አዲሱ ከንቲባ እና ጠ/ሚኒስትሩ: ፍሬውን ትቶ ገለባውን!

ያሬድ ሃ/ማሪያም (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የወያኔ ምክር ቤት የመረጣቸውን የኢህአዴግ ሊቀመንበር የዶ/ር አብይን ወደ ሥልጣን መምጣት ከመደገፍም ታልፎ ምስላቸውን በየደረት ላይ ለጥፈው እየዞሩ እሳቸው የመረጡትን “የአዲስ አበባ ከንቲባ ሕዝብ ያልመረጠው ነው” እያሉ ማልቀስ አይገባኝም። እውነቱን መነጋገር ካለብን እንኳን ተሿሚውን ሿሚውንም ሕዝብ አልመረጠም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ገና በመረጣቸው ሰዎች ለመተዳደር አልታደለም። ዛሬም እየተዳደረ ያለው ሳይመርጣቸው ነገር ግን በደገፋቸው ሰዎች ነው። የመረጡትን ሰው መደገፍ እና ድንገት መጥቶ አናት ላይ ቂብ ያለን ሰው መደገፍ ይለያያል። የመረጥነው ሰው ሲሆን ሃሳቡን፣ ፖሊሲውን እና አመለካከቱን አይተንና መዝነን፣ ከሌሎች ጋር አወዳድረን “አንተ ትሻለናለህ” ብለን ነው። ስለዚህ ያ ሰው ሥልጣን ሲይዝ ምን እንደሚያደርግ ቀድመን እናውቃለን። ምርጫውም ቃል ኪዳን ነው።


ከግራ ወደ ቀኝ፦ የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ እና ጠ/ሚ አብይ አህመድ

እኛ የመምረጥ እድል ሳይኖረን እና አቅሙን አጥተን በፍትጊያ ውስጥ የመጣን ሰው መደገፍ ግን የተለየ ነው። ያሰው አናታችን ላይ ቂብ ካለብን በኋላ ነው ማንነቱ እየተገለጸልን፣ የሚናገራቸውንና የሚሰራቸውን ነገሮች እያየን የምንደግፈው ወይም የምንቃወመው። ለዚህም ነው ዶ/ር አብይ በእለት ከዕለት ክስተቶች እያስደመሙን አንዳንዴም እያናደዱን በየቀኑ በሰበር ዜና ያጠመዱን። ዶ/ር አብይ ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን አድርገውልናል፤

 • 1. አገሪቱ ላይ አንጃቦ የነበረውን አደጋ በመቀልበስ በተቃውሞ ስትናጥ የቆየችውን አገር በተወሰነ ደረጃ በማረጋጋት ሕዝባዊው ተቃውሞ ወደ ሕዝባዊ ድጋፍ እንዲቀየር አድርገዋል።
 • 2. አገሪቱን ቀፍድዶ የያዘውን የአገዛዝ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ባያስወግዱትም አቅሙ እንዲዳከም እና እጁን ጠምዝዘው ለውጡን እንዲቀበል አድርገዋል። ሥርዓቱ በጠላትነት የፈረጃቸው ሰዎችና ፓርቲዎች ሳይቀሩ የፖለቲካ ሂደቱ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ተደርጓል።

የተፈጠረውን እድል እና ክፍተት በመጠቀም መሰረታዊ ወደሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ ለመግባት የሚያስችል የትግል እስትራቴጂ መንደፍ ከለውጥ ፈላጊው ኃይል ይጠበቃል። ይህን አንኳር ነገር ወደ ጎን ትቶ በየመንደሩ የሚሾሙ ካድሬዎችን የጎሳ ማንነት እያነሳን በዛው በዘር አዙሪት ውስጥ አብረን የምንሽከረከር ከሆነ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልጋቸውን አገልጋዮቹን በነጻ እና ዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚመርጥበት የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር ብንታገል ይሻላል።

