የዶ/ር አብይ ፍቅር ሞልቶ ፈሰሰ፣ ኤርትራን አቋርጦ ደቡብ ሱዳን ደረሰ!

ባለፈው ጠ/ሚ አብይ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ አንድ መምህር ስንቶቻችን የቋመጥንለት የመጠየቅ አድል አግኝቶ እንዲህ የሚል ሃሳብ ሰነዘረ፤ “ጠዋት ልጄን ወደዚህ እንደምመጣ ስነግረው ‘ዶ/ር አብይን እንወድሃለን’ በለህ ንገርልኝ አለኝ። በእርግጥ ልጄ ይወድሃል። እኔም እውድሃለሁ። ነገር ግን እንደ ልጄ ፍቅሬን በይፋ መግለፅ እፈራለሁ። ምክንያቱም መሪዎች በሕዝብ ሲወደዱ አምባገነን ይሆናሉ። የእኔ ስጋት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይወድሃል። ይህ በመሆኑ በአንድ በኩል ደስ ይለኛል። በሌላ ጎኑ ደግሞ አምባገነን እንዳትሆን የሚል ስጋት ያድርብኛል” ዶ/ር አብይ “ፍቅር ሲበዛ ሞልቶ ይፈሳል። ፍቅር ሲበዛ ከራስ አልፎ ለሌሎች ይተርፋል። ፍቅር ፍቅርን ይወልዳል እንጂ ወደ ጥላቻ አይቀየርም። እና…አይዞህ ስጋት አይግባህ!” በማለት ምላሽ ሰጡት።

ዶ/ር አብይ ሁለቱን የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ መሪዎች አዲስ አበባ ጠርተው ባነጋገሩበት ወቅት

ፌስቡክ ላይ ከፃፍኳቸው ፅሁፎች ሁሉ በጣም ተወዳጅ የሆነው ዶ/ር አብይ አንዳርጋቸው ፅጌን ከማስፈታት አልፎ ቤተ መንግስት ጠርተው ሲያናግሩት በማየቴ የተሰማኝን የገለፅኩበት ነው። በእርግጥ አንድ ወዳጄ ነው በውስጥ መስመር “ስዩም እስኪ ምንም ሳትደብቅ የተሰማህን ስሜት ፃፈው?” ሲለኝ ነው የፃፍኩት። ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት በቂም-በቀል ሰቀቀን በተሞላ ፖለቲካችን ላይ የፍቅርና ይቅርታ መዓት ሲያወርድበት ለአብዛኞቻችን ህልም ነበር የመሰለን። የዶ/ር አብይ ፍቅርና ይቅርታ ሞልቶ እየፈሰሰ አስመራን አቋርጦ አሜሪካ ደረሰ። ዶ/ር አብይ “ፍቅር ሲበዛ ከራስ አልፎ ለሌሎች ይተርፋል” እንዳሉት እንሆ የእሳቸው ፍቅርና ይቅርታ ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን አልፎ ለደቡብ ሱዳኖች ተርፏል።

የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ከካርቱሙ የሰላም ስምምነት በኋላ ለአማፂያኑ ሙሉ ምህረት ማድረጋቸው ይፋ ሲያደርጉ የሚያሳይ ምስል (ምንጭ፦ EBC)

ይህን እንድፅፍ ያነሳሳኝ “የደቡብ ሱዳን ፕረዜዳንት ለተቀናቃኞቻቸው ምህረት የሚሰጥ አዋጅ ይፋ አደረጉ” የሚለው የዜና ነው። በእርግጥ “ይህ አንዲሆን የዶ/ር አብይ ሚና ምንድነው?” የሚል ጥያቄ ልታነሱ ትችላላችሁ። ለዚህ ደግሞ ከዚህ ፅሁፍ ጋር የተያያዘውን የቪዲዮ ምስል ማየት ብቻ በቂ ነው። ዶ/ር አብይ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ መሪዎችን ልብ በፍቅርና ይቅርታ ሲሞላ ትመለከታላችሁ። እሱ የሞላው ፍቅርና ይቅርታ በደቡብ ሱዳን ሞልቶ ፈሰሰ። በሀገሪቱ ላይ ጥላቻን አድርቆ፣ ሰላምን ጸነሰ። አዎ…ፍቅር ሲበዛ ሞልቶ ይፈሳል፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች ይተርፋል እንጂ ወደ ጥላቻ አይቀየርም።