ለውጡ የሰነቃቸው ተስፋዎች፣ የተወሰዱ በጎ እርምጃዎች እና ያንዣበቡ አደጋዎች

ድልድይ፤ በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን የውይይት መድረክ

አቅራቢ፤ ያሬድ ኃይለማርያም
ሐምሌ 28 ቀን 2018
ብራስልስ፣ ቤልጂየም
ሀ. ምስጋና
አገራችን በፍቅር፣ በእርቅ እና በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ለመገምገም፣ በጎ የሆኑትን እርምጃዎች ለማበረታታት፣ ተስፋዎቻችንን ለማለምለም፣ ለማጎልበት እና ለማስፋት እንዲሁም ይህ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እንዳይደናቀፍ ሊገጥሙት የሚችሉ አደጋዎችን እና መሰናክሎችን ከወዲሁ ለመጠቆም በማሰብ በተዘጋጀው በዚህ ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ባለው የውይይት መድረክ ላይ ሃሳቤን እንዳካፍል ይገበዘኝን ድልድይ፤ በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን ማህበር ከልብ አመሰግናለሁ። እንዲህ አይነት መድረኮች ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ አገራችን ዛሬ ላለችበት ሁኔታ እጅግ አስፈላጊና የሚኖረውም ጠቀሜታ ከፍ ያለ ስለሚሆን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማሳሰብ እወዳለሁ።
ለ. መግቢያ፤
የለውጥ ጉዞ፤ ከየት ወዴት
ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት የሕግ የበላይነት በገፍ የተጣሰባት፣ ነጻ ዳኝነት እና ፍትህ የተጓደለባት፣ ሰብአዊ መብቶች እና የዜጎች መሰረታዊ ነጻነቶች ያለ ገደቢ የተጣሱባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የተዛነፈባት እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የተዳፈነባት አገር ነበረች። በየጊዜው ብልጭ ብለው የተዳፈኑ ተስፋ ሰጪ የሆኑ እድሎች በአግባቡ ሳንጠቀምባቸው አልፈዋል። ለዚህም በምርጫ 1987 ወቅት የታዩ ሕዝባዊ መነቃቃቶች እና ጠንካራ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር መጨረሻው እንዳይሆን ሆኖ ተጠናቀቀ እንጂ ከሚጠቀሱት የመከኑ እድሎች መካከል አንዱ ነው። ከዚህ ምርጫ ማግሥት ጀምሮ ግን በተከታታይ በመንግሥት የተወሰዱት እርምጃዎች የታዩትን የዲሞክራሲ ጭላንጭሎች ያዳፈነ እና ሥርዓቱም ከለዘብተኛ አንባገነንነት (semiauthoritariean) ወደ ለየለት አንባገነንነት (authoritarean) የተሸጋገረበት ወቅት ነበር። ሕጎች፣ የፍትሕ አካላት፣ ሕግ አውጪው፣ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙሃን እና መከላከያ ሠራዊቱ ጭምር የአፈና መዋቅሩ አካል ሆነው ቆይተዋል።
ከታሪክ እንደምንማረው እና በተለያዩ አገራትም ተደጋግሞ እንደተስተዋለው አንድን በሕዝብ ያልተደገፈ እና በሥልጣን ላይ ለረዥም ጊዜ የቆየን መንግስታዊ ሥርዓት ከስልጣን እንዲወገድ ወይም እራሱን ወደ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና እንዲመልስ ለማድረግ አራት የለውጥ መንገዶች በሥራ ላይ ይውላሉ።
አንደኛው መንገድ የተደራጁ የለውጥ ኃይሎች በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት በጉልበት እና በአመጽ ከሥሩ መንግሎ በመጣል ሙሉ በሙሉ በሌላ ኃይል የሚተኩበት ሥር-ነቀል (Revolutionary) የለውጥ ሂደት ነው። ከቀ/ኃይለስላሴ ወደ ደርግ፤ ከደርግ ወደ ኢህአዴግ የመጣንበት መንገድ ማለት ነው።