እርግጥ ነው ዶ/ር አብይ እና ቡድናቸው ለሌላ 27 አመት አገሪቷን እንዲያስተዳድሩ የሚመኝ እና የሚፈልግ ሰው ካለ ካለ በዛሬዎቹ የመንደር ተሿሚዎች ማንነት ላይም ሆነ በሌሎች ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ አትኩሮት ሰጥቶ መከታተል እና መነታረኩም ሊያዋጣው ይችላል። ካለዚያ ግን በቀጣዩ ምርጫዎች ሌሎች ጠንካራ እና ተፎካካሪ ኃይሎች እንዲወጡ እና የምንመኘው ለውጥም እንዲመጣ ከፈለግን አገሪቱ የዴሞክራሲያዊ መንገድ እንድትከተል የሚያስችሉ ሁኔታዎች ከወዲሁ እንዲፈጠሩ እና ተቋማዊ ቅርጽ እንዲይዙ የሚከተሉት አንኳር ጉዳዮች ላይ ብናተኩር ይበጃል ባይ ነኝ።

 • 1. ባፋጣኝ ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት እና ሌሎች ባለድርሻዎች የሚሳተፉበት ብሔራዊ እና ሁሉ አቀፍ የምክክር ጉባዔ እንዲካሄድ፣
 • 2. የምክክር ጉባኤው የአገሪቱን ፍኖተ ዲሞክራሲ ሰነድ እንዲያረቅ፣ እንዲወያይበት እና አጽድቆ እንዲያወጣ ቢደረግ፣
 • 3. በብሔራዊው ጉባኤ የተሰየመ አንድ ቡድን የምርጫ ቦርድ አወቃቀርን፣ የምርጫ ሕጉን እና የድምጽ አሰጣጥ ሂደቶቹ የሚሻሻሉበትን ንድፈ ሃሳብ እንዲያቀርብ ቢደረግ፣
 • 4. የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከወዲሁ ሃሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ እና በቂ የበጀት ድጋፍ እንዲያገኙ የሚደረግበት ሁኔታ እንዲፈጠር ቢደረግ፣
 • 5. ባለፉት 27 አመታት እና አሁንም ድረስ በአገሪቱ በርካታ ሥፍራዎች ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ስለሆነ እነዚህን ጥሰቶች የሚምመረምር፣ በጥሰቶቹ ተሳታፊ የሆኑ የመንግስት ኃላፊዎችን ማንነት በበቂ ማስረጃ አንጥሮ የሚያወጣ፣ ተጎጂዎች የሚካሱበትን እና ሌሎች መወሰድ የሚገባቸውን እርምጃዎች ሊጠቁም የሚችል አንድ ገለልተኛ የባለሙያዎች አጣሪ ቡድን እንዲቋቋም ቢደረግ፣

ባጭሩ ትኩረታችን እዚም እዛም በሚጣሉ አዳዲስ አጀንዳዎች ላይ ከሚሆን ዘላቂ እና አገራዊ ለውጥን ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ቢሆን መልካም ነው። ለጊዜው ማንም ተሾመ ማንም አዲስ አበባ እንደሆነ የምትተዳደረው በኢህአዴግ/ወያኔ ፖሊሲ ነው። ሕዝብ ተወያይቶ ያላጸደቀውን ፖሊሲ ለማጽፈጸም ማን ጥሩ ካድሬ ነው፣ ከየትኛው ዘር ቢሆን ይሻላል የሚለው ክርክር ሚዛን ባይደፋም ጸብ ያለሽ በዳቦ ይመስላል።

ቸር እንሰንብት!


ምንጭ፦ የአቶ ያሬድ ሃይለማሪያም ፌስቡክ ገፅ

3 thoughts on “አዲሱ ከንቲባ እና ጠ/ሚኒስትሩ: ፍሬውን ትቶ ገለባውን!

 1. አመሰግናለሁ

  On Thu, Jul 19, 2018, 1:44 PM Ethiopian Think Thank Group, wrote:

  > Seyoum Teshome posted: “በያሬድ ሃ/ማሪያም (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች) የወያኔ ምክር ቤት የመረጣቸውን
  > የኢህአዴግ ሊቀመንበር የዶ/ር አብይን ወደ ሥልጣን መምጣት ከመደገፍም ታልፎ ምስላቸውን በየደረት ላይ ለጥፈው እየዞሩ
  > እሳቸው የመረጡትን “የአዲስ አበባ ከንቲባ ሕዝብ ያልመረጠው ነው” እያሉ ማልቀስ አይገባኝም። እውነቱን መነጋገር ካለብን
  > እንኳን ተሿሚውን ሿሚውንም ሕዝብ አልመረጠም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ገና በመረጣቸው ሰዎች ለ”
  >

