አብዲ ኢሌን ከስልጣን ማስወገድ የሚያስፈልገበት ሰባት (7) ምክንያቶች፡-

1ኛ፡- አብዲ ኢሌ የአዕምሮ ብስለትና የሰከነ አመለካከት የለውም!
በመጀመሪያ ደረጃ አብዲ ኢሌ የአንድ ክልል ፕረዜዳንት ለመሆን የሚያስችል የአዕምሮ ብስለት (ጤንነት) እና ህዝብን ለማስተዳደር የሚያስችል በቂ ግንዛቤ የለውም። በተደጋጋሚ ከሚያደርጋቸው ተግባራት ግለሰቡ ከፍተኛ የሆነ የስነ-ልቦና ችግር እንዳለበት መረዳት ይቻላል። እንዲህ ያለ ነገሮችን በሰከነ መልኩ መገንዘብ የማይችል ሰው ሕዝብን ለማስተዳደር የሚያስችል አቅምና ስብዕና የሌለው ግለሰብ በህዝብ ብዛት ከሀገሪቱ ሦስተኛ የሆነውን ክልል ሊያስተዳድር አይገባም።

2ኛ፡- የአብዲ ኢሌ ስልጣን ከብቃት ይልቅ በጦርነት የተገኘ ነው!
አብዲ ኢሌ ወደ ስልጣን የመጣው በክልሉ ሕዝብ ፍቃድና ምርጫ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ክልሉን የማስተዳደር ስልጣን የተሰጠው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ-አውጪ ግንባርን (ኦብነግ) ከሶማሌ ክልል በማስወጣት ረገድ ላበረከተው አስተዋፅዖ ከህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት የተሰጠው ገፀ-በረከት ነው። ስለዚህ አብዲ ኢሌ ወደ ስልጣን የመጣው በፖለቲካ አመራር እና ሕዝብ አስተዳደር ልምድና ዕውቀት ስላለው ሳይሆን ከኦብነግ አማፂያን ጋር በተደረገው ጦርነት አማካኝነት ነው።

3ኛ፡- የአብዲ ኢሌ ስልጣን ሕዝብ በመጨፍጨፍ የተሰጠ ሽልማት ነው!
አብዲ ኢሌ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስን በዋና አዛዥነት የመራው እ.አ.አ. ከ2007-2010 ዓ.ም ባሉት ሦስት አመታት ነው። በእነዚህ ሦስት አመታት የልዩ ፖሊስ አባላት በክልሉ ሕዝብ፣ በተለይ ደግሞ በኦጋዴን ሕዝብ ላይ እጅግ በጣም ዘግናኝ የሆነ ግፍና ጭፍጨፋን አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ወደ አከባቢው ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ወደ አከባቢው ለመላክ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጓል። ሆኖም ግን በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። አብዲ ኢሌ የኦጋዴንን ሕዝብ በመጨፍጨፍና በማሸበር ላበረከተው አስተዋፅዖ እ.አ.አ. በ2010 የክልሉ ፕረዜዳንት እንዲሆን ተደረገ።

4ኛ፡- አብዲ ኢሌ ከአሸባሪዎች በላይ አሸባሪ ነው!
አብዲ ኢሌ ልዩ ኃይል የሚመራው ልዩ ኃይል “በአሸባሪነት” የተፈረጀውን ኦብነግ ከሶማሌ ክልል ለማስወጣት የተጠቀመው የውጊያ ስልት “ከአሸባሪዎቹ በላይ አሸባሪ” መሆን ነው። የልዩ ፖሊሱ አባላት ከኦብነግ ታጣቂዎች በላይ በሕዝቡ ላይ ሽብርና ፍርሃት የሚፈጥሩ፣ እጅግ ዘግናኝ የሆነ በደልና ግፍ ፈፅመዋል። “የኦብነግ አባላት ናችሁ፣ ታጣቂዎችን ትደግፋለችሁ፥ ታስጠጋላችሁ፥…” ወዘተ በሚል የክልሉን ነዋሪ በተደጋጋሚ ሲያስሩት፥ ሲያሰቃዩትና ሲያሸብሩት ኦብነግ መጠጊያና መሸሺያ አሳጡት። አብዲ ኢሌ የክልሉ ፕረዜዳንት ከሆነ በኋላም እ.አ.አ. እስከ 2012 ድረስ ተመሳሳይ ግፍና በደል ሲፈፅም እንደነበር የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ይገልፃሉ። በዚህ ምክንያት ኦብነግ ከአብዛኛው አከባቢ ለቅቆ ለመውጣት ተገደደ። አብዲ ኢሌ ሲከተለው የነበረው የውጊያ ስልት አስመልክቶ “Human Rights Watch” ያቀረበው ዝርዝር ሪፖርት እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

