የህወሓት ቀጣይ አቅጣጫ፡ “ትላንት አፋኝ የነበረ ነገ እንቅፋት ይሆናል!”

ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ የወሰዳቸው የለውጥ እርምጃዎች በጣም አስደናቂ ናቸው አይደል? አዎ! በእርግጥ አንዳንዶቹ ለውጦች በቀጣይ አስርና ሃያ አመት ይመጣሉ ተብለው ያልተጠበቁ ናቸው። ይህ ለውጥ እንዲመጣ ላለፉት 27 ዓመታት ብዙዎች ታግለዋል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ለእስርና ስደት ተዳርገዋል። ስለዚህ ለውጡን ለማምጣት ብዙዎች መስዕዋት ከፍለዋል። ዶ/ር አብይ በአሜሪካ ሚኒሶታ ባደረገው ንግግር “ከሁለት አመት በፊት ፊቴ ላይ ማዲያት አልነበረም። ልጆቻችንን ማሳደግ ተስኖን በስደት የአሜሪካ መንግስት ነበር የሚያሳድግልን” ብሏል።

የተደረገው ትግልና የተከፈለው መስዕዋት አሁን የመጣውን ለውጥ ማምጣት ምን ያህል ከባድና አስቸጋሪ እንደነበር ያሳያል። ይህ ደግሞ የሆነው በሌላ ምክንያት ሳይሆን ፀረ-ለውጥ የሆነ ኃይል ስለነበር ነው። ዛሬ ላይ ለውጡ ብርቅ የሆነብን ይህን ፀረ-ለውጥ ኃይል ተቋቁመን በማሸነፋችን ነው። የመጣውን ለውጥ ጉልህ የሚያደርገው ለውጡ እንዳይመጣ የሚፈልገው ኃይል ጠንካሬ ነው። ስለዚህ የለውጡ ፍላጎትና ጥያቄ ትልቅ ቢሆንም ይህን የለውጥ ንቅናቄ ለማዳፈን የሚሻው ወገን በዚያኑ ያክል ትልቅና ጠንካራ ነው።

የለውጡን ንቅናቄ በኃይል ለማዳፈን ያላሳለሰ ጥረት ሲያደርግ የነበረው ኃይል ማን ነው? በዚህ ረገድ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ህወሓት ነው። በእርግጥ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች፣ ቡድኖች እና የመንግስት ተቋማት ለውጡን ለማደናቀፍ ተንቀሳቅሰዋል። ሆኖም ግን፣ እነዚህ አካላት ለውጡን በማደናቀፍ ረገድ የነበራቸው ሚና የህወሓት መገልገያና መጠቀሚያ ከመሆናቸው የመነጨ ነው።

ለምሳሌ የክልል መንግስት ኃላፊዎች፣ የፌዴራልና ክልል ፀጥታ ተቋማት፣ የሀገር መከላከያና ደህንነት መስሪያ ቤቶች፣ እንደ ቴሌኮሚኒኬሽን ያሉ የመንግስት ልማት ድርጅቶች፣…ወዘተ ሁሉም ለውጡን በማደናቀፍ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው እንደነበር ይታወሳል። ይህ የሆነው ግን ህወሓት ከመንግስታዊ መዋቅሩ ጀምሮ የተቋማት አደረጃጀትና አሰራር የተዘረጋው በፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ የሚቃጣን ማንኛውም ዓይነት ለውጥና መሻሻል ለማዳፈንና ለማፈን እንዲያመቸው አድርጎ ስለነበር ነው። ስለዚህ እነዚህ አካላት ለውጡን በማደናቀፍ ረገድ የነበራቸው ሚና የህወሓት መጠቀሚያና መገልገያ መሆን ነው።

እነዚህ አካላት የተቋቋሙበትን ዓላማና አገልግሎት ወደ ጎን በመተው የህወሓትን የበላይነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጭቆና መሳሪያና መገልገያ በመሆናቸው ተጠያቂ ናቸው። ነገር ግን፣ በግንባር ቀደምትነት የሚጠየቀው ለራሱ ጥቅምና የበላይነት እንዲያገለግሉ አድርጎ የዘረጋቸው ህወሓት ነው። ስለዚህ አሁን የመጣው ለውጥ እንዳይመጣ በራሱም ሆነ ከላይ በተጠቀሱት ተቋማት አማካኝነት በግንባር ቀደምትነት ሲንቀሳቀስ የነበረው ህወሓት ነው። ከለውጡ በኋላ ይህ ፀረ-ለውጥ ቡድን ወደየት ሄደ? ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ አፈገፈገ እንጂ አልወደቀም ወይም ሀገር ጥሎ አልወጣም።

