ሥርዓት አልበኝነት በመከላከል የለውጡ ተስፋ እንዳይቀለበስ ሁላችንም ዘብ ልንቆም ይገባል!!

[ ..የሚመለከተው የመንግስት አካል አስቸኳይ ምርመራ አድረጎ ከግድያው በስተጀርባ ያለውን አሻጥር ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አለበት..]

በይድነቃቸው ከበደ

በአገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት ወራት የታየው የለውጥ ጅማሮ የሚበረታታ እና ይበል የሚያስብል ከመሆኑም ባሻገር በዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ኃይል እና ሕዝብ በከፍተኛ ፍላጎት እና ትልቅ ተስፋ በመሰነቅ ለአገራዊ መግባባትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሁሉም በየፊናው የበኩሉን በጎ አስተዋጽኦ እየተወጣ ይገኛል ፡፡ አሁን ላይ ለታየው የለውጥ ተስፋና እሱን ተከትሎ ለሚታየው አንጻራዊ ሰላም እና ዴሞክራሲ አብዛኛው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ታላቅ መሰዋዕትነት በመክፈል ያገኘው እና ታሪክ ሁሌም የሚዘክረው የዜጎች ድል ጭምር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ባሰለፉት 27 ዓመታት የተጫነበትን የአገዛዝ ቀንበር ከትከሻው በማንሣት፤ በመስዋዕትነቱ ያመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል እና በይበልጥ ወደፊት ለመጓዝ የሚያደርገውን ከፍተኛ ጥረት ለማደናቀፍ እና ሥርዓት አልበኝነትን በአገራችን ለማስፋፋት፤ የለውጥ ኃይሉ እንቅፋት የሆኑ ተሸናፊ “ የቀን ጅቦች “ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በመሰማራት እኩይ ተግባራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ሕዝብ ሲገድሉ፣ ሲዘርፉ፣ ሲያስሩ እንዲሁም ሲያሳድዱ እና ሲያሰቃዮ የነበሩ ሹመኞች እና የቀድሞ የህወሃት መራሹ ጎጠኛ ኢህአዴግ አገዛዝ ሥርዓት የጥቅም ተጋሪ የሆኑ ሆድ አደሮች በሕግ ሊዳኙ እና ሊጠየቁ ሲገባ፤ መንግስት ጉዳዮን በቸልተኝነት በማለፉ እና በማየቱ አሁን በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎችን በማፈናቀል፣ የሐይማኖት ግጭቶችን በመቀስቀስ፣ የዜጎች እርስ በእርስ ግጭት በማነሳሳት፣ በመላው አገሪቱ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ሁከትና ብጥብጥ በመቀስቀስ ፤በዜጎች ላይ የሕይወትና የአካል ጉዳት እንዲደርስ ትልቁን አፍራሽ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡

የጉዳዮ አሳሳቢነት እየዋለ እና እያደረ አሁን ላይ በአገሪቱ ሕግ እና ሕግ አስከባሪ አካል የሌለ እስኪመስል ድረስ ሥርዓት አልበኝነት በጥቂቱም ቢሆን እየታየ ነው፡፡ እነኚህ የለውጥ እንቅፋቶች እንቅስቃሴያቸውን ለመግታት ሕዝቡ በየአካባቢው በንቃት በመጠበቅ ፣ጥፋተኞችን ለሕግ አካላት በማቅርብ ፣የአገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች እና ወጣቶች በየአካባቢያቸው የነቃ ተሣትፎ በማድረግ ሥርዓት አልበኝነት በመከላከል የለውጡ ተስፋ እንዳይቀለበስ፤ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የዜግነት ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል።

