የስራ ሀላፊ ሌላዉን የትምህርት የጤና የፍቃድ ወዘተ አገልግሎቶችን በብሔሩ ምክንያት ብቻ ሲከለክለዉ፤ አንድ የቀበሌ ሀላፊ ሌላዉን በብሔሩ ምክንያት ብቻ መታወቂያና መሬት እንዳያገኝ ሲያደርገዉ፣ ወዘተ ነዉ፡፡

እዚህ ላይ ”በብሔሩ ምክንያት” ተብሎ የተገለጸዉ በዘር በጾታ በመደብና ደረጃም ሊሆን ቢችልም በኢትዮጵያ ነባራዊ እዉነታ ግን ብሔር ዋነጫ የጭቆናና ማግለያ መሳሪያ ነዉ፡፡ በዚህ ሰበብ ማን ያደላል ማንስ ይበደላል የሚለዉን በከፊል የሚወስነዉ የበላይነት ባገኘዉ የተዛባ ማህበራዊ እሳቤ ይዘት (contents of legitimizing myths) ነዉ፡፡ እነዚህ የተዛቡ ማህበራዊ እሳቤዎች ነባራዊ እሴቶች፤ ጠባዮች፤ እምነቶች፤ አመለካከቶችና ባህላዊ ርዮተ ዓለማትን ሲያጠቃልሉ መገለጫዎች ዉስጥ ከምርጥ ዘር መፈጠር፤ የታሪክ የበላይነት፤ ጦርነት ማሸነፍ፣ ዉርስ፤ የትግል አስተዋጽኦና፣ ስልጣኔይገኙበታል፡፡

ግለሰቦች ቁልፍ የዚህ አስተሳሰብ ተሸካሚዎች ሲሆኑ አስተሳሰቡን ወደ ስራ ሲቀይሩት የአድሎ ተዋናይ ከመሆን አልፈዉ የስርዓቱ መኖር ዋስትና ይሆናሉ፡፡ ስራ አጥነት ብሔር ተኮር በሚሆንበት ጊዜ ስራ እንዲቀጠር ምክር የሚሰጠዉ ሰዉ ከጨቋኞች ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ጉምሩክ ወይም አየር መንገድ አልያም ደህንነት ዉስጥ ለመቀጠር የምክር ሰጪ ግለሰቦች ሚና ትልቅ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ከ600 አዳዲስ ሰራተኞች ዉስጥ 400ዉ ከትግራይ እንዲሆኑ አይተ መለስ ዜናዊ ለወቅቱ የገቢዎችና ጉምሩክ ዳይሬክተር ምክር በመስጠት አስፈጽሟል፡፡

አይተ ጌታቸዉ አሰፋ ባንድ ወቅት ከ300 የአየር መንገድ ሰራተኞች 200ዎቹ ትግራዋይ እንዲሆኑ አስደርጓል፡፡ ግዜ በረዘመ ቁጥር እንደዚህ ያሉ ግለሰቦች ቁጥርም እየበዛ አድማሳቸዉም እየሰፋ ችግሩ ሀገራዊ ይሆናል፡፡ የዚህ ርዕስ ጭብጥም የሚሆነዉ ግለሰቦቹ የሚፈጽሙት የአድሎ ድርጊቶች ሲደመሩ በብሔሮች መካከል ያለዉ የበላይነትና የበታችነት ጸንቶ እንዲቆይ ያደርጋል፣ ስርዐቱም በነሱም ጭምር እየተነዳ ይቀጥላል ነዉ፡፡

ማህበራዊ መዋቅሩም ራሱ በግለሰቦች የሚፈጸሙ አድሎዎችን ያጠናክራል፡፡ ስለጣን ላይ ካለ/ከበላይ ብሄር የወጡ ግለሰቦች የራሳቸዉ ወገኖች (ስራ እዉቀት ሀብት ደንነትና ስልጣን ጨምሮ) የተሻሉ እሴቶችን ለሌሉች ደግሞ (እስር አሸባሪነት ድንነትን ጨምሮ)አሉታዊ እሴቶችን ይሰጣሉ፡፡ ሀብት ያላቸዉም እንዱኑ፡፡ ይሄ ሲባል ግን የሰዎች ድርጊት ባሉበት ማህበረሰብ/ቡድን ዉስጥ ባላቸዉ ደረጃ ይወሰናል ማለት አይደለም፡፡ ይልቅስ ተዋረዳዊ የማህበረሰብ ዉቅር (hierarchical structure) አለ ማለት ከእኩልነት ይልቅ መበላለጥን የሚያሰፉና የሚያጸኑ ድርጊቶች የተመቻቸ ስርዐት አለ ማለት ነዉ፡፡

ሆኖም ግን ከተመሳሳይ ብሔር የሚወጡ ግለሰቦች የድርጊቶቻቸዉና የዉሳኔዎቻቸዉ ጥግ (ማን የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚደረግ፣ የሚፈጸመዉ አድሎ እስከምን ድረስ እነደሆነ፣ ስለ ሌሎች ቡድኖች ያላቸዉ የጥላቻ መጠንና፣ አድሎአዊ ወይም የእኩልነት ፖሊሲዎችን እስከ ምን ጥግ ድረስ እንደሚደግፉ) ይለያያል፡፡ ልዩነቱ የሚመጣዉ ግለሰቦቹ ስለማህበራዊ መበላለጥ ባላቸዉ የስነልቦና ዝግጁነት (psychological orientation) ነዉ፡፡ ይሄም የማህበራዊ የበላይነት ዝግጁነት (social dominance orientation SDO) ተብሎ ይጠራል፡፡ የSDO ግለሰቦች ለቡድን የበላይነትና መበላለጥ ያላቸዉን የፍላጎት ልክ ያመለክታል፡፡ ፍላጎቱም የሚገለጸዉ አንድም ግለሰቡ በሚያደርጋቸዉ የአድሎ ድርጊቶች ሲሆን በተጨማሪም የበላዩ ቡድን የበለጠ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በሚል ግለሰቡ በህብረብሔራዊና ተቋማዊ ሂደቶች ዉስጥ ባለዉ ተሳትፎ ነዉ፡፡

…ይቀጥላል

በቀጣዩ ክፍል “በሁለቱ ቡድኖች” (የበላይና የበታች) መካከል ያለዉ የግንኙነት ሂደቶች ዉስጥ የሚፈጸሙ ተመጣጣኝ ያልሆኑ አድልኦዎች በዝርዝር እንመለከታለን!

ለፀሃፊ ገመቺስ አስፋው በፌስቡክ ገፁ ሃሳብና አስተያየት መስጠት ይቻላል፡፡