ሁለተኛው በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ታዛዥ ሆነው በቆዩ የራሱ ወታደራዊ ኃይል መሪ ተዋናይነት የሚደረግ መፈንቅለ መንግስት (coup d’etat) ነው። በአንዳንድ አገሮች ወታደራዊው ኃይል ስልጣኑን እንደያዘ ይቆያል በሌሎች ደግሞ ለአዲስ የሲቪል አስተዳደር አስረክቦ ወደ ካምፑ ይመለሳል። ይህ ሂደት ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ ተሞክሮ የከሸፈ ነገር ነው።
ሦስተኛው ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ነጻና ፍትሐዊ በሆነ የምርጫ ሂደት ተሸንፎ ሙሉ በሙሉ ሥልጣኑን ለአሸናፊው ኃይል ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መልኩ የሚያስረክብበት (democratic transtion) ነው። ለእዚህ አይነቱ ሥልጡን መንገድ ሳንታደል ስለቆየን የምናጣቅሰው ታሪካዊ ምሳሌ የለንም።
አራተኛው መንገድ ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት በውስጣዊም ሆነ በውጫዊ ወይም በሁለቱም ግፊቶች ተገዶ እራሱን የሚያርቅበት እና በሂደት ከአንባገነናዊነት ወደ ከፊል ዲሞክራት ወይም ሙሉ በሙሉ ዲሞክራሲያዊ ወደ ሆነ ሥርዓት የሚሸጋገርበት ሂደት ነው። እንደ እኔ ምልከታ ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበት ሁኔታ በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠውን የለውጥ ሂደት የተከተለ ነው።
አንድ የሕዝብ ቅቡልነት ያላገኘ እና አንባገነናዊ የሆነ ሥርዓት እራሱን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሃይል እንዲቀይር እና የፖለቲካ ለውጥም እንዲያደርግ የሚገደደው በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ Stephan Haggard እና Robert R. Kufman የተባሉት ሁለት የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎች Dictators and Democrats, Masses, Elites and Regime Change በሚል ባሳተሙት የጥናት መጽሐፋቸው ላይ በዝርዝር ገልጸውታል።
ሀ/ የመጀመሪያው ሕዝባዊ ንቅናቄ እና የተቃውሞ አመጽን መነሻ ያደረገ የሥርዓት ለውጥ ነው። ይህ የለውጥ ግፊት በተመራማሪዎች አገላለጽ Distributive Conflict Transtions የሚባለው ሲሆን ይኼውም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ባልተቀናጀ መልኩ በተለያየ አቅጣጫ በሚነሱ ተቃውሞዎች እና ግጭቶች ግፊት የተነሳ የሚመጣ የሥርዓት ለውጥ ነው፡፡ እንደ ተመራማሪዎቹ ገለጻ ይህ አይነቱ የለውጥ መንስዔ የሆነው ግፊት የሚነሳው በሦስት መልኩ ነው።
 1. በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ስጋት ውስጥ የሚጥል ሕዝባዊ የተቃውሞ ንቅናቄ ሲነሳ (mass mobilization constitutes a significant and immediate threat to the ruling elite)፣
 2. የሕዝቡ ብሶት ከማህበራዊ ፍትህ መታጣት እና ፍትሃዊ ካልሆነ የሃብት ክፍፍል ጋር የተያያዘ ሲሆን (Grievance associated with socieoeconomic inequalities constitute at least one of the motives for mobilaization) እና
 3. በሥልጣን ላይ ያሉት ልሂቃን የዲሞክራሲን ባህል ማዳበር ሳይችሉ ሲቀሩ እና በዚህም ምክንያት ለሕዝብ ጥያቄዎች እና ብሶቶች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ሲሳናቸው (Elites acquiesce to democracy in part in response to these threats. ነው።