ከለውጡ በኋላ ህወሓት ቀድሞ በበላይነት ተቆጣጥሮት የነበረው የፖለቲካ ስልጣን በከፊል ተቀማ እንጂ ጨርሶ አልተሸነፈም። ላለፉት 27 አመታት ለውጡን ለማደናቀፍ በተቻለው አቅም ሲረባረብ ከነበረ የፖለቲካ ቡድን ጋር አብሮ መስራት ይቻላል? ይህን ፀረ-ለውጥ ቡድን በሂደቱ ውስጥ በማሳተፍ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣትና ማስቀጠል ይቻላል? በፍፁም አይቻልም!

ላለፉት አመታት የለውጡን እንቅስቃሴ በኃይል ለማፈንና ለማዳፈን በመሪነት ሲንቀሳቀስ የነበረው ህወሓት መሆኑ እርግጥ ነው። ነገር ግን፣ አሁን ላይ ህወሓት እንደ ቀድሞው በደልና ግፍ መፈፀም ያቆመው ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ ፈልጎና ፈቅዶ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የለውጡን እንቅስቃሴ ለማዳፈን ሲጠቀምባቸው፥ ሲገለገልባቸው የነበሩት ኃይሎች ከህወሓት ቁጥጥር ውጪ በመሆናቸው ነው።

የተለወጠ ነገር ቢኖር የህወሓት መጠቀሚያ የነበሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፤ በዋናነት ኦህዴድና ብአዴን፣ እንዲሁም የህወሓት መገልገያ የነበሩት የመከላከያና ደህንነት ተቋማት፣ የክልልና ፌደራል ፀጥታ ሃይሎች፣ እንዲሁም የቴሌኮሚኒኬሽን፣ ፋይናንስ እና እንደ የብሮድካስት ባለስልጣን ያሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከህወሓት ቁጥጥር ውጪ በመሆናቸው ነው። ከዚያ በተረፈ የህወሓት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ እንኳን መደገፍ እውነት መሆኑን መቀበል አይሹም።

ከለውጡ ጋር በተያያዘ ለህወሓት አባላትና ደጋፊዎች የሚታያቸው ነገር ቢኖር አፍራሽና በትግራይ ህዝብና ህወሓት ላይ የጋረጠው አደጋ መሆኑ ብቻ ነው። በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በጎረቤት ሀገራት ህዝብና መንግስት፣ ብሎም በዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ዘንድ እንደ መልካም ጅምር የተወሰደው ለውጥ በህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ዘንድ የህልውና አደጋ ተደርጎ ይወሰዳል። በእንዲህ ያለ አመለካከትና እይታ ህወሓት የለውጡን እንቅስቃሴ ይደግፋል ብሎ መጠበቅ ከየዋህነትም በላይ ቂልነት ነው።

በመሰረቱ የትኛውም የፖለቲካ ቡድን ቢሆን ህልውናውን በሚያሳጣው እንቅስቃሴ ውስጥ በራሱ ምርጫና ፍቃድ አይሳተፍም። የለውጡን እንቅስቃሴ በማደናቀፍ ህልውናውን ለመታደግ ይረባረባል እንጂ ራሱን በራሱ ጠልፎ አይጥልም። ስለዚህ ህወሓት መቼም፥ እንዴትም ቢሆን ላለፉት 27 አመታት ለማዳፈን የታገለውንና አሁን እውን እየሆነ ያለውን ለውጥ አይደግፍም። ከዚያ ይልቅ የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ከመስራት አይቦዝንም። ለምን?

