በሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታ የተጠረጠሩት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መምሪያ አዛዥ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አባባ በሰኔ 16ቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተደረገው የድጋፍ ሰለፍ ላይ በተፈጸመው ቦንብ ፍንዳታ፣ በማሰተባበር፤ በመምራትና ለቦንብ ፍንዳታ የሚሳተፉ አከላትን በመመልመል የተጠረጠሩት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መምሪያ አዛዥ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተሰጠ።

መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የምስክር ቃል መቀበሉን፤የገንዘብ ድጋፍ መደረጉ ላይ ከፋይናንስ ተቋም ምላሽ ማመጣቱን በቦንቡ ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች የጉዳት መጠንን እና የሟቾችን አስከሬን ምርመራ ወጤት የሚገለጽ የህክምና ማስረጃ ማመጣቱን፣ የቦንቡ የቴክኒክ ውጤትን ማምጣቱን፣ የድምጽ ቅጂን በተመለከተ ከኢትዮ-ቴሌኮም ማስረጃ ማመጣቱን ተሳትፎ አላቸው የተባሉ ሌሎች በሃገረ ውስጥና በውጪ የሚኖሩ የሽብር ቡድን አካላትን መያዢያ ከፍርድ ቤት ማወጣቱን ለፍርድ ቤቱ አስታወቋል።

ቀሩኝ ያላቸውን ከሃገር ውጪ የሚገኙ ተጠርጣሪዎቸን ለመያዝ ከሃገራቱ ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን በመጥቀስ በቁጥጥር ስር ለማዋል የተስፋዬ ኡርጌ በርካታ ያፈሩት ሃብትን ምንጭ ለማጣራት፤ ከተቋማቸው በተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ ለመስበሰብ እና ሌሎች ቀሪ ምርመራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ፍርድቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪ ተስፋዬ ኡርጌ በጠበቃቸው አማካኝነት ደንበኛዬ ከተቋሙ ሰነድ ማውጣት አይችሉም በዋስ ተለቀው ምርመራው መቀጠል ይችላል ሲሉ የመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተቃውመዋል።

ፍርድቤቱ ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጡ የሚያደረሱት ተጽዕኖ ምንድነው ብሎ ለመርማሪ ፖሊስ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጠው መርማሪ ፖሊስ ምስክሮች ከተጠርጣሪው ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ስለሚችል ምስክሮቻችንን ሊያሸሹበን ይቸላሉ ከተቋማቸው ማስረጃ ስናመጣ የሰነድ ማስረጃው ያለው ከስራቸው ባሉ ሰራተኞች በመሆኑ የሰነድ ማስረጃው ሊጠፋ ይችላል።

በሃብት ምንጫቸው ለምናደረገው ማጣራት እንቅፋት ሊፈጥሩ ይችላሉ ሲል መርማሪ ፖሊስ ሊያደርሱት ስለሚችለው ተጽዕኖ የገለጸ ሲሆን ወንጀሉ ከባድና ውስብስብ በመሆኑ በዋስ ሊወጡ አይገባም ሲል ዋስትናውን ተቃውመዋል።

የሁለቱን ክርክር የተከታተለው ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን በማለፍ ለመረማሪ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ የሰባት ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

የፌዴራል መርማሪ ፖሊስ በዚሁ ቦንብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ ተሳትፎ ነበራቸው ተብለው ምርመራ ሲከናወንባቸው የነበሩት በነ በየነ ቡላና አብዲሳ መገርሳ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ ለአቃቢ ህግ አስረክቧል።

በፌዴራለ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮን በሚመለከተው ተረኛ 1ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት በየነ ቡላና አብዲሳ መገርሳ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ ለአቃቢ ህግ አስረክቧል።

ጠቅላይ አቃቢ ህግ በበኩሉ መዝገቡን ሐምሌ 27 መረከቡን በማስታወቅ የመርመራ መዝገቡ በምስልና በድምጽ የታገዘና በርካታ ውስብስብ የወንጀል አፈጻጸም የያዘ በመሆኑ መዝገቡን አይቶ የተናጠል ወንጀል ደርጊታቸውን በግልጽ ለፍርድ ቤቱ ለማቀረብ እና ክስ ለመመስረት የ15 ቀን ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ፍረድቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪ በየነ ቡላ በበኩሉ ከተያዝኩ አንድ ወር የሞላኝ እና ቤተሰቤ የተበተነ ሲሆን የዛሬ 10 ቀን ነው ቃሌን ፖሊስ የወሰደው በዚህ 10 ቀን ክስ ሊመሰረት ይችል ነበር ፍትህ ሊጓተት አይገባም ስለዚህ በዋስ ወጥቼ ጉዳዬን ልከታተል ሲል የአቃቢህግ ተጨማሪ ጊዜን በመቃወም የዋስትና ጥያቄውን አቅርቧል።

አብዲሳ መገርሳ በበኩሉ በጠበቃ አማካኝነት ዋስትና መብቱ እንዲፈቀድ ጠይቋል።

የዋስትና መብት ጥያቄውን የተቃወመው አቃቢ ህግ ጉዳዩ ውስብስብ ወንጀል እንደመሆኑ የሌሎች ተጠርጣረዎች መዝገብ ያለ በመሆኑ በዋስ ቢወጡ ምስክር ሊያሸሹብኝ ስለሚችሉ ዋስትናውን እቃወማለው ብሏል።

የሁለቱን ክርክር የተከታተለው ፍርድቤቱ የተጠርጣሪዎችን ዋስትና ጥያቄ በማለፍ ለአቃቢ ህግ ተጨማሪ ክስ መመስረቻ የ10 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪከ አዱኛ

ምንጭ፦ FBC