ለ/ ሁለተኛው ደግሞ በአገዛዝ ሥርዓቱ ውስጥ ባሉ ልሂቃን የሚጠነሰስ እና የሚመራ ሽግግር ነው (Elite-led transtions)። የእዚህ ለውጥ መነሻው የሕዝብ ግፊት ሳይሆን በሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ልሂቃን የተለያዩ ጥቅሞቻቸው ሲጎሉባቸው ወይም የተሻለ ለመጠቀም ሲሉ ከራሳቸው ዘላቂ ጥቅም በመነሳት የሚያካሂዱት የሥርዓት ለውጥ ነው።
እንደ እኔ ምልከታ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ከአንባገነናዊ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው የለውጥ ጉዞ ሁለቱን አንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ነው። የለውጡ ቀስቃሽና ገፊ የሆነው ኃይል ሕዝብ ነው። ሕዝብ ባልተቀናጀ እና በአካባቢዎች በተማከለና በጎበዝ አለቆች እየተመራ የብሶት ጥያቄ የጀመረው አመጽና ቁጣ የአገዛዝ ሥርዓቱን ስጋት ላይ ለመጣል ችሏል። ይህ Distributive Conflict Transtions እንዲኖር ጫና ፈጥሯል። በኢህአዴግም ውስጥ መከፋፈልን እና ቅራኔን አስከትሏል። ሥርዓቱ የሄደበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑን እና በዛው አካሄዱም ከቀጠለ ድርጅቱ፣ አመራሩ እና አባላቱ እንዲሁም አገሪቱ አደጋ ላይ ልትወድቅ እንደምትችል የተረዱ የድርጅቱ ጥቂት አመራሮች እና ልሂቃን ፈጥነው እርምጃ መውሰድ በመቻላቸው የተጀመረውን ሕዝባዊ ንቅናቄ ወደ ሥር ነቀል የመንግሥት ለውጥ ሊያመራ እንደሚችል በመስጋታቸው በድርጅቱ ውስጥ የራሳቸውን ትግል ጀመሩ። ይህም ለውጡ የሥርዓቱ ልሂቃን ሊቆጣጠሩት ወደሚያስችል መንገድ እንዲያመራ እድል ፈጠረላቸው። የዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን መምጣት እና ኢሕአዴግ በአደባባይ ጥፋቶቹን አምኖ እና ተናዞ ለለውጥ የተዘጋጀ መሆኑ ለሕዝብ መግለጹም የተጀመረውን በብሶት ላይ የተመሰረተ የለውጥ ሥር-ነቀል የሥርዓት ለውጥ እንቅስቃሴ እንዲረግብ በማድረግ ሽግግሩ በልሂቃን እጅ እንዲወድቅ አድርጎታል። በመሆኑም አሁን ያለው የለውጥ ሂደት Elite-led transtions እንዲሆን አድርጎታል።
ይህ በሕዝብ ግፊትና ቁጣ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በአገዛዙ ልሂቃን መሪነት እንዲቀጥል መደረጉ የራሱ የሆነ አወንታዊና አሉታዊ ገጽታዎች አሉት። አዎንታዊ ከሆኑት ገጽታዎቹ በመጀመር ይህ አይነቱ የለውጥ ሂደት ያለውን አሉታዊ ገጽታም የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታዎች በማገናዘብ በመጠኑ ለመዳሰስ እወዳለሁ።
ሐ. የለውጡ አወንታዊ ገጽታዎች
ይህ በአሁን ሰዓት በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ ከሞላ ጎደል ከዚህ የሚከተሉት በጎ ገጽታዎች አሉት፤
 • ለውጡ በሕዝብ ብሶት እና ግፊት የተጀመረ በመሆኑ የሽግግሩ ዋና መድረሻ እና ግቡ የሕዝቡ ጥያቄ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መመለስ መሆኑ፣
 • በሕዝብ የተጠሉ እና በመጥፎ አድራጎታቸው የሕዝብ አይን ውስጥ የገቡ አመራሮችን እና ልሂቃንን በተለያዩ መንገዶች ከለውጡ መስመር እንዲገለሉ ማድረጉ፣
 • ሽግግሩ ከአንድ መንግሥት ወደ ሌላ መንግሥታዊ ሥርዓት የተደረገ ሥር ነቀል ለውጥ ባለመሆኑ በበርካታ ፈተናዎች የተከበበ ቢሆንም እጅግ ለስላሳ እና በተረጋጋ መልኩ እየተከናወነ መሆኑ፣