በአገራችን ኢትዮጵያ በባለፉት ወራት የለውጥ አደናቃፊዎች በተለያየ የወንጀል ተግባር በግልፅ እና በስውር ስለመሳተፋቸው የአደባባይ ምስጥር ከሆነ ቆይቷል፡፡ በተለይ በጦር መሣሪያ ዝውውር፣ በብዙ ሚሊየን የሚቆጠረ ዶላር በማሸሽ እና መሰል እኩይ ተግባር ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሰቦች እና ብድኖች በቁጥጥር ስር አዋልኩ የሚለው የፊዴራል ፖለሲ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብቻ በሚውል መልኩ በቡዙሃን መገናኛ ከሚናገረው ልፍለፋ ባለፈ የወሰድው ተጨባጭ እርምጃ ባለመኖሩ፤ እነኚህ አገር አጥፊዎች የልብ ልብ ተሰምቷቸው አገር የማመስ የተንኮል ተግባራቸውን ቀጥለውበታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ዶ/ር አብይ አህመድ ከመምህራን ጋር በነበራቸው ውይይት “ አሁን ባለው አካሄድ የህዳሴው ግድብ በቀጣይ አስር አመት ውስጥ አይጠናቀቅም ፤ ስለ ህዳሴው ግድብ የሚነገረው ነገር አብዛኛውን ለፖለቲካ ፍጆታ ወሬ ነው” ብለው በተናገሩ በቀናት ልዩነት ውስጥ፤ የህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም ጠዋት ላይ በመኪናቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው፤ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ጥልቅ ሐዘን ውስጥ የከተተ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ፕሮጀክት የሆነው የህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ! የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በታላቅ አገራዊ ፍቅር የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የአገር ባለውለታ ናቸው። የኢንጂነር ስመኘው በቀለ አሟሟትን አስመልክቶ የሚመለከተው የመንግስት አካል አስቸኳይ ምርመራ አድረጎ ከግድያው በስተጀርባ ያለውን አሻጥር ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አለበት ፡፡ ለኢንጂነር ስመኘው በቀለ ቤተሰቦች፣ወዳጅ ዘመዶች እና ለሥራ ባልደረቦች እንዲሁም ለመላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ መጽናናትን እየተመኘሁ ፤ በሥጋ ሞት ለተለዮን ባላውለታችን ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን፤ አሜን !!!

ይድነቃቸው ከበደ

One thought on “ሥርዓት አልበኝነት በመከላከል የለውጡ ተስፋ እንዳይቀለበስ ሁላችንም ዘብ ልንቆም ይገባል!!

 1. ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ…. ሀገራችን እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሳለች ፡፡ ከዶ/ር አብይ ስልጣን በፊት የተጋረጠው የስጋት ደመና ተመልሶ መቷል …. ወዴት እያመራን እንደሆነ ግልፅ ካለመሆኑ ሌላ አሳሰሳቢ ነው ፡፡ ከምንም በላይ የሀገር ደህንነት የዜጎች በሠላም ወጥቶ መግባት የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በየቦታው ያለው የሠላም መናጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በየዕለቱ የሞት ዜና መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ በሀገራችን ላይ ሞት ና ስርአተ አልበኝነት ነግሷል፡፡ከአሟሟትም የሚዘገንኑትን የሞት ዜናዎች በተለይ ኦሮሚያ ክልል እየተስተዋለ ነው፡፡ በምጥ ያለች ሴት ተኩሶ መግደል ፡ ለዚያውም ህግን በሚያወቁ ሰዎች ፡፡ የሰዉ ክቡርነት ወርዶ ነውርን ግፍን የሚጠየፍ ኢትዮጵያዊ ማንነት ባህላችን ጠፍቶ ከመለማመዳችን የተነሳ በየለቱ የሞትና የክፋት ዜናዎች ሰምተን ምንም እንዳልሆነ ማለፍ ህይወታችን ሆኗል፡፡ በተለይ ኦሮሚያ ክልል ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መቷል፡፡በየዕለቱ የሞት ዜና የማይጠፋበት የሰው ህይወት የረከሰበት በየቀኑ የንፁሀን ደም የሚፈስበት ባለቤት ያጣ አካባቢ ሆኗል፡፡ በሌሎችም አካባቢዎች ችግሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ይኼ ነገር አድጎ ማለቂያ ወደሌለው አጠቃላይ ትርምስ ውስጥ ይህች ሀገር እንዳትገባ ያሰጋል፡፡ ይህ እንዲሆን ሌት ተቀን የሚሰሩ የወያኔ ሀይሎች በምድሪቱ ሁሉ ተበትነዋል፡፡ አንድ እግራቸውን መንግስት ውስጥ ተክለው በሌላው የግድያና የአፈና ቡድን አሰማርተው ያሻቸውን ይሠራሉ፡፡ይገድላሉ ፡ ያስገድላሉ ፡ ያጋድላሉ የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ በሙሉ ሀይላቸው እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉት፡፡በጠ/ሚሩ የተደረገው የግድያ ሙከራ፡ በህዳሴው ግድብ መሀንዲስ ላይ የተደረገው የጠራራ ፀሐይ ግድያ ና በየቦታው የሚፈሰው የንፁሀን ደምና ለሌሎችም ስርዓተ አልበኝነት መንገስ ተጠያቂው ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡

  አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግራ የሚያጋቡ እውነታዎች አሉ፡፡በእርግጥ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት እያስተዳደረ ያለው ማነው ? የለውጥ ሀይሉ ወይንስ በጥቂቱ የተገፋው ና አሁንም ቁልፍ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ መዋቅርና ኢኮኖሚ ያዘው ወያኔ ነው? አዲሱ ጠቅላይ ሚ/ር ባልፈረሰው የወያኔ መዋቅር ና አሁንም ቁልፍ ቁልፍ የሚባሉ የወታደራዊና ስቪል መ/ቤቶች የወያኔ አባላት ተሰግስገው በተያዙበት ሁኔታ እንዴት ይህችን ሀገር ከገባችበት አረንቋ ሊያወጧት ይችላሉ? የዶ/ር አብይ ጉልበት እስከምን ድረስ ነው ? እስከአሁን የወሰዱት እርምጃ ሳይናቅ የገጠሙንና ሊገጥሙን ከሚችሉ ፈተናዎች አንፃር ወይንም የፀረ -ለውጡ ጥንካሬ ና የተንኮል ልምድ አንፃር ያለው ዝግጁነት ገና ብዙ የሚቀሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሀይላቸውን በበቂ ሁኔታ አላደራጁም ፡፡ ጠ/ሚ ነገሮችን አቅለው የማየት ነገር አላቸው፡፡ ይኼ ግን አደገኛ ነው፡፡ በሁሉም መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ የእዝ ሠንሠለቱ ሀሳባቸውን የሚተገብሩ ሠዎች የተሞሉ ሳይሆኑ በአንድ ብሔር የበላይነት የተሰገሰጉ የህወሀት አባላት አሁንም ይዘውታል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከዶ/ር አብይ መምጣት በፊት ዘርን ባማከለ አካሄድ ተመቻችቶላቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ዜጋ ሆነው ቁልፍ ቁልፍ የወታደራዊ ፡የኢኮኖሚ ና የፖለቲካ ቦታዎች እንዲይዙ ተደርገው ሀገር ሲመዘብሩ የኖሩ ሀይሎች በምንም ሁኔታ የለውጥ አጋር ለሆኑ አይችሉም፡፡

  የጠቅላይ ሚ/ሩ የፍቅርና የመደመር የይቅርታ ፍልስፍና ትላንት ህዝብን ሲያሰቃዩ ሲገርፉ አሰቃቂ ግድያ ሲፈፅሙ የኖሩ ተደራጅተው የሀገር ሀብት ዘርፈው የደለቡ የማፍያ ቡድን አባላት ጋር ጉዞ መጀመራቸው ዋጋ የሚያስከፍል እንጂ የሚጠቅም እስትራቴጂ አይደለም፡፡ እነዚህ የወያኔ ማፍያ አባላት ክፋት ና ተንኮል እንጂ ፍቅርን ፡ ይቅር ብለው ስለማያውቁ ይቅርታ አይገባቸውም ፡፡ የሰሩት በደል ፡ ያፈሰሱት ደም ፡ በጠራራ ፀሐይ ተደራጅተው የዘረፉት ሀብት አንድ ቀን መጠየቃችን አይቀርም ብለው ስለሚያስቡ እንቅልፍ የላቸውም ፡፡ በዚህ የተነሳ በያዙት የስልጣን መዋቅር በዘረፉት ሀብት ተጠቅመው ለውጡን ለመቀልበስ ወይንም አቅጣጫ ለማሳት የሚቻላቸውን የሞት ሽረት ትግል ያደርጋሉ፡፡ እያደረጉም ነው፡፡ የማይገባው ነገር ግን ይቅርታ ና ይቅር መባባል የተባለ ጉዳይ መልካም ቢሆንም አዲሱ ጠ/ሚ/ር ስልጣን ላይ እንደወጡ መንግስትን ና ኢሐዴግን በመወከል ለተፈፀመው በደል በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ነገር ግን በስመ መንግሰት ናበስመ ኢሐዴግ ለ27 ዓመት የኢትዮጵየ ህዝብ ላይ የመከራ ዝናብ ሲያዘንብ የኖረው መሪ ተዋናዩ ህወሀት በከለላ ቆረጣ ለማለፍ እየሞከረ ነው፡ ፡ በየትኛውም ክልል ለደረሰው ህልቆመሳፍርት ግድያ ና ቶረቸር ፡አይን ያወጣ ዘረፋና በደል የፈፀመው ያስፈፀመው ወያኔ ነው፡፡ ድፍን የኢትዮድያ ህዝብ ጣቱን የሚቀስረው ወያኔ ላይ ነው፡፡ ለደረሰው በደል የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ ያለበት ለብቻው ህወሀት እንጂ ኢሐዴግ የተባለው የይስሙለ ስብስብ አይደለም፡፡ይሁንና ወያኔ እንኳን ይቅርታ ሊጠይቅ ጥፋቱን እንኳን ያላመነ ከመሆኑም ሌላ ይባስ ብሎ ለተጨማሪ ዓመታት ሊገድል ሊዘርፍ እየተውተረተረ ይገኛል፡፡ የጠ/ሚ/ ሩ ይቅርታ ሊሰራ የሚችለው ተበዳይ ና የተጸጸተ በዳይ ሲኖር ነው፡፡ካለበለዚያ ከንግግር የዘለለ ጉዳይ አይደለም፡፡ የዚህ ቡድን የጥፋት እጅ ከሀገሪቱ አሁንም ካለመሠብሠቡም ሌላ የሀገሪቱ የሠላም ስጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡

  ስለዚህ በየትኛውም መመዘኛ እንደነዚህ ያሉ ሠዎች በመደመር ሳይሆን በመቀነስ ፍልስፍና የበለጠ ጥፋት ሊያደርሱ ከሚችሉ መዋቅር ውስጥ ማግለልና ማጥራት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚ/ሩ ላይ ላዪን እንጂ ስር አልሠደዱም ፡፡ህዝብ ቢደግፋቸውም አጠገባቸው በበቂ ሁኔታ አመኔታ ያለው ሀይል አላሰባሰቡም፡፡ ከገጠማቸው ችግር አንፃር ብቻቸውን ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው እሳቸው የሚሉትና እታች አየተሰራ ያለው እየተለያየ ያስቸገረው፡፡

  በተለይ የወታደራዊ ፡ የደህነነትና የፀጥታ መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ ከፀረ ለውጥ የወያኔ አባላት ካልፀዳ በስተቀር ይህች ሀገር ከሁከትና ብጥብጥ ፀድታ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ትሸጋገራለች ማለት ዘበት ነው፡፡ እስከ አሁንም የተደረገው የስልጣን ሹም ሽርም ቢሆን አባይን በጭልፋ ነው ፡፡ አልተነካም ማለት የቻላል፡፡ የተቀየሩትም ቢሆኑ ከላይ ያለው ሀላፊ ቢቀየርም ዘሬ ተነካ ብለው ባኮረፉ ና ጥቅማቸው በጎደለበቸው በአንድ ዘር አባላት የተሞላ የደህንነት መዋቅር ለለውጥ ሊሰራ አይችልም ፡፡ በየመዋቅሩ ውስጥ በዘር ተቧድነው ያሉ ሠዎች ታማኝነታቸው ለማን ነው ? የተደራጁት ና ሲሰሩ የኖሩት ለሐገር ሳይሆን ያንድን ቡድን የበላይነት ለማስጠበቅ ነው ? በመከላከያም ውስጥ ያለው ነገር እንዲሀ ተመሳሳይ ነው፡፡