5ኛ፡- ለሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ቀጥተኛ አደጋ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል!
እ.አ.አ. ከ2015 ጀምሮ በተለያዩ የኦሮሚያና አማራ አከባቢዎች አመፅና ተቃውሞ ሲቀሰቀስ የሶማሌ ልዩ ፖሊስ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ የኦሮሚያ አከባቢዎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት መፈፀም ጀመረ። የጥቃቱ ስልት በኦጋዴን ከነበረው ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው። የጥቃቱ ዓላማ በተለይ በኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን አመፅና ተቃውሞ በጉልበት ማፈንና ማዳፈን ነው። በሁለቱ ክልሎች አጎራባች አከባቢዎች በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት በመፈፀም፣ በተለይ የኦሮሞን ሕዝብ ከመጠን በላይ በማስጨነቅ የቄሮዎችን የመብትና ነፃነት ትግል ለማኮላሸት ጥረት አድርጓል። በዚህ ምክንያት አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሏል፣ በሺህ የሚቆጠሩ ለሞትና አካል ጉዳት ተዳርገዋል። በመሆኑም ለሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ቀጥተኛ አደጋ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል።

6ኛ፡- የአብዲ ኢሌ መገልገያዎችን በህዝብ አገልጋዮች ለመተካት ያስችላል!
አብዲ ኢሌ በዙሪያው የሰበሰባቸው ባለስልጣናት የክልሉን ሕዝብና መንግስት ለመምራት የሚያስችል አቅምና ብቃት የላቸውም። ለምሳሌ ቅዳሜ ዕለት አብዲ ኢሌ በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ የክልሉ ዋና ዋና ባለስልጣናት በፌደራል መንግስቱ ላይ ጦርነት ሲውጁ፣ በተለይ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ደግሞ የዘር ማጥፋት እንዲፈፀም በቪዲዮ ጥሪና ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር። አብዲ ኢሌ ስለተነካ ብቻ የክልሉን ሕዝብና መንግስት ወደ ጦርነት የእንዲገባ፣ በሌሎች ብሔር ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት እንዲፈፀም ጥሪ ማድረጋቸው የሚያሳየው እነዚህ ባለስልጣናት በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉት አብዲ ኢሌን ለማገልገል ወይም የእሱ አገልጋይ በመሆናቸው ብቻ እንደሆነ ነው። ስለዚህ አብዲ ኢሌ ከስልጣን ሲወገድ እነዚህም ባለስልጣናት አብረው ይወገዳሉ። በመሆኑም ለክልሉ ሕዝብ ተቆርቋሪና አገልጋይ የሆኑ ግለሰቦች ወደ አመራርነት እንዲመጡ ምቹ እድል ይፈጥራል። በአጠቃላይ የአብዲ ኢሌ መውረድ የእሱን መገልገያዎች በህዝብ አገልጋዮች ለመተካት ምቹ እድል ይፈጥራል!

7ኛ፡- የአብዲ ኢሌ ከስልጣን መውረድ የህወሓትን የእጅ አዙር አገዛዝ ማስወገድ ነው!

ከላይ ከተራ ቁጥር 1-5 በተገለፀው መሰረት የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ አመሰራረት እና የአብዲ ኢሌ ፕረዘዳንትነት በስተጀርባ የህወሓት ባለስልጣናት እና ጄኔራሎች እጅ አለበት። ላለፉት ሦስት አመታት በኦሮሚያ አዋሳኝ አከባቢዎች ላይ ጥቃት የፈፀመው በህወሓቶች ተላላኪነት እንደሆነ ይታወቃል። አሁንም ከፌደራሉ መንግስት ጋር ግጭት ውስጥ የገባበት እና ባለፉት ቀናት ክልሉን ለመገንጠል መንቀሳቀስ የጀመረው የህወሓቶችን ድጋፍና አለኝታነት መከታ በማድረግ ነው። በዚህ ረገድ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ ያወጣው የአቋም መግለጫ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። በአጠቃላይ ከልዩ ፖሊሱ አመሰራረት እስከ የአብዲ ኢሌ ፕረዘዳንትነት፣ ከኦጋዴን እስከ ምስራቅ ኦሮሚያ በሕዝብ ላይ የተፈፀመው ግፍና ጭፍጨፋ የህወሓት የእጅ አዙር አገዛዝ ውጤት ነው። በመሆኑም የአብዲ ኢሌ ከስልጣን መውረድ የህወሓትን የእጅ አዙር አገዛዝ ማስወገድ ነው። ይህ የእጅ አዙር አገዛዝ ለሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደማይጠቅም ላለፉት አስራ አንድ አመታት በተግባር ተረጋግጧል። ስለዚህ የህወሓትን የጥፋት እጅ መቁረጥ ለሁሉም ይበጃል።