 • ሂደቱ የሚመራባቸው መርሆዎች ፍትሐዊነትን፣ ይቅር ባይነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን እና አንድነት የሚያጸኑ እንዲሆን እየተደረገ ያለው ጥረት በልሂቃኑ እና በሕዝቡ መካከል ቀደም ብለው ያልነበሩ አይነት መቀራረቦችን እና መተማመንን መፍጠሩ፤
 • የጋራ አገራዊ እራይ እንዲኖር የሚደረገው ጥረትም ሕዝቡ በልሂቃኑ ላይ እምነት እንዲጥል በቻ ሳይሆን ለውጡንም በባለቤትነት እንዲደግፍ እና ሂደቱንም በትዕግስት እንዲጠባበቅ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ፣
 • ሕዝብ የአንባገነናዊ ሥርዓቱ ማክተም ከሚፈጥርበት ደስታ ባሻገር ለውጡ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳረሻ ጎዳናንን ከወዲሁ ማመላከቱ እና የሚያያቸው አንዳንድ ተጨባጭ ኩነቶችም እንዲረጋጋ እና በሥርዓት ለውጡም ላይ እና በአገሩ ፖለቲካም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተስፋ እንዲያደርግ ማስቻሉ፣
 • ይህ አይነቱ የለውጥ ሽግግር ሳይደናቀፍ ግቡን የሚያሳካ ከሆነ ባልተናጋ መንግስታዊ መዋቅር ላይ የሚቀመጥ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ስለሚሆን በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና በሌሎች ዘርፎች የሚታዩ ችግሮችን እና በዜጎች መካከል የተፈጠሩ አግላይና ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ አሰራሮችን በቶሎ ለማጽዳትና የሕዝብ ጥያቄዎችንም በአፋጣኝ ለመመለስ ትልቅ እድልን ይፈጥራል።
መ. የእዚህ አይነት ለውጥ አሉታዊ ገጽታዎች
 • ይህ ከአንባገነናዊነት ወደ ዲሞክራሲ ጎዳና የሚደረገው የአንድ ሥርዓት ለውጥ በብዙ ጥፋቶች ውስጥ የቆየውን ሥርዓት የሥልጣን እድሜን ለማራዘሚያነት ጭምር ስለሚያገለግል የፖለቲካ ኃይሎችን ቅሬታ ውስጥ ሊከት ይችላል፣
 • ሥርዓቱ እራሱን ወደ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ቀይሮ እና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ሌሎችን አሳታፊ እንዲሆን በሚችልበት ደረጃ አዘጋጅቶ እስኪጨርስ ድረስ ባለው ጊዜ እና ሂደት ውስጥ የሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራት እና ባለ ድርሻ አካላት ሚና እጅግ የተገደበ እና በሥርዓቱ ተለክቶ በሚሰጠው ልክ ብቻ የሚወሰን መሆኑ፣
 • ሥርዓቱ በሕዝብ ተገፍቶ የተቀበለውን የለውጥ ሂደት የሚያንቀሳቅሰው ከራሱ እልውና ጋር በማጣጣም ስለሚሆን አንኳር የሆኑ እና ሥርዓቱን ሊያናጉ የሚችሉ የሕዝብ ጥያቄዎችን እያስታመመ በራሱ እርምጃ ፍጥነት ነው የሚመልሰው። በመሆኑም ሥር-ነቀል የሆኑ ለውጦችን ሊያስከትሉ የሚችሉ የሽግግር መንግስት፣የሕገ-መንግስት ቅየራ፣ የመንግስት መዋቅሮችን ማስተካከል፣ የደህንነት እና የመከላከያ ተቋማትን ገለልተኛ የማድረግ እና ሌሎች መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት በረዥም ጊዜ ሂደት ውስጥ ይሆናል።
 • በተቃራኒው የኢኮኖሚ ጥቅሞች ላይ፣ በሕዝብ አንድነት ዙሪያ፣ በአገር ሉአላዊነት እና በመሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ላይ ፈጣን የሆኑ ለውጦችን በማድረግ ቁጣዎችን ስለሚያበርድ ሌሎቹ መሰረታዊ የሆኑ ለውጦች አፋጣኝ ምላሽ ሳያገኙ ይቆያሉ አንዳንዴም በሂደት ጥያቄዎቹ እየደበዘዙ እና የሕዝቡ ትኩረት በሌሎች ጉዳዮች ላይ እንዲሆን በማድረግ ከመድረክ እንዲጠፉም ሊደረግ ይችላል።
