በኢ/ር ስመኘው ግድያ እጁ አለበት የተባለው ግለሰብ “ኢህአዴግን ለመታደግ ማንንም ለመግደል ዝግጁ መሆኑን” ሲገልፅ የሚያሳይ ቪዲዮ

ከኢ/ር ስመኘው ግድያ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ግምቶች እየተሰጡ ነው። ከግድያው ጋር ተያይዞ ብዙ አጠራጣሪ ነገሮች ተከስተዋል። በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ “ልፍዓተይ ተስፋ” እና “Tsion Berhanu” የተባሉት ግለሰቦች የሚያወጧቸው መረጃዎች የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። በመጀመሪያ “ልፍዓተይ ተስፋ” የተባለው ግለሰብ ምንም ነገር በሌለበት “የኢ/ር ስመኘው ድህንነት ያሰጋኛል” የሚል ጠቋሚ መረጃ ማውጣቱ ይታወሳል። ከአምስት ቀናት በኋላ ኢ/ር ስመኘው በጥይት ተመትተው ይገደላሉ። ከዚያ በመቀጠል “Tsion Berhanu” የሚባለው ግለሰብ ራሱን “ልፍዓተይ ተስፋ” እንደሆነ በመግለፅ የተወሰኑ መረጃዎችን ማውጣት ጀመረ። እኔን ጨምሮ የተወሰኑ ታዋቂ ሰዎችና የመንግስት ባለስልጣናት “ደህንነት ያሰጋኛል” የሚል መረጃ አውጥቶ ነበር።

ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ከኋላው ካሉ ግለሰቦች ጋር ያለ መግባባት እንደተፈጠረ በመግለጽ የኢ/ር ስመኘውን ትክክለኛ ገዳዮችን ማንነት ይፋ እንደሚያወጣ ተናገረ። ይህን ተከትሎ “ልፍዓተይ ተስፋ” የሚባለው ግለሰብ ዳንኤል ብርሃነ እንደሆነ እና ቴዲ ማንጁስ (Teddy Manjus) ከተባለ ግለሰብ ጋር በኢ/ር ስመኘው ግድያ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንደሆነ ጠቆመ። ቴዲ ማንጁስ የተባለው ግለሰብ ከግድያው በፊት ፌስቡክ ገፁ ላይ የነበሩ ምስሎችን እንዳጠፋ፣ ዳንኤል ብርሃነ ደግሞ ወደ ውጪ ሀገር እንደሄደ ተናገረ።

እኔም እነዚህን መረጃዎች በፌስቡክ ገፄ ላይ ያወጣሁ ሲሆን በአንድ ቀን ውስጥ ከ3ሺህ በላይ ሰዎች በፌስቡክ ገፃቸው ላይ አጋሩት። ይህን ተከትሎ “ልፍዓተይ ተስፋ” እና ቴዲ ማንጁስ (Teddy Manjus) ወደ ፌስቡክ ተመልሰው በመምጣት “Tsion Berhanu” የሚባለው ግለሰብ እኔ (ስዩም ተሾመ) እንደሆነ መግለፅ ጀመሩ። ከዚህ በተጨማሪ፣ ቀንደኛ የህወሓት ደጋፊዎች እኔ ከጠ/ሚ አብይ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለኝ በመጥቀስ በኢ/ር ስመኘው ግድያ ላይ እጄ እንዳለበት በገፃቸው ላይ መወንጀል ጀመሩ።

አሁን ይሄን ፅሁፍ የምፅፍበት ምክንያት እነዚህን ሰዎች ውንጀላ ለማስተባበል ወይም ራሴን ለመከላከል አይደለም። ምክንያቱም እኔ በእንዲህ ያለ ወራዳ ተግባር ለመሰማራት የሚፈቅድ ስብዕና ሆነ አቅም የለኝም። ከዚያ ይልቅ፣ የ“Tsion Berhanu” እና “ልፍዓተይ ተስፋ” ፅሁፎችን በፌስቡክ ገፄ ላይ ማውጣቴ በሁለቱ መካከል ልዩነት እንዳለ ለመረዳት አስችሎናል። የመጀመሪያው ነገር “Tsion Berhanu” እና “ልፍዓተይ ተስፋ” የተለያዩ ግለሰቦች መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል። ሁለተኛ ነገር ሁለቱም ግለሰቦች በኢ/ር ስመኘው ግድያ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎና መረጃ እንዳላቸው መገመት ይቻላል።

