የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መምሪያ ሃላፊን ጨምሮ በሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታ የተጠረጠሩ 8 ተከሳሾች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠየቀ

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መምሪያ ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌን ጨምሮ በሰኔ 16ቱ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከተፈጠረው የቦንብ ፍንዳታ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 8 ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተሰጠ።

በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮን በሚመለከተው አንደኛ የወንጀል ችሎት የተገኙ ተጠርጣሪዎች በየመዝገባቸው ጉዳያቸው ታይቷል።

ችሎቱ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በተዘጋጀው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከተፈጠረው የቦንብ ፍንዳታ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የተጠረጠሩ አምስት ተጠርጣሪዎች ምርመራን የተመለከተ ሲሆን፥ በአዕምሮ ህክምና ላይ የምትገኘው ህይዎት ገዳን ጨምሮ አምስቱ ተጠርጣሪዎች ላይ መርማሪ ፖሊስ የሰራቸውን እና ቀሩኝ ያላቸውን ስራዎች ገልጿል።

በተለይም ከመከላከያ፣ ከኤፍ ቢ አይ የምርመራ አባላት፣ በእንግሊዝኛ የተጻፉ እና አማርኛ ትርጉም የሚያስፈልጋቸው ማስረጃዎችን ለማስተርጎም፥ ስለፍንዳታው እንዲያስረዳ ከፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ ዝውውርን የሚመለከት ውጤት እንዲሁም የምስክር ቃል መቀበልና በቦንቡ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የጉዳት መጠን የሚገልጽ የህክምና ማስረጃ ምላሽ ለመቀበል 14 ተጨማሪ ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ በመቃወም ዋስትና ሊሰጣቸው እንደሚገባ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

በእስር ቤት ቆይታችን ሰብዓዊ መብታችን ይከበር ሲሉም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል፤ መርማሪ ፖሊስም ዋስትናውን ተቃውሟል፤ ችሎቱ ሰባት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን ለፖሊስ ፈቅዷል።

የተጠርጣሪ ህይወት ገዳ የጤና ሁኔታን የሚገልጽ የህክምና ውጤት ፖሊስ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብ እና የተጠርጣሪዎች የሰብዓዊ መብት እንዲከበርም ችሎቱ አዟል።

በሌላ መዝገብ የቀረበውና ከሶስት ወር በፊት በይቅርታ የተፈታው በየነ ቡላ የተባለ ተጠርጣሪ የቦንብ ፍንዳታውን ሲያስተባብር እንደነበረ ማስረጃ ማግኘቱን ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪው በይቅርታ የተለቀቀ እና በወቅቱ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ሳይኖረው ፍቼ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ መያዙን በመጥቀስ፥ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የለኝም በማለት ዋስትና እንዲፈቀድለት ጠይቋል፤ ግብረ አበሩ ነው የተባለው ግለሰብም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቧል።

መርማሪ ፖሊስም ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ያልተያዙ ግብረ አበሮቻቸውን ሊያሸሹና ማስረጃ ሊያጠፉ ይችላሉ ሲል ዋስትናውን ተቃውሟል።

ችሎቱም ፖሊስ ቀረኝ ያለውን ምርመራ እንዲያከናውን የ12 ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።

መርማሪ ፖሊስ በቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መምሪያ ሃላፊ በነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ፥ የምስክርና የተጠርጣሪን ቃል የመቀበል ስራ ማከናወኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ያሉኝን ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅና ለቦንቡ ፍንዳታ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ፥ ተጨማሪ 14 ቀን ይፈቀድልኝ ሲልም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪው አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በበኩላቸው ስራቸው የመምሪያ ሃላፊና ህግ ማስከበር መሆኑን በመጥቀስ፥ ለ20 አመት በሰሩት ስራ እንጅ በተባለው ጉዳይ ልጠየቅ አይገባም ብለዋል።

ከድርጊቱ ጋር ግንኙነት የለኝም ለምን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉኝም አላውቅም፤ ዋስትናም ሊፈቀድልኝ ይገባል ሲሉም ለፍርድ ቤቱ አብራርተዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪው የቦንቡን ፍንዳታ ከፈጸመው ቡድን ጋር ግንኙነት በመፍጠር ድርጊቱ እንዲፈጸም ያደረጉ በመሆናቸው እና ከፍተኛ ባለስልጣን በመሆናቸው ማስረጃ ሊያጠፉብን ይችላሉ በማለት ዋስትናውን በመቃወም አስረድቷል።

ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪን ዋስትና በማለፍ ለመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርግ የ12 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዛሬው የችሎት ውሎ በዕለቱ ከተከሰተው የቦንብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ የስራ ከፍተት አሳይተዋል ተብለው የተጠረጠሩት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳን ጨምሮ 10 የኮሚሽኑ አባላት ላይ መርማሪ ፖሊስ የሰራቸውን ስራዎች ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

በዚህም ያልተሰሩ ማለትም ያልተያዙ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን የመያዝ፣ የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሰነድ አጠናቆ ለሚመለከተው አካል የማስረከብ ስራን ለማከናወን ተጨማሪ 10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው በጠበቆቻቸው አማካኝነት በተጠረጠርንበት የስራ ክፍተት ምንም ማስረጃ ባልተገኘበትና በቃል ማስጠንቀቂያ ብቻ በሚታለፍ አስተዳደራዊ አሰራር ከአንድ ወር በላይ ታስረን ልንቀጣ አይገባም በማለት የዋስትና መብት ሊከለከሉ እንደማይገባም አስታውሰዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪዎቹ ከታችኛው እርከን እስከ ከፍተኛ ደረጃ ባለ ሀላፊነት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው የምስክርን ሀሳብ እና ማስረጃ ሊያስለውጡ ይችላሉ ሲል የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሞታል።

ጠበቆችም ደንበኞቻችን ፓስፖርት እንኳን የሌላቸውና አነስተኛ ደመወዝ የሚያገኙ ህዝብ አገልጋይ እንደመሆናቸው ምንም አይነት ማስረጃ ሊያስቀይሩ አይችሉም ስለዚህ ዋስትናው ሊፈቀድ ይገባል ፍርድ ቤቱም ይህን መብት ሊያስከብር ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎችን ዋስትና ጥያቄ በማለፍ መርማሪ ፖሊስ ለመጨረሻ ጊዜ በአራት ቀን የጊዜ ቀጠሮ የምርመራው ስራውን አጠናቆ እንዲያቀርብ አዟል።

በታሪክ አዱኛ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 20 ፣ 2010

ምንጭ፦ ኤፍ ቢ ሲ (FBC)

One thought on “የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መምሪያ ሃላፊን ጨምሮ በሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታ የተጠረጠሩ 8 ተከሳሾች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠየቀ

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