የመምህራን ቅጥርና ልማትን አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያና ያሉበት ክፍተቶች

ትምህርት ሚኒስቴር ከነሃሴ 07/2010 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመሩበት የመምህራን ምልመላ፣ ቅጥርና ልማት መመሪያ ማውጣቱን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ምልመላ፣ ቅጥርና ልማት በተጠቀሰው መመሪያ መሠረት መከናወን እንዳለበት ተገልጿል፡፡ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም መምህርና የድረገፃችን ፀሃፊ አቶ ገመቺስ አስፋው በአዲሱ መመሪያ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን እንደሚከተለው በዝርዝር አቅርቧል፡፡ (አዲሱን መመሪያ ይህን ማያያዣ (link) በመጫን ማውረድ ይቻላል)

  1. ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሪ የሆኑ መርሆችን ለማስፈጸምና አሰራሩን ስርዓት ባለዉ መልኩ ለመምራት መመሪያ ማዉጣት ተገቢ ነዉ፡፡ ሆኖም ግን በትምህርት ሚኒስቴርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የሚኖረዉ ግንኙነት ወደ አንድ ወገን ያዘነበለና አሰራሩን የተማከለ የማድረግ አዝማሚያ አዋጪ አይመስለኝም፡፡ የመመሪያዉ ይዘት በተወሰነ መልኩ ከላይ-ወደ ታች የአሰራር ዘይቤ አመላካት በመሆኑ የተቋማቱን አንጻራዊ ኦቶኖሚ (ነባራዊ ሁኔታዎችን በማየት የሚወስዱትን እርምጃ) ይገድባል፡፡
  2. መመሪያዉ በመስከረም ወር ባጠቃላይ የት/ርት ሮድ ማፕ ላይ ከሚደረገዉ የመምህርን ምክክር በኋላ ስራ ላይ ቢዉል የተሻለ ነበር፡፡ ከምክክሩ ጎን ለጎን በዚህም ጉዳይ ላይ መምህራኑ ቢመክሩና ዉጤቱን እንደ ግብዓት መጠቀም መመሪያዉን የተሻለ ያደርገዉ ነበር፡፡ ነገሩ “ከፈሰሱ ጋሪዉ ቀደመ” መሆኑ የተቋማቱና የመምህራኑ ድምጽ እንዳይሰማ የተደረገ ያስመስለዋል፡፡

3. ከተቀመጡት የቅጥር መስፈርቶች ዉስጥ ነባራዊ እዉነታን ያላገናዘቡ ይገኙበታል፡፡

አንደኛዉ ማሳያ-ለተቀጣሪዎች የተቀመጠዉ የCGPA ዉጤት መስፈርት ነዉ፡፡ ለምሳሌ-የአዳማ ሳ.ቴ.ዩ ባለፉት 4 አመታት ሲጠቀምበት በነበረዉ መስፈርት (ለባችለር 3.25፤ ለማስተርስ 3.5 ከሌሎቹ ተቋማት በተሻለ ጥቅማጥቅምና የሎኬሽን አድቫንቴጅ) እንኳ በቂ መምህራንን ከገበያዉ ማግኘት አልቻለም፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ የመቀጠሪያ ዉጤቱን ይበልጥ ወደ ላይ መስቀል በሰዉ ሀይል እጥረት የሚመጡ ችግሮችን ይበልጥ ሊያባብስ ይችላል፡፡ በተጨማሪም የትምህርት አሰጣጥ ባህል፣ የዉጤት አሰጣጥ ዘዴና አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ካልተሻሻለ በስተቀር በCGPA ላይ መንጠልጠሉ ዉጤታማ ያደርግም፡፡ ሁለተኛ ማሳያ- በክፍል 3 ስር በ3.1 እንደተመለከተዉ ከሆነ ለአንድ ስራ መደብ የአመልካቾች ቁጥር ከ10 በታች ከሆነ ቅጥሩ ተሰርዞ በድጋሚ ሁለት ጊዜ ማስታወቂያ እንዲወጣ ያስገድዳል፡፡ አሁን ባለዉ ልምድ ከጥቂት የትምህርት አይነቶች በስተቀር ለአንድ የስራ መደብ 10 አመልካች ማግኘት ህልም ነዉ፡፡ ይሄ በፍጹም ተቀባይነት የሌለዉ ነዉ፡፡ በተጨማሪም አንድ ተቋም ወሳኝ ክፍተቱን ለማሟላት ያስችል ዘንድ ልዩ ችሎታ/ልምድ ያላቸዉን አንድም ይሁን ሁለት መምህራን የመቅጠር መብት ለተቋሙ መስጠት ሲገባ ማገዱ ቅንነት አይደለም፡፡

4. በቁ.4.3 ስር ቀጣይ የትምህርት እድሎችና ሥልጠና አፈጻጸም በተመለከተ

ሀ) መምህራን የትምህርት ድረጃቸዉን ከፍ ወደሚያደርግ ሥልጠና ሲላኩ ማሟላት ካለባችዉ ተብሎ ከቀረቡት ዉስጥ ሰልጣኙ ሥልጠና ላይ ለቆየባችዉ እያንዳንዱ አመት ለእጥፍ አመታት አገልግሎች የመስጠት ግዴታ ያስቀምጣል፡፡ ለ) ሰልጣኙ ሥልጠና ላይ ሲቆይ ለሚወጣበት ወጪ በጠቅላላ የውል ግዴታ መግባትና ዋስ ማቅረብ ይኖርበታል ብሎ ደንግጓል፡፡