 • እያንዳንዱ አንባገነናዊ ሥርዓት አመራር ብቻ ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ እና በጥቅም የተሳሰሩ አገልጋዮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ስለሚኖሩት የለውጡን መንፈስ ልሂቃኑ በተረዱበት መጠን እና ደረጃ ምንዝሮቹም እስኪረዱት ድረስ እረዘም ያለ ጊዜን ስለሚወስድ ለውጡ በታቀደለት እና በተጀመረበት ፍጥነት ላይቀጥል ይችላል፣
 • ልክ እንደ ኢህአዴግ ረጅም የአገዛዝ ዘመን ያስቆጠረ አንባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና ሲያቀና ከሚገጥሙት ፈተናዎች መካከል ዋናው ደግሞ በአገዛዙ ዘመን በሕዝብ ላይ ግፍ የፈጸሙ፣ በተለያዩ ወንጀሎች የተሳተፉ፣ በሙስና እና የሌብነት ወንጀል ውስጥ የተዘፈቁ አመራሮቹን እና አባላቱን በተመለከተ የሚወስደ እርምጃ አዝጋሚ መሆኑ የሚፈጥረው ችግር ነው። እነዚህ አካላት የለውጡ አካል ሆነው ወይም ከለውጡ ተገልለው የሚቆዩበት መንገድ የሥርዓቱን ቀጣይ ጉዞ ወሳኝ ያደርገዋልም
 • በተበላሸ ሥርዓት ውስጥ በአንድ ወይ በሌላ መልኩ ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር እጅግ ከሚገመተው በላይ ሊሆን ስለሚችል የምህረት፣ ይቅርታ፣ ፍትህ እና እውነትን የማፈላለጉን ጉዳይ እጅግ ውስብስብ ያደረገዋል፣
 • ይህ አይነቱ ለውጥ የሚካሄደው ልክ እንደ ኢትዮጵያ በዘር እና በቋንቋ ተከፋፍሎ እና እርስ በእርስ እየተፈራራ እንዲኖር በተደረገ ማህበረሰብ ውስጥ ሲሆን ደግሞ ሌሎች በርካታ ፈተናዎች ይገጥሙታል። እያንዳንዱ ብሔር የሚያነሳቸው ጥያቄዎች፣ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ አንዱ ሌላውን መወንጀል፣ ማፈናቀል እና ማሳደድ እንዲሁም የአክራሪ ብሔረተኞች ጥያቄ እና የአገር አንድነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ በርካታ ነገሮች በዚህ ሂደት ውስጥ እንደ አሸን ይፈለፈላሉ፣
 • ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገውን የለውጥ ሂደት የአገዛዝ ሥርዓቱ በጎ እርምጃዎች ተደርገው ስለሚቆጠሩ እና በሕዝብም ዘንድ ያልጠቆጠበ እና ስሜታዊ የሆነ አድናቆት እና ድጋፍ ስለሚቸራቸው ከለውጡ ማግስት በሚደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ውድድር ላይ ትልቅ ጫናንም ይፈጥራል። ተቃዋሚዎች ባልተሳተፉበት ሂደት ውስጥ የተገኙት የለውጥ ድሎች ሁሉ የአገዛዝ ሥርዓቱ እና የልሂቃኑ ተደርገው ስለሚወሰዱ ሕዝብ በነጻና ፍትሐዊ በሚመስለው ቢያንስ በመጀመሪያው ምርጫ ሂደት ላይ ምንም ሳያቅማማ ድምጹን ለአገዛዝ ሥርዓቱ እንዲሰጥ መንፈጻዊ ጫናን ያሳድራል፣
 • በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ምንም አስተዋጽኦ እንዳይኖራቸው የተደረጉ የፖለቲካ ተወዳዳሪ ኃይሎች በአገዛዝ ሥርዓቱ የለውጥ ሂደት የተደመመውን ሕዝብ ትኩረት ለማግኘት መንገዱ የተራራ ያህል ከባድ ይሆንባቸዋል። በመሆኑም የዲሞክራሲያዊው ምርጫ አዳማቂዎች ከመሆን እና የተወሰኑ የምክር ቤት ወንበሮችን እንዲያገኙ ከማድረግ በዘለለ ጥሩ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ሂደቱ አይፈቅድላቸውም።
ሠ. የመፍትሔ ሃሳብ
ከዚህ የሚከተሉት አራት ዋና ዋና ነገሮች ከላይ በእንቅፋትነት እና ለውጡን በማሰናከል እረገድ ወይም አቅጣጫ ለማሳት አስተዋጾ የሚኖራችውን ችግሮች ለመቋቋም እና ለማለፍ ያስችላሉ።
