ለህወሓት “መደመር” ማለት ራስን-በራስ ማጥፋት ነው!

በሀገራችን እየታየ ያለውን ለውጥ ህወሓቶች ለምን እንደሚቃወሙት ለብዙዎቻችን ግልፅ አይደለም። አንዳንዶቻችን “ሁከትና ብጥብጥ ማስነሳቱን ትተው ምን አለ ከብዙሃኑ ጋር ቢደመሩ?” ብለን እናስባለን። ምክንያቱም ፍቅርና ይቅርታን የሚቃወም የፖለቲካ ቡድን መኖሩን ማሰብ በራሱ ከባድ ነው። ዶ/ር አብይ “መደመር” በማለት ያቀረቡት ጥሪ “የዜጎች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ዴሞክራሲያዊ ስርኣት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት እንተባበር” የሚል የአብሮነትና አንድነት ጥያቄ ነው። ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በአብሮነት መኖር የሚሻ የህብረተሰብ ክፍል የብዙሃኑን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አይቃወምም። በመሆኑም አሁን ላይ የህወሓት አመራሮችና ደጋፊ ልሂቃን የለውጡን እንቅስቃሴ የሚቃወሙበት ምክንያት ለብዙዎቻችን ግልፅ አይደለም።

በእርግጥ ቅንነት እና/ወይም ዕውቀት ያለው ሰው በሙሉ የብዙሃኑን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ እንዳለበት ያምናል። በዚህ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን አስተዋፅዖ በማበርከት “ይደመራል”። ነገር ግን፣ አብዛኞቹ የህወሓት አመራሮችና ደጋፊ ልሂቃን ከሞራል አንፃር ቅንነት የጎደላቸው፣ ከዕውቀት አንፃር ደግሞ በግንዛቤ ጥበትና ድርቀት የተጠቁ ናቸው።

የህወሓቶች መሰረታዊ ዓላማ የዜጎች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የትግራይን የበላይነት እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። አሁን በሀገራችን የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ አምርረው ከሚቃወሙት ውስጥ የቀድሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ሃላፊ ሜ/ር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልዳረጋይ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ይህ ግለሰብ ከወራት በፊት “ወራይና” ከተባለ መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ህወሓት የትግራይን ፖሊሲ የቀረጸው “የሰው አስተሳሰብን መሰረት አድርጎ ነው” እንደሆነ መግለፃቸው ይታወሳል።

እንደ ጄኔራሉ አገላለጽ፣ የትግራይ ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሲነጻጸር የራሱ የሆነ አንጸራዊ ብልጫ (comparative advantage) የሚያስገኙለት እሴቶች እንዳሉት ተናግረዋል። የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያኖች አንፃር ያለውን አንጻራዊ ብልጫ በአገር አመራር ደረጃ ሊጠቀምበት ይገባል። የትግራይ ወጣቶችም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በተለይም በዘመናዊ ቴክኖሎጂው ዘርፍ ተምረው አመራሩን መያዝ አለባቸው። ህወሓት ከሌለው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለዬ የትግራይ ተወላጆችን ብቻ በብዛት ወደ ውጭ ልኮ የሚያስተምረው በአገሪቱ አመራር ውስጥ አንጻራዊ ብልጫ (comparative advantage) ለማግኘት መሆኑን ጄኔራሉ መናገራቸው ይታወሳል።

በዚህ መልኩ የትግራይን የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ቡድን በፍፁም የሌሎችን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መቀበል አይችልም። ምክንያቱም የብዙሃኑ እኩልነት ሲረጋገጥ የጥቂቶች የበላይነት ያበቃል። በተመሳሳይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከተረጋገጠ የጥቂቶች ኢ-ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያበቃል። ስለዚህ የሁሉንም እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ጥረት የአንድ ወገን የበላይነትና ኢ-ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያስቀራል። በመሆኑም የለውጡን እንቅስቃሴ ተቀብሎ መደገፍ ህወሓቶችን የቆሙለትን መሰረታዊ ዓላማ እንዲስቱ ያደርጋቸዋል።

መሰረታዊ ዓላማውን የሳተ ነገር ፋይዳ-ቢስ ነው። ህወሓትም የተጀመረውን ለውጥ ከደገፉ ከፖለቲካ አንፃር ፋይዳ-ቢስ ይሆናሉ። የለውጡን እንቅስቃሴ ተቀብሎ መደገፍ ለህወሓት ራስን በራስ እንደ ማጥፋት ነው። ማንም ቢሆን አውቆና ፈቅዶ ራሱን በራሱ አያጠፋም። ህወሓትም በምንም ተዓምር አውቆና ፈቅዶ ለውጡን ተቀብሎ ሊደግፍ አይችልም። ህወሓት በፖለቲካው ውስጥ ህልውና እስካለው ድረስ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ይቃወማል። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የለውጡን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ያሴራል፥ ይሰራል። በአጠቃላይ ለህወሓቶች “መደመር” ማለት ራስን-በራስ ማጥፋት ነው።

One thought on “ለህወሓት “መደመር” ማለት ራስን-በራስ ማጥፋት ነው!

  1. ህወሓት TPLF Manifesto በሚባለው በገማ የጠባቦች ገንዳ ውስጥ ከመጨማለቅ ሌላ ምንም እውነታ የሚፈጥር የአእምሮ ችሎታ የለውም። ስለዚህም ማጥፋት እንጅ ማልማትና መደመር በህውሓት DNA ውስጥ አልተመሠረቱም።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