“ልፍዓተይ ተስፋ” የተባለው ግለሰብ ኢ/ር ስመኘው ከመገደሉ በፊት ስለሁኔታው ቀጥተኛ መረጃ አለው። ምክንያቱም ምንም ነገር በሌለበት ስለ ኢ/ር ስመኘው ደህንነት ስጋት ሊገባው አይችልም። በእርግጥ ይህ ግለሰብ ዳንኤል ብርሃነ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለኝም። ነገሮችን በአጭሩና ስላቃዊ በሆነ መንገድ የሚገልፅበት ሁኔታ የረጅም አመት የመፃፍ ልምድ እንዳለው፣ ከሚያወጣቸው መረጃዎች አንፃር ደግሞ “ውስጥ-አዋቂ” መሆኑን መገመት ይቻላል። ነገር ግን፣ የኢ/ር ስመኘውን ግድያ በሌሎች ላይ ፍርሃትና ሽብር ለመንዛት መጠቀሙ ግለሰቡን አጋልጦታል።

በዚህ ረገድ “Tsion Berhanu” ግድያው የተፈፀመበትን ሁኔታ የገለፀበት አግባብ ለብዙዎቻችን አሳማኝ ባይሆን እንኳን ጠቋሚ መሆኑ እርግጥ ነው። የመጀመሪያው ነገር ፅሁፎቹን በፌስቡክ ገፄ ላይ ማውጣቴን ተከትሎ “ልፍዓተይ ተስፋ” እና “ቴዲ ማንጁስ” ወደ ፌስቡክ በመምጣት “Tsion Berhanu ስዩም ተሾመ ነው” በማለት ነገሩን ወደ እኔ ለማዞር መሞከራቸው ነው። ሁለተኛ ቀንደኛ የሆኑ የህወሓት ደጋፊዎች በተመሳሳይ የስም ማጥፋት ተግባር መሰማራታቸው ነው። ሦስተኛና ዋንኛው የቴዲ ማንጁስ አመለካከትና አቋምን በግልፅ የሚያሳይ ቪዲዮ መገኘቱ ነው።

“Tsion Berhanu በኢ/ር ስመኘው ግድያ ላይ ተሳትፏል” በማለት የሚወነጅለው ቴዲ ማንጁስ ማን ነው? በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የወጣው ቪዲዮ ምስል “Tsion Berhanu” ካወጣው የፎቶ ምስል ጋር አንድ ነው። ከዚህ ፅሁፍ ጋር በተያያዘው የቪዲዮ ምስል እንደምትመለከቱት ቴዲ ማንጁስ የሚባለው ግለሰብ ጀዋር መሃመድን ለመግደል ይዝታል። አሁን በኢህአዴግ ውስጥ እየታየ ያለውን ለውጥ በፅኑ የሚቃወም ከመሆኑ በተጨማሪ ለውጡን ለማደናቀፍ ማንኛውንም ዓይነት እኩይ ተግባር ለመፈፀም ዝግጁ እንደሆነ ይገልፃል።

በእርግጥ ይህን የቪዲዮ ምስል መነሻ በማድረግ ግለሰቡ በኢ/ር ስመኘው ግድያ ላይ በቀጥታ ተሳትፏል ለማለት አይቻልም። ነገር ግን፣ በዚህ ቪዲዮ ምስል ከሚያንፀባርቀው አቋም፣ እንደ እሱ አገላለፅ “ኢህአዴግን ለመታደግ ማንኛውንም ዓይነት ነገር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን፣ እንዲሁም የጦር መሳሪያና የአሜሪካ ቪዛ ቢያገኝ ጃዋር መሃመድን ያለበት ድረስ ሄዶ እንደሚገድለው በግልፅ ተናግሯል። ከዚህ አንፃር ግለሰቡ ኢ/ር ስመኘውን የመግደል ግዳጅ ቢሰጠው ያለ ምንም ማወላወል ሊገድል እንደሚችል መገመት ይቻላል። በመሆኑም ለሚመለከተው የመንግስትና ለማህብረሰቡ ጠቃሚ መረጃ ሊሰጥ ይችላል በሚል እምነት ቴዲ ማንጁስ የሚናገርበትን የቪዲዮ ምስል ከዚህ ፅሁፍ ጋር አያይዘን አቅርበናል።