ጠ/ሚ አብይ አህመድ የጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴ በሁለት ነገሮች ላይ ማዕከል ያደረገ ነው። እነሱም እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ናቸው። ላለፉት 27 አመታት ሲነሳ የነበረው የፖለቲካ ጥያቄ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ነው። በየትኛውም የፖለቲካ ማህብረሰብ ዘንድ ቢሆን ዜጎች የሚያነሱት የፖለቲካ ጥያቄ በጥቅሉ “እኩል መብትና ነፃነት ይኑረን፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልና ተጠቃሚነት ይኑር” የሚል ነው። ላለፉት ሦስት አመታት የታየው የለውጥ ንቅናቄም በእነዚህ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ላይ ማዕከል ያደረገ ነው።

ይሁን እንጂ፣ ከህወሓት አንጋፋ አመራሮች አንዱ አቶ ስዩም መስፍን ባለፈው ወር መቐለ ላይ በተካሄደ ስብሰባ አሁን የተጀመረው ለውጥ በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የተቃጣ አደጋ እንደሆነ በግልፅ ተናግረዋል። ሌላው ቀንደኛ የህወሓት ታጋይና የቀድሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ጄኔራል ተክለብርሃን ወልዳረጋይ ከወራት በፊት “ወራይና” ከተባለ መጽሄት ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ በማሳያነት የሚጠቀስ ነው። እንደ ጄኔራሉ አገላለፅ፣ የትግራይ ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሲነጻጸር የራሱ የሆነ አንጸራዊ ብልጫ (comparative advantage) የሚያስገኙለት እሴቶች አሉት። ይህን አንጻራዊ ብልጫ በአገር አመራር ደረጃ ሊጠቀምበት እንደሚገባ በመጥቀስ የትግራይ ወጣቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂው ዘርፍ ተምረው አመራሩን መያዝ እንዲችሉ ከሌላ ብሔር ተወላጆች በተለየ የትግራይ ተወላጆችን በብዛት ወደ ውጭ ሀገር ለትምህርት እንደሚልኩ በግልፅ ተናግረዋል። ከዚህ አንፃር የህወሓት ዓላማና ስትራቴጂ ከኢትዮጵያዊያን እኩልነት ይልቅ የትግራይን የበላይነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

በሌላ በኩል ባለፉት ሦስት አመታት የታየውን የለውጥ ንቅናቄ በኃይል ለማዳፈን የሚደረገውን ጥረት ከፊት ሆነው የመሩት የህወሓት መስራችና አመራር የሆኑት አቶ አባይ ፀሓዬ ናቸው። በዚህ አመት መጀመሪያ በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ የፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች የህዝብ ብዛትና የመሬት ቆዳ ስፋት መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል?” የሚል ጥያቄ ከኦህዴድና ብአዴን አመራሮች በመነሳቱ ምክንያት ክፉኛ ተበሳጭተው “ይህ ጥያቄ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሲነሳ ከመስማት ግንባሩ ራሱ ቢፈርስ ይሻላል” በማለት በቁጭት መናገራቸው ይታወሳል። ስለዚህ አቶ አባይ ፀሓዬን የሚያስቆጫቸው ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አለመረጋገጡ ሳይሆን የፍትሃዊነት ጥያቄ መነሳቱ ነው።

በዚህ መሰረት፣ ጠ1ሚ አብይ የጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴ ሆነ ባለፉት አመታት ሲነሳ የነበረው የፖለቲካ ጥያቄ በእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ማዕከል ያደረገ ነው። በሌላ በኩል የህወሓት አመራሮች፥ አባላትና ደጋፊዎች ዓላማና ግብ የራሳቸውን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ የብዙሃኑን መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስችላል። የብዙሃኑ መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከተረጋገጠ የህወሓቶች የበላይነትና ተጠቃሚነት ያበቃል። ይህ ከሆነ ደግሞ የህወሓቶች ህልውና ያከትማል። ስለዚህ በተቻላቸው አቅም ሁሉ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ጥረት ያደርጋሉ። ለህወሓት አባላትና ደጋፊዎች የለውጡን እንቅስቃሴ ማደናቀፍ የተመሰረቱበትን ዓላማና ግብ ማስቀጠል፣ ህልውናቸውን ማረጋገጥ ነው። በተቃራኒው የለውጡ መሳካት ለህወሓቶች ውድቀት ነው። ስለዚህ ላለፉት 27 አመታት የለውጥ አፋኝ ነበሩ፣ ከአሁን በኋላ ደግሞ የለውጡ እንቅፋት ሆነው ይቀጥላሉ።