ይሁንና እነዚህ ሁለቱ ጉዳዮች በመለስ ዜናዊ ግዜ የነበሩ በኋላም የተሻሻሉና አሁንም ተመልሰዉ የመጡ ናችዉ፡፡ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እየተሸጋገረች ካለች ሀገር ቁመናና አስተሳሰብ ጋር አብሮ የሚራመድ ሳይሆን ጎታች ይመስላል፡፡ ለምሳሌ በሀ) ሰር “እጥፍ” የተደረገዉ የአገልግሎት ጊዜ ተሻሽሎ በግማሽ ወርዶ ነበር፡፡ ከዚህ በላይ ሁለቱም መምህራን ለስልጠና በሚሄዱበት ጊዜ ትልቅ እንቅፋቶች የነበሩ ናቸዉ፡፡ መመሪያዉ ይሄንን ከግንዛቤ ሳያስገባ ተጨማሪ ጫና ማሳደሩ የሚኒስትር መ/ቤቱን አካሄድ አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ እንዲሁም የችግሩ ምንጭ ከሚኒስትር መ/ቤቱ የአስተሳሰብ መርህ ነዉ፡፡ ይህ መርህ መብትንና የስኬት ምህዳርን ከማስፋት ይልቅ በግዴታና ማዕቀብ መጣል ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነዉ፡፡ ስለዚህ መመሪያዉ መምህራን ሲሰለጥኑ ያለባችዉን ችግር ከመፍታት ይልቅ አሳሪና ገዳቢ ይሆናል፡፡በሌላ አነጋገር መመሪያዉ ከመፍቀድ ይልቅ ክልከላ ላይ በማተኮሩ ምክንያት መምህራን ለስልጠና ሲሄዱና ሥልጠና ላይ ሲቆዩ በስኬት እንዲመለሱ ከማገዝና ከማበረታታት ወይም አዳጋች የሆኑትን ችግሮች ከመፍታት ይልቅ የሚያባብሱ ናቸው፡፡ ከዚህ ሌላ መመሪያዉ ሠልጣኞችን ያላማከለ/ያላማከረ በመሆኑ፣ ሠልጣኞች ትምህርታቸዉን በስኬት እንዲወጡ ከማደላደልና ከማመቻቸት ይልቅ የተለመደዉ ግዴታን የመቸርቸር ጥረት አካል ነዉ፡፡

በሌላ በኩል አንዱ የመመሪያዉ ድክመት ምሩቃን ከከፍተኛ ት/ርት ተቋማት ወደ ሌሎች (በተለይ መንግስታዊ) ተቋማት እንዲፈልሱ የሚያደርጉትን ምክንያቶች ከመሰረቱ ከመፍታት ይልቅ ማዕቀብ መጣል ሲሆን ዉሳኔዉ ምሁራዊና ዲሞክራሲያዊ ካለመሆኑም በላይ ካሁኑ የመንግስት ገጽታ ጋር የማይመሳሰልና፤ ባለፉት 27 ዓመታት ከነበረዉ አሰራርም የባሰ ጨቋኝ ነዉ፡፡

  1. በመጨረሻም በ1.3 ስር መመሪያዉ ተፈጻሚነት ለሚኒስትር መ/ቤቱ ተጠሪ ተቋማት ነዉ ብሎ ሲያበቃ በሸኚ ደብዳቤዉ ላይ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ተጠሪ የሆኑትን ሁለት ተቋማት፥ የአዳማና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኑቨርሲቲዎችን ማካተቱም አስገራሚ ነዉ፡፡

3 thoughts on “የመምህራን ቅጥርና ልማትን አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያና ያሉበት ክፍተቶች

  1. CGPA ን በተመለከተ 3.5 መብለጡ በጣም የተጋነነ ነው፡፡ የሌሎች ሀሳብ ተካቶበት እንደገና መታየት አለበት ባይ ነኝ፡፡ የተማሪው ብቁ መሆንና ያለመሆን ሳይሆን መውደቅና ማለፍ በመምህሩ ጫንቃ ላይ መጣሉ ሁላችንም የምናውቀው ሀቅ ነው፡፡ ስለሆነም የተቀጣረውን በቃት CGPA ሙሉ በሙሉ ላይለካው ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡መታየት ያለበት ትላቁ ችግር ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎች ያለው የCGPA አሰጣጥ ልዪነት ነው፡፡ ለምሳሌ ሀዋሳና በሀርማያ ዩንቨርስቲዎች መካከል ያለውን ልዩነት መመልከት ይቻላል፡፡ በማስተር ሌቨል የሀሩማያ 4.00 ነጥብ እና የሀዋሳ 3.75 እኩል ናቸው፡፡ ሀዋሳ A+=>95፤ A=>90-95; B+ = 85-90; B=75-80 ; B- =75-80 በሀሩማያ A+ >90; A= 85-90 ; B+ = 80-85; B = 75-80; B- =70-75:: የአምስት ማርክ ልዩነት በአንድ ሀገር ላይ ያለምንም ምክኒት አነዝህ ጎላ ያሉ ልዩነቶች ባሉበት አንዴት ይቻላል፡፡

    Like

  2. እንደዚህ መሆኑ በጣም ያሳዝናል ማስተርስ ልቭል ላይ 3.75 ማምጣት ከባድ ነው እንደገና ሊታይ ይገባል ። እኔ ለምሳሌ በአንድ በአገራችን ውስጥ በሚገኝ ዩንቨርሲቲ ተወዳድሪ የመመዘኛ ፈተናውን ወስጀ ማለፌ ተነግሮኝ ከዚያ አዲስ መስፈርት ከትምህርት ሚኒስቴር መጥቷል ተብሎ አግሪመንት ልሞላ ስል ታግዷል ተብያለሁ ። በጣም ያበሳጫል! !

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