ማሳሰቢያ፡-

በዚህ ፅሁፍ የቀረበው ሃሳብ በነባራዊ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ግምትና መላምት ነው። የፅሁፉ ዓላማ መረጃን ለአንባቢያን ማቅረብ ነው። ከዚያ በተረፈ በፅሁፉ ውስጥ በተጠቀሱት ግለሰቦች ላይ የሃሰት ውንጀላ ወይም ስም የማጥፋት ዓላማ የለውም። በዚህ ፅሁፍ ምክንያት የሃሰት ውንጀላ ወይም ስም ማጥፋት ደርሶብኛል የሚል አካል ቢኖር ከሁሉም አስቀድሜ ይርቅታ ለመጠየቅና ለመታረም ዝግጁ መሆኔን ለመግለፅ እውዳለሁ።

4 thoughts on “በኢ/ር ስመኘው ግድያ እጁ አለበት የተባለው ግለሰብ “ኢህአዴግን ለመታደግ ማንንም ለመግደል ዝግጁ መሆኑን” ሲገልፅ የሚያሳይ ቪዲዮ

  1. ስዩም፤ በነዚህ ሰዎች ተንኮል መሸበር አይኖርብህም፡አንተ ለሀገርህ በሀቅ የምትደክም እንጂ እንደነዚህ ሰዎች ሸርና ተንኮል የማታዉቅ በመሆንህ ተደናጠህ ከጀመርከዉ ዓላማ ማፈግፈግ አይኖርብህም፡፡ከዓላማህ ማፈግፈግ ከጀመርክ የነሱን ዓላማ አሳካህ ማት ነዉ፡፤እነሱ እኮ ትላንት በአደባባይ ሊገሉት ሞክረዉ ያልተሳካላቸዉን ዶ/ር አብይን ከኢንጂነሩ ግድያ ጋር ሊያቆራኙ የሚመክሩ ባለጌዎች አንተን አንድ ምስኪን ሰዉ ያለቦታህ ሊያነካከሁህ መፈለጋቸዉ የሰይጣን ባህሪያቸዉን ነዉ የሚያሳየዉ፡፡ለማንኛዉም የዚህ ዓነቱ ለዉጥ ለጊዜዉ እንቅፋት ባያጣዉም ቀስ በቀስ እየጠራ መሄዱ አይቀርምና በርታ በል፡፤እኛን በጣም የቸገረን ነገር ወንጀለኞች እንዳሻቸዉ እየቦረቁ ንጹሃን ዜጎች ለስጋት መዳረጋቸዉ መቼ ያበቃል የሚለዉ ጥያቄ ነዉ፡፡ ሰዉያችን መቼ ነዉ ቆንጠጥ ያለ እርምጃ መዉሰድ የሚጀምሩት?ለፈስፈስ ማለታቸዉን አልወደድኩላቸዉም፡፡ ደግሞ እሳቸዉ ካላዘዙ በስተቀር ራሱን ችሎ ህግ ማስከበር የሚችል አካል የለም እንዴ?የት አለ ደህንነት መስሪያቤቱ ?መከላከያና ፖሊስስ ዬት ነዉ ያለዉ ?ለምንድነዉ ምድረ ወንጀለኛን እንድ በአንድ እየለቀሙ በቁጥጥር ስር የማያደርጉት?የለዉጡ አመራር ጠንካራ ካልሆነ የለዉጡ ደጋፊዎች ማመንታት እንደሚጀምሩና በዚያ አጋጣሚ ተጠቅመዉ ጸረ- ለዉጥ ኃይሎች ተመልሰዉ የቀድሞ ቦታቸዉን በመቆጣጠር የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ ከሌሎች ሀገሮች ልምድ አይታወቅም እንዴ?”ራሱን መከላከል የማይችል አብዮት እርባና የለዉም” የተባለዉን የሩሲያ ዘመን አባባል ተዘንግቶ ይሆን?

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