ጠቅላይ ሚንስትሩ ለፀጥታ ሀይሎች የሰጡት ትዕዛዝ ጥንቃቄ ያሻዋል ተባለ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ላይ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎችን ለህግ እንዲያቀርቡ ለፀጥታ ሀይሎች ያስተላለፉት ትዕዛዝ ተገቢ ነዉ ሲሉ አንዳንድ ሙህራን ገለፁ።

ይሁን እንጅ የተላለፈዉ ትዕዛዝ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ በአፈፃጸሙ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ሙህራኑ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ያለፈዉ ቅዳሜ ከኤርትራዉ ፕሬዝዳንት ጋር በሀዋሳ ጉብኝት አድርገዉ ነበር። ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ ጉብኝት ወቅት ባሰሙት ንግግር በሀገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች በተከሰቱ ግጭቶች ላይ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች የሰላምና የፍቅር ዋጋ እንዲገነዘቡ አሳስበዋል።እነዚህ አካላት ይህንን የማይገነዘቡ ከሆነ ግን መንግስት ወደ ሌላ ርምጃ ለሚሸጋገር የሚገደድ መሆኑንም ማስጠንቀቃቸዉ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በዛሬዉ ዕለት ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሽኝት በኋላ ባደረጉት ንግግር ደግሞ በየትኛዉም የሀገሪቱ ክፍል ህዝብን ከህዝብ ጋር በሚያጋጩ ድርጊቶች ላይ የሚሳተፉ ወገኖችን በመረጃ ላይ ተመስርተዉ ወደ ህግ እንዲያቀርቡ ለፀጥታ አካላት ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

«የሀገር መከላከያ ሰራዊት መከላከያ ሚንስቴር እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ ከዚህ ስዓት ጀምሮ በየትኛዉም ቀጠና ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጩ የሰዉ ህይወትን ከሚያጠፉና ከሚያስጠፉ ድርጊት ዉስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች ህግ ፊት እንድታቀርቡ ።መሃል ገብታችሁም እያጋጠመ ያለዉን ችግር ረገብ እንዲል ሀገራዊ እና ህገመንግስታዊ ሀላፊነታችሁን እንድትወጡ» ካሉ በኋላ የጸጥታ ሀይሎች የሚሰሩትን ስራ ሙያዊና በመረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አሳስበዋል።

ፀጥ ያለ አብዮት

ጉዳዩን በተመለከተ ዶቼ ቩሌ ያነጋገራቸዉ ጦማሪና መምህር አቶ ስዩም ተሾመ እንደሚሉት ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረቡ ሂደት በጥንቃቄ መያዝ አለበት።በግላቸዉ በሀገሪቱ «ፀጥ ያለ አብዮት» ተካሂዷል ብለዉ እንደሚያምኑ የገለፁት አቶ ስዩም በእንደዚህ አይነትቱ ሂደት ለዉጡን ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን ለመመመከት መንግስት የሚወስደዉ ርምጃ ሀይል ያልተቀላቀለበትና የሰከነ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል። ያካልሆነ ግን ሀገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫና ወደ ብጥብጥ ሊወስድ ይችላል ሲሉ ስጋታቸዉን ገልጸዋል።
ያማለት ግን ወንጀለኞችን ለህግ ሳያቀርቡ በቸልተኝነት ይታለፉ ማለት እንዳልሆነ አቶ ስዩም አስረግጠዉ ይናገራሉ።

«በእርግጥ ወንጀል የሰራ ሰዉ እስካለ ድረስ በዜጎች ህይወትና ንብረት ጉዳት ያደረሰ ሰዉ እስካለ ድረስ በህግ መጠየቅ አለበት።በዚህ ነገር ምንም አይነት ቸልተንነት፤ መለሳለስና ይቅርታም አያስፈልግም። በሰዉ ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ ሰዉ ተይዞ ለፍርድ መቅረብ አለበት። ይህን ሳናደርግ መቅረታችን በራሱ ነገሩን ያባብሰዋል።» ነዉ ያሉት። ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሌላቸዉን ሰዎች እንዳይጎዳ የሚወሰደዉ ርምጃ በጥናት ላይ የተመስረት እንዲሆን ነዉ ያሳሰቡት።

የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ዳንኤል መኮንን በበኩላቸዉ የጠቅላይ ሚንስትሩ ርምጃ ተገቢ ቢሆንም እስካሁን በየቦታዉ ከታዩት ግጭቶች አንፃር ዘግይቷል ባይ ናቸዉ። በአፈፃጸም ላይም ጥንቃቄ ካልታከለበት መመሪያዉ ወደ ታች ሲወርድ የህዝብን ጥያቄ ለማፈን ሊዉል ይችላል የሚል ስጋትም አላቸዉ።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ጦማሪ ዳንኤል መኮንን

«አሁንም ብዙ ነገሮች አሉ ።በየአካባቢዉ ያሉ የአመራር አካላት ኮራፕት ሊያደርጉት ይችላሉ።ምክንያቱም ዶክተሩ አይደሉም ርምጃዉን የሚወስዱት።»ይሉና

መመሪያዉን በሚያስፈፀሙ በየደረጃዉ ባሉ የፀጥታ አካላት ሊመጣ ይችላል ያሉትን ስጋት ያብራራሉ።«በየወረዳዉ በየዞኑ ያሉ ጥያቄ የበዛባቸዉ የአመራሮች «ኮራፕት»ሊያደርጉትና ጥያቄ እየጠየቁ ያሉ ሰዎችን ለመምታት ሊያገለግል ይችላል። ልክ በደርግ ጊዜ እንደተደረገዉ።ነገር ግን በጥንቃቄ የሚሰራበት ከሆነ ነገሩ ዘግይቷል እንጅ አልፈጠነም።» ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከሰቱ ግጭቶች በሶማሌ ፤በኦሮሚያ፤ በቤንሻንጉልና በደቡብ ክልሎች ከ አንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ሲሆን በርካቶች ለአካል ጉዳትና ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸዉን መረጃዎች ያሳያሉ።ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን ትዕዛዝ ባስተላለፉበት በአሁኑ ወቅትም በደቡብ ክልል ብቻ ከ 8መቶ ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በቂ መጠለያ፣ ምግብ ፤ዉሃና የንፅህና አግልግሎት እንደማያገኙ የተባባሩት መንግስታት ዘገባ አመልክቷል።

ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ

ምንጨ፦