ኢትዮጵያ ወደ ሽብር ወይም ብልፅግና በሚወስድ “መንታ መንገድ” ላይ ናት!

የፖለቲካ ለውጥ ማለት የኃይል ሚዛን ሽግግር ነው። በፖለቲካ ረገድ የኃይል ሚዛን የሚወሰነው በብዙሃን አመለካከት (public opinion) ነው። በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው የፖለቲካ ቡድን ስልጣን በመያዝ በስርዓቱ ውስጥ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት ይንቀሳቀሳል። በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያጣው የፖለቲካ ቡድን ደግሞ የነበረውን ስልጣን ያጣል። በመሆኑም ከዚህ በኋላ ባለው ግዜ ህልውናውን ለማረጋገጥ ሁለት አማራጮች ይኖሩታል። የመጀመሪያው የኃይል ሚዛኑ ከእጁ መውጣቱን ተቀብሎ በለውጡ ውስጥ ጥቅምና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ መንቀሳቀስ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የለውጡን እንቅስቃሴ በማደናቀፍ የለውጥ ሚዛኑን ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስ መንቀሳቀስ ነው።

የመጀመሪያው የፖለቲካ አቅጣጫ አዋጭና ቀድሞ የነበረውን የኃይል ሚዛን መልሶ ለማግኘት የሚያስችል ነው። ይህን ለማድረግ ግን በብዙሃኑ ዘንድ ያጣውን ተዓማኒነትና ተቀባይነት መልሶ ማግኘት ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ የብዙሃኑን ፍላጎት በጥንቃቄ ማጤን እና ተቀናቃኝ የፖለቲካ ቡድኖች ያለባቸውን ክፍተት መለየት እና ይህን መሰረት አድርጎ ጠንክሮ መስራት ይጠይቃል። በዚህ መሰረት የብዙሃኑን ፍላጎት በማርካት ተቀባይነት ማግኘት፣ በዚህም የፖለቲካ ኃይል ሚዛኑ ወደ እሱ እንዲያዘነብል ማድረግ ይቻላል።

ሁለተኛው አማራጭ ግን አፍራሽና አስቸጋሪ ከመሆኑ በተጨማሪ በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። ምክንያቱም የፖለቲካ ኃይል ሚዛኑ ወደ ተቀናቃኝ ቡድኖች ያዘነበለውና በዚህም የፖለቲካ ስልጣኑን ያጣው በብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት ስላጣ ነው። የለውጡን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የሚያደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴ በስልጣን ላይ ካለው የፖለቲካ ቡድን ጋር በቀጥታ ያጋጨዋል። ከዚህ በተጨማሪ ይህ አፍራሽ እንቅስቃሴ በብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተዓማኒነት ተንጠፍጥፎ እንዲያልቅ ያደርገዋል። በመሆኑም ለውጥን ለማደናቀፍ የሚደረግ ጥረት በስልጣን ላይ ካለ የፖለቲካ ቡድን ብቻ ሳይሆን ከሕዝብ ጋር ያጋጫል።

ከስልጣን የተወገደው የፖለቲካ ቡድን ቀድሞ ያጣውን የብዙሃን ድጋፍና ተቀባይነት መልሶ ለማግኘት የሚያደርገው እንቅስቃሴ በዋናነት አፍራሽና በጉልበት ላይ የተመሰረተ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። በረጅም ግዜ ሂደት ያጣውን ተቀባይነት በአጭር ግዜ ውስጥ መልሶ ለማግኘት ይሞክራል። ለዚህ ደግሞ የለውጡ ደጋፊ በሆነው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ፍርሃትና ሽብር ይነዛል። በብዙሃኑ ፍቃድና ምርጫ ያጣውን ተቀባይነትና ድጋፍ ለውጡን በሚያደናቅፍ የኃይል እርምጃ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል። በዜጎች ላይ የሽብር ጥቃት በመፈፀም የፍርሃት ድባብ ለማስፈን ይሞክራል። ይህን የሚያደርገው ለውጡ ለብዙሃኑ ሰላምና ደህንነት ዋስና እንደሌለው በማሳየት የቀድሞውን ስርዓት እንዲናፍቅ ለማድረግ ነው።

በዚህ መልኩ በለውጥ እና በፀረ-ለውጥ ኃይሎች መካከል የሚፈጠረው ግጭት በሂደት ወደ ለየለት ሽብርና ሁከት ያመራል። አብዛኛውን ግዜ “የሽብር ዘመን” (Reign of Terror) የሚመጣው አብዮታዊ ለውጥን ተከትሎ ነው። ይህ እ.አ.አ. በ1779 ዓ.ም ከተካሄደው የፈረንሳይ አብዮት እስከ 1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት በተግባር የተረጋገጠ ሃቅ ነው። በለውጥ አራማጆች እና ፀረ-ለውጥ ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ግጭት የፈረንሳይ አብዮትን ተከትሎ የሽብር ዘመን ተከስቷል። በተመሳሳይ በ1966 ዓ.ም የተካሄደውን አብዮት ተከትሎ በለውጥ አራማጆች እና ፀረ-አብዮት ቡድኖች (አድሃሪያን) መካከል የተፈጠረው ግጭት ኢትዮጵያ ላይ የሽብር ዘመን አስከትሏል።