  Like

 2. ስዩም እውነት ላይ ተተርሰህ ለምታቀርባቸው ትንታኔዎች አመሠግንሀለሁ፡፡እኔንም የገረመኝ ይኼ ሁሉ ጫጫታ ስለ አንድ ኦሮሞ ከንቲባ ሹመት መሆኑ ነው፡፡ እስከ ዛሬስ የይስሙላ ቢሆን ወያኔ ከንቲባ እያለ ሲያሰቀምጥ የነበረው ከኦሮሞ አልነበረም ወይ? ፡፡ የስርአት ለውጥ እኮገና አልመጣም፡፡ እስከተወሰነ ጊዜ አንዳንድ ነገሮች ባሉበት እንዲቀጥሉ የሚያስገድዱ ነገሮች ያሉት ይመስለኛል፡ እነዚህ ነገሮች ጊዜአዊ እንጂ ዘላቂ አካሔድ ግን አይመስሉኝም፡፡ በአንድ ጀምበር የሚያልቅ ነገር የለም፡፡ጥቃቅን ነገር ይዘን ከምንጫጫ የጋራ ጠላታችን ላይ እናተኩር፡፡ 27 ዓመት የተገመደ ትብታብ በቀናት እንዲስተካከል መጠበቅ በፍፁም አግባብነት የለውም፡፡
  የጠላት መሰሪ ፕሮፓጋንዳ የገደል ማሚቶ አንሁን፡፡የምናራግበው ነገር ጥቅሙንና ጉዳቱን እያየን ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ካመነውና ከደገፍነው ገዜ ብንስጠውና ብንመዝነው እንጂ ስር ስሩ እየተከተልን ጥቃቅኗን ነገር አቃቂር እያወጣን በመጯጯህ አናውከው ፡፡ የሚወስዳቸው ድርጊቶች የየራሳቸው ምክንያቶች ይኖሩታል ብየ አስባለሁ፡፡ በአንድ በኩል የውስጥ ፍትጊያና ጦርነት አላበቃም፡፡አረረም መረረም ጠ/ሚሩ አምርረን ከምንጠላውና ከምንቃወመው ወያኔ ጋር እየሠራ ነው፡፡እነዚህ ሰዎች ገዝጓዝ እያነጠፉለት አይደለም፡፡ባደባባይ ላይ እስከማስወገድ ሙከራ ድረስ ሔደዋል፡፡ ሲጀመር እስከዛሬ ድረስ እንዳየነው ኢትዮጵያዊነትንና እኩልነትን የሚሰብክ እንጂ ዘርን የመያቀነቅን ሰው አይደለም፡፡ ሁሉን እንቅስቃሴ በዘር ስሌት አየመዘንን አካኪ ዘራፍ የምንል ከሆነ እራሳችንን እንፈትሽ፡፡ አሁን እጅ ለእጅ ተያይዘን በመደጋገፍ ለሁላችን እኩል የምትሆን ሀገር ለመገንባት እንሰለፍ፡፡ ለልዩነት በር አንክፈት

  Like

 3. ውድ ወንድሜ ያሬድ
  አዎ ዶክተር አብይን በደረታችን ለጥፈናል፣በሙሉ ድምፅ ተቀብለናል፣ በልባችን አኑረናል፣ ሙሴ ብለናቸዋል እና ተደምረናል!! ለምን? ዶር አብይ እንደ ንስር እሻግረው የሚያዩና (ዘር አላልኩም ) አገር ወዳድ ስለሆኑ ነው። ከየት መጡ ችግራችን አይደለም ምን ሰሩ እንጂ። በሌላ በኩል አዲሱን ለምን ተቃወምን? ከ2011 ጀምሮ በማህበራዊ ድህረ ገብ ያቀነቅኑት የነበረን ሃሳብ ይመለከትታል።
  እኔን በተመለከተ ስውየው ከተሾሙ በኋላ የፃፏቸውን መልእክቶች አይቻለሁ። ጥሩ ናቸው።
  እኔ Let’s give him the benefit of the doubt እልምለሁ። ወደፊጥ ጥሩ ሲሰራ እናመሰግነዋለን። ሲያጠፋ ደግሞ እንደ ኢትዮጵይያዊ ይወቀሳል። አለቀ!

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