  ስለዚህ አሁን የሀይል አሰላለፍ በፍጥነት ለመቀየር ከተቋሚ ፓርቲም ጋር ቢሆን ልዩነት እንዳለ ሆኖ ለውጡ እንዳይቀለበስ እስከ ሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ብቃት ያላቸዉን ምሁራን እየመለመሉ ጠ/ሚሩ ቁልፍ ቀልፍ ቦታዎች ከቀን ጅቦች ና ከግልገሎቻቸው እያስለቀቁ መሙላትና በአማካሪነትም እያስገቡ ሀይል ማሠባሰብ ሀገር ማዳን ይኖርባቸዋል፡ በመከላከያ ና በደህንነት ቁልፍ ቦታዎች የተሠገሠጉ የወያኔ መኮንኖች በሙስና ገንዘብ ያበዱ በየቦታው የእልቂት መርዝ በሀገሪቱ እየዘሩ ሀገር የሚያምሱት ገለል ካልተደረጉ ይች ሀገር መቼም ሠላሟ አይመጣም፡፡ እነዚህ ሀይሎች በአንድ ሉአላዊ መንግስት ውሰጥ የሚያዙት የጦር ሀይል ይዘው ሌላ መንግስታት ሆነው ባሉበት ሁኔታ ለውጡን ለመቀልበስ እንጂ የለውጥ አጋር በፍፁም ሊሆኑ አይችሉም፡፡ኢትዮጵያ የልጅ ደሀ አይደለችም፡፡ በውትድርና ሙያ አንቱ የተባሉ የተማሩ በታሪክ አጋጣሚ የተገፉ የቀድሞ ጦር ና ከዚህ መንግስት የነበሩ ዛሬም በተለያየ መሰክ ሊረዱ የሚችሉ መኮንኖች አሉ፡፡
  ስለዚህ ጠ/ሚ/ር ሆይ የኢትዮጰያ ህዝብ ቢደግፍዎት ሊሆን የሚችለው የህዝብ የደጀን ሀይል እንጂ በዕለት ዕለት ተግባርዎ ሊረዳዎት አይችልም፡፡ በዙሪያዎት ሊረዱዎት የሚችሉትን ሠዎች የማሠባሠብና የማጠናከር የቀን ጅቦችን እንዳይነክሱዎት የማባረር ስራ መስራት የርስዎ ብቻ ና አጣዳፊ ተግባርዎ ይሁን ፡፡ እግርዎ መሬት አልረገጠም ፡፡ ና ይበርቱ ፡፡ ይህ አሳር የበዛበት ህዝብ በርስዎ ላይ ተስፋ ሠንቋልና እንዳይበለጡ፡፡

  የደርግን መንግስት ገዝግዘው የጣሉት በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው የነበሩ የወያኔ አባላት በሚያቀብሉት ወታደራዊ መረጃና የኢኮኖሚና አሻጥር ነበር፡፡ የአሁኑ ሁኔታ ደግሞ ከዚያ የባሰ ደረጃ ላይ አሉ፡፡ እነዚህ ሠዎች ካለባቸው የዘር ልክፍት ፀድተው ለውጡን ይደግፋሉ ብሎ ማሰብ ለኔ የዋህነት ነው፡፡ ያኔ የነበሩበት ደረጃ ና አሁን የደረሱበት ደረጃ ስናይ ደግሞ በብዙ እጥፍ የገዘፈ ና ዘርፈ ብዙ ከመሆን አንፃር ትልቅ የለውጥ ና የሰላም ስጋት ናቸው፡፡

  በኔ እምነት ይህች ሀገር በሰላም እንዲሰፍን ና ሰላማዊ ዲሞከራሲዊ ሽግግር እንዲመጣ በዘር ኔት ወርክ የተሳሰሩና በቁልፍ ቁልፍ የስልጣን እርከኖች የተሰገሰጉትን የወያኔ አባላት መንጥሮ የማውጣት ቆራጥ አረምጃ ያስፈልጋል፡፡ በዘር ተደራጅተው ጥቃት ሲፈፅሙ ኖረው በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ደረሰ ብለው ጥቅማቸው የተነካባቸው ወያኔዎች እንደልማዳቸው ከትግራይ ህዝብ ጋር ማያያዛቸው አይቀርም፡፡ ግን ከቡድን ፍላጎት ሀገር ይቀድማል፡፡ የትግራይ ህዝብ ወንድሙ ከሆነው ከተቀረው የኢትዮጲያ ህዝብ ወያኔ ካጠረው አጥር ወጥቶ በሰላም በፍቅር አብሮ ይኖራል፡፡

  አሁን በየቦታው የሚታየውና የሚሰማው ምክንያተ ብዙ የሚዘገንኑ የሞት ዜናዎች ፡ መፈናቀሎች ፡ ረብሻ ና ስርዓተ አልበኝነት አሁንም የሚያመላክተው የሀገሪቱን አለመረጋጋት ነው፡፡ከምንም በላይ በቅድሚያ የሚያስፈልገን ሰላም ነው ፡፡ሌሎቹ ቀጥለው ነው የሚመጡት፡፡ ህዝብ ስለደገፈዎት ብቻ መንግስትዎ አይፀናም ና፡፡ ይልቁንም በህዝብ ክንድ ተደግፎ ቆራጥ ና የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ሠላማችንን ያረጋግጡ፡፡

  ሰላም ለኢትዮጵያ ይሁን

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