የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ሀይል ማመንጫ የማመንጨት አቅሙ ከ50 ሜጋ ዋት ወደ 25 ሜጋ ዋት ዝቅ ብሏል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 11፣2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ሀይል ማመንጫ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ለግንባታ ወጪ ተደርጎበት ከሁለት ዓመታት መዘግየት በኋላ ግንባታው ተጠናቆ በመጪው እሁድ ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው የደረቅ ቆሻሻ ሀይል ማመንጫ ከግንባታ መጓተት ችግር በተጨማሪ ያመነጫል ተብሎ ከታቀደው 50 ሜጋ ዋት በግማሽ በመቀነስ ወደ 25 ሜጋ ዋት ዝቅ ማለቱ ጥያቄን አስነስቷል።

የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አዜብ አስናቀ፥ ሜጋ ዋቱ 50ም ሆነ 25 ማምረቱ አሳሳቢ እንዳልሆነና የሃይል ማመንጨት አቅም ልዩነት በአመታዊ ምርቱ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ እንደሌለ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቀዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች በበኩላቸው በቀን 50 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የሀይል ፕሮጀክት 25 ሜጋ ዋት ከሚያመነጭ ፕሮጀክት ጋር አመታዊ የሃይል መጠኑ አንድ ዓይነት ሊሆን አይችልም በማለት የተቋሙን ውሳኔ ተችተዋል።

ሆኖም በካምብሪጅ ኢንዱስትሪ ስራ ተቋራጭ ግንባታው ሲከናወን የቆየው የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ሀይል ማመንጫ ለ50 ሜጋ ዋት የሀይል ማመንጫ የተመደበለትም በጀት የተጠቀመ ቢሆንም ከ25 ሜጋ ዋት በላይ ሀይል የማምረት አቅም እንደሌለው ታውቋል።

የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ሀይል ማመንጫ በተያዘለት በእቅዱ መሰረት 50 ሜጋ ዋት ሀይል ማመንጨት እንደማይችል በተረጋገጠበት ወቅት ከግንባታው ተቋራጭ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበረ ታውቋል።

በዚህም ተቋሙ ካምብሪጅ ኢንዱስትሪ ስራ ተቋራጭ ተጠያቂ ለማድረግ ጥረት የተደረገ ቢሆንም፥ ተቋራጩ የሀይል ማመንጨት አቅም ክፍተቱን ትራንስፎርመር በማቅረብ እንዲክስ ከስምምነት እንደተደረሰ ነው የታወቀው።

በመሆኑም ሁለቱ አካላት 50 ሜጋ ዋት የነበረው 25 እንዲሆን ስምምነቱን የፈፀሙ ሲሆን፥ ኩባንያው ደግሞ ተጨማሪ ትራንስፎርመር እንዲያቀርብ በማድረግ የፕሮጀክቱ ግንባታ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል።

ችግሩን በስምምነት ከመፍታት ይልቅ ለምን በህግ እንዲታይ አልተደረም በሚል ለዋና ስራ አስፈፃሚዋ በቀረበላቸው ጥያቄ፥ ጉዳዩ በህግ እንዲታይ ቢደረግም ከተቋራጩ ጋር የተገባው ኮንትራት ግልፅ እንዳልነበረ ገልፀዋል።

By ኤፍሬም ምትኩ

On Aug 17, 2018 101
Source: FBC