ባለፉት ሦስት አመታት በተካሄደው ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ አማካኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት መካሄዱ ለብዙዎቻችን ግልፅ የሆነ አይመስለኝም። ይህን በግልፅ ባለመገንዘባችን ምክንያት ትላንት ከሆነው በተጨማሪ ዛሬ እየሆነ ያለውን እና ነገ የሚሆነውን በአግባቡ መገመትና መገንዘብ ተስኖናል። በእርግጥ ባለፉት ሦስት አመታት በሀገራችን አብዮታዊ ለውጥ ተካሂዷል። ይህን ተከትሎ የለውጡ ደጋፊ የሆነ የፖለቲካ ቡድን ወደ ስልጣን መጥቷል። ብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ለለውጡ እንቅስቃሴ ያለውን ድጋፍ በግልፅ አሳይቷል።

በጠ/ሚ አብይ አህመድ መሪነት የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ አለው። ነገር ግን፣ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች በለውጡ ምክንያት ቀድሞ የነበራቸው የስልጣን የበላይነትና ተጠቃሚነት አጥተዋል። በመሆኑም ለውጡን መደገፍ ወይም “መደመር” ማለት ለእነሱ የፖለቲካ ሽንፈትና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራን አምኖ እንደ መቀበል ነው። በእርግጥ ለውጡ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሊሆን ይችላል። በ1779 የተካሄደው የፈረንሳዩ አብዮት ሆነ የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት “እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ” በሚሉት መርሆች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ነገር ግን፣ አብዮቱ በተካሄደ ማግስት ፍርሃትና ሽብር ነግሷል።

በአብዮት ማግስት የሽብር ዘመን የሚከሰተው ከስልጣን የተወገደው የፖለቲካ ቡድን ለውጡን ለማደናቀፍ በሚወስደው እርምጃ እና ይህን ለመከላከል መንግስትና የለውጡ ደጋፊዎች በሚወስዱት የአፀፋ እርምጃ አማካኝነት ነው። ለውጡን ለማደናቀፍ የሚወሰዱ እርምጃዎች በዋናነት ብዙሃኑን የህብረተሰብ ክፍል በፍርሃትና ሽብር የሚያርዱ ናቸው። በመሆኑም የለውጡ ደጋፊዎች ይህን የሽብር ጥቃት እንዲያስቆም በመንግስት ላይ ጫና እና ግፊት ያደርጋሉ። ይህን ተከትሎ መንግስት የሁሉንም ዜጎች ሰላምና ደህንነት ለማስከበር የተመደበውን የፀጥታ ኃይል እና ጦር መሳሪያ ተጠቅሞ ፀረ-ለውጥ ባላቸው ቡድኖች ላይ ጥቃት መፈፀም ይጀምራል።

ከዚህ በተጨማሪ የገፈቱ ቀማሽ የሆነው የህብረተሰብ ከፍል በራሱ ተነሳሽነትና በመንግስት ድጋፍ በፀረ-ለውጥ ኃይሎች ላይ ጥቃት መፈፀም ይጀምራል። በዚህ መልኩ ሀገሪቱና ሕዝቡ በጦርነትና እልቂት ይታመሳሉ። ይህ ግዜና ሁኔታ “የሽብር ዘመን” በመባል ይታወቃል። ዛሬ በሀገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ይሄ ነው። የለውጡ ደጋፊዎች ሆነ ፀረ-ለውጥ ቡድኖች የሚወስዱት እርምጃ ሀገሪቱን ወደ ወደ ለየለት ሽብርና ብጥብጥ ሊያስገባት ይችላል። ይህን ችግር በጥንቃቄ ማለፍ ከተቻለ ግን የሁሉም መብትና ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ይቻላል። በአጠቃላይ ሀገራችን መንታ መንገድ ላይ ናት። ኢትዮጵያ ወደ ሽብር ወይም ወደ ብልፅግና በሚወስድ መንታ መንገድ ላይ ናት!

One thought on “ኢትዮጵያ ወደ ሽብር ወይም ብልፅግና በሚወስድ “መንታ መንገድ” ላይ ናት!

  1. አንዳንድ ነገሮች በሚገርም ሁኔታ እንዳይሰተካከሉ ሆነው ይበለሻሉ፡፡ፍፅም ሊስተካከል በማይችል ሁኔታ፡፡ከሰልጣን የተወገደው የፖለቲካ ቡድን ምንም ቢያደርግ ድጋሚ የብዙኃኑን ተቀባየነት አግኝቶ ወደስልጣን ሊመጣ አይችልም፡፡በቀጠይ ሊኖር የሚችለው በእኔ ግምት. . (ቆይ ትንሽ ላስብ)

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