የመከላከያ ሰራዊት በሶማሌ ክልል እየወሰደ ያለው እርምጃ: ወሳኝነት ስጋቶች እና ምክንያቶች

ጅጅጋና ሶማሌ ክልል ወሳኝ ወታደራዊ ኦፕሬሽን እየተካሄደ ነው። አብዲ ኢሌይ ቢያዝም ከፖለቲካና ወታደራዊ ጉዳዮች ረገድ ዘመቻው ቀጣይና ያላበቃ ነው። ሆኖም ግን የዘመቻው ውጤት የወደፊቱን ሀገሪዊ የፖለቲካ አቅጣጫ አመላካች የመሆን አቅም አለው።

በገመቺስ አስፋው

ከምክንያቶቹ ውስጥ የጠሚ አብይ አስተዳደር ሰላም ለማውረድ ሲባል ሲያራምደው ከነበረው የምክክርና የመደመር ፖለቲካ ወደ ወታደራዊ እርምጃ መሽጋገሩ ነው። ጠሚው በዚህ ወቅት በግፊት ወደዚህ እርምጃ የገቡ ቢሆንም በዚህ መንገድም ሰላም ማረጋገጥ እንደሚቻል ለማየት የዘመቻው ዉጤት ወሳኝ ነው።

ዘመቻው በክልሉ ህዝቦችና የፌደራል መንግስት (የኦሮሚያም ጨምሮ) መካከል ወደ ፊት የሚኖረው ግንኙነት ምን አይነት መልክ እንደሚኖረው የመወሰን አቅም አለው። የተሳካ ዘመቻን ተከትሎ ክልሉን ባዲስ መልክ ማዋቀር፡ ድንበር አካባቢ ሰላምና መረጋጋትን መፍጠርና ከፌደራል መንግስት ጋር ለጋራ ግብ መቆም ያስፈልጋል።የሶማሌ ልዩ ፖሊስንም ሚና በዛው መተመንና በጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማስተካከል ተገቢ ነው።

ሌላው በአዲሱን አመራርና አመረሩን በውክልና ጦርነት እየተፈታተኑ ባሉት የፖለቲካ ቁማርተኞች መካከል ስለሚኖረው የወደፊት አቅጣጫ ፍንጭ ሰጪ በመሆኑ ነው። አንድም የግጭቱን ሜዳ በማጥበብ የውክልና “ጦርነት” ቀጠና የሚቀይር ሲሆን ወደፊት ያለውን የሽኩቻ ማእከል ወደ ሴረኞቹ ሜዳ ለመውሰድ ያግዛል። ይሄም የራሱ ጥቅሞች ቢኖሩትም ሴረኞቹን ተስፋ በማሳሳት ወደ ቀጥተኛ የፖለቲካ መስመር መግፋት አንዱ ሊሆን ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ በአዲሱ አመራርና በተቃራኒ ጎራ የተሰለፉት መካከል ያለውን ፍትጊያ ወደ አንድ አቅጣጫ የሚወስድ ይሆናል። ተቃራኒው ቡድን አሽከሮቹና የደገሰው የተራዘመ ግጭት በከሸፈ ቁጥር ወደ ዳር እየተገፋ ብቻውን መቅረቱ አይቀሬ ነው። በውጤቱም የጠሚው አመራር የስነልቦና የበላይነትን የሚያጠናክር ሲሆን በተቃራኒው የሴረኞቹን ስነልቦናና ተስፋና እንዲሁም የድጋፍ መሰረትን ያዳክማል። በዚህ አጋጣሚ ሴረኞቹን ከተደበቁበት ህዝብ ለመነጠል አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። ይህ ካልሆነና ክልሉን የመረጋጋቱ ስራ በተራዘመ ቁጥር አለመረጋጋት የሚፈጥርና አለመረጋጋቱም ወደ ሌሎች አካባቢዎች መስፋፋት ይችላል። የጠሚ አብይ አስተዳደርም ብዙ ኪሳራዊች ይደርስበታል።

የዘመቻው መልእክት

  • መሳሪያና ስልጣንን ተገን አድርጎ ወንጀል የሰራ ማንም ግለሰብም ሆነ ቡድን ከሕግ በላይ አለመሆኑን ያሳያል
  • ወንጀለኞች የትኛውም የፌደራል ክልል ውስጥ ለዘላለም ተደብቀው መኖር እንደማይችሉ
  • አዲሱ አመራር ትእግስት ፍራቻ አለመሆኑና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ህጋዊ ስልጣን ተጠቅሞ የሀገር ሰላምና ደህንነት ማስከበር እንደሚችል ያሳያል ወዘተ

ዘመቻው ለምን?

ዘመቻው በአስቸኳይ ማካሄድ ያስፈለገው በሶስት ምክንያቶች ንርው።

አንደኛው በአብዲ ኢሌይ እብደት ምክንያት በየቦታው ግጭት መቀጠሉ ነው። ልብ ሊባል የሚገባው ጦርነቱ በሶማሌና በኦሮሚያ መሬቶች ላይ ቢካሄድም የሁለቱ ህዝቦች ጦርነት ሳይሆን ከሁለቱም ያልሆኑ ሴረኞች በሌሎች ሜዳ ላይ የሚያካሄዱት ነው።

ሁለተኛው በክልሉ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ሁለንተናዊ የመብቶች ረገጣና አፈና ነው። ይሄን አብዲ ኢሌይን ቦታው ላይ አስቀምጦ ለመስማት እንኳ የሚሰቀጥጡ ረገጣዎችን ማስቆም አልተቻለም። በመሆኑም ሰላምና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ የሰውየው መወገድ መንገድ ጠራጊ ይሆናል።

ሶስተኛው በያቅጣጫው የሚነሱ የህዝብና ተቋማት ጩኸት በጠሚ አብይ አማራር ላይ ያሰደረው ጫና ነው። የኦሮሞና የሶማሌ የሀገር ሽማግሌዎች ፖለቲከኞች አክቲቪስቶች ዲያስፖራና ምሁራን ጩኸት መበርከቱና የማይታለፍ በመሆኑ ለዚህም አፋጣኝ መልስ መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ነው። በተጨማሪም የአለም አቀፍ ተቋማት ውትወታና ማስጠንቀቂያም ትልቅ ተጽእኖ ፈጥሯል።
ከሁሉ በላይ አስገዳጅና ወቅታዊ ምክንያት ግን በወያኔ ጀነራሎች የተቀነባብረ የመገብጠል ሴራ ለማክሽፍ ነው።

Gemechis D. Asfaw

One thought on “የመከላከያ ሰራዊት በሶማሌ ክልል እየወሰደ ያለው እርምጃ: ወሳኝነት ስጋቶች እና ምክንያቶች

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