 1. መንግስት በጀመረው የለውጥ ሂደት ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከታዛቢነት እና ደጋፊነት ባለፈ ዋና ተዋናይ እንዲሆኑ እና በሙሉ ሂደቱ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ። ለዚህም በአፋጣኝ አንድ አገራዊ ጉባዔ በመጥራት የለውጡን አቅጣጫ የሚከታተል፣ የሚመራ እና ፍኖተ ዲሞክራሲ የሚነድፍ ሁሉ አቀፍ ብሔራዊ ጉባዔ ቢቋቋም፤
 2. በአገሪቱ ውስጥ ላለፉት 27 ዓመታት እና ከዛም በፊት በርካታ የመብት ጥሰቶች በግለሰቦች እና በሕዝብ ላይ ሲፈጸም የቆየበት አገር ስለሆነ ለበቀል ሳይሆን ለትምህርት እና ለይቅርታ በሚያመች መልኩ የተፈጸሙትን በደሎች በዝርዝር የሚያጠና፣ የመብት ጥሰት ፈጻሚ የሆኑትን አካላት እና የኃላፊነት ደረጃ ለይቶ የሚያወጣ፣ በተለይም የስቃይ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ለደረሰባቸው የስነ-ልቦና እና የአካል ጉዳት ተገቢውን ድጋፍ እና እርዳታ እንዲያገኙ የሚያደርግ አገራዊ የእውነት እና ፍትሕ አጣሪ እና አፈላላጊ ጉባኤ እንዲቋቋም ማድረግ፤
 3. በአገር ግንባታ ላይ የግለሰቦች መልካም ስብዕና ትልቁን ሚና የሚጫወት ቢሆንም አገር የሚቆመው በጠንካራ፣ ገለልተኛ እና የሕዝብ በሆኑ ተቋማት ሰለሆነ የፍትህ፣ የአገር ጸጥታ እና ደህንነት፣ መከላከያ እና ሌሎች ወሳኝ በሆኑ ሕዝባዊ ተቋማት ላይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት እራሳቸውን በዲሞክራሲያዊ እሴቶች እንዲያንጹ እና አገራዊ ኃላፊነት በሚሰማቸው ባለሙያዎች እንዲመሩ ማድረግ፤
 4. የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ጎን ለጎን ጠንካራ ሚዲያዎች፣ የሲቪክ ማህበራት እና የሙያ ማህበራት እንዲፈጠሩ አስፈላጊውን የሕግ፣ የፖለቲካ እና ሌሎች አስተዳደራዊ እርምጃዎችን በአፋጣም መውሰድ የግድ ይላል።
መደምደሚያ
ኢትዮጵያን ከገባችበት ቅርቃር እንድትወጣ እና በአለም አደባባይ ቀና እንድትል ለማድረግ ጥሩ መሪ ማግኘት እና የመንግስት ለውጥ ብቻውን በቂ አይደለም። በትምህርት፣ በምርምር እና በእውቀት ያልተገነባ ማህበረሰብ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚደረገው ለውይ ላይ ንቁ ተሳታፊ ሊሆን አይችልም። ሕዝብ መንግስትን ሊቆጣጠር እና የአገሩና የሥልጣኑ ባለቤት ሊሆን የሚችለው በእውቀትና በንቃት የአገሩን ጉዳይ በባለቤትነት ስሜት ስከታተል፣ ጥፋት ሲያይ በድፍረት በአደባባይ ሲቃወም እና ሲያርም፤ እንዲሁም በጎ የሆኑ ነገሮችን ደግሞ ማበረታታ ሲችል ብቻ ነው። መንግስት የተቆጣ ለት ወደ የጉሮኖው የሚገባ እና መንግስትን ከነ ጥፋቱ እና ወንጀሎ አዝሎ እሹሩሩ የሚል፤ መንግስት መዳከሙን ሲያይ ደግሞ የአገሩ ባለበት እሱ መሆኑ ትዝ ብሎት አደባባይ ወጥቶ የሚፎክር ሕዝብ ሊለወጥ አይችልም። የጠንካራ ሕዝብ መገለጫው ከሕግ እና ከሥርዓት ያፈነገጠን አካል አስገድዶ ወደ መስመር ማምጣት ሲችል ነው። ስለዚህም ለሕዝብ ያለኝ መልክት ገዢዎቻችን ሲባልጉ ወይም መስመር ሲስቱ እያየን ዝም አንበርል። ሳይቃጠል በቅጠል እንደሚባለው ሁሉም ዜጋ መብቱን አስከባሪ እና ግዴታውን አክባሪ መሆን ይኖርበታል።
መንግሥትም ይህ የተከፈተው አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ እንዳይጨናገፍ እና እየወጣነበት ካለነው የአንባገነን ሥርዓት አዙሪት ዳግም እንዳንመለስ እና አገሪቱም ወዳልተፈለገ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ ለሕዝብ ብሶቶች እና ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የለውጡን እውነተኝነት እስከ አሁን እየወሰዳቸው እንዳሉት የለውጥ እርምጃዎችን በተመባጭ ማሳየቱን መቀጠል አለበት።
አቶ ያሬድ ሃይለማሪያም

Source: Human Rights in Ethiopia Blog