“ማህበራዊ ሚዲያዎችን መቆጣጠር ያስፈልጋል” የሚሉ ነፃነትን ሳያውቁ ጭቆናን የሚናፍቁ ናቸው!

ባለፈው የኤልቲቪ ”LTV” አዘጋጅ በማህበራዊ ሚዲየዎች ላይ በሚያተኩር የውይይት ፕሮግራም ላይ በተወያይነት እንድገኝ ጠይቃኝ ነበር። ነገር ግን በዕለቱ ወደ ወሊሶ እየተመለስኩ ስለነበር በፕሮግራሙ ላይ መገኘት እንደማልችል ነገርኳት። ዛሬ ኢቲቪ (ETV/EBC) “በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች … ለምናምን ቅብርጥስ ምክንያት እየሆኑ ነው” በሚል ይዞት የወጣውን ዘገባ በጨረፍታ አይቼ አለፍኩት። ከዚህ በተጨማሪ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሆነ በአካል የሚያዉቁኝ ወዳጆቼ “አሁንስ ይሄ ፌስቡክ የሚባል ነገር ለተወሰነ ግዜ ቢዘጋ ጥሩ ነበር” እያሉ ሲወተዉቱ ታዝቤያለሁ።

ባለፈው አመት የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ የአዲስ አበባ ወጣቶች ከአንድ ቅጥር ግቢ አጥር ስር ተጠግተው “Wi-Fi” ሲጠቀሙ የሚያሳይ ፎቶ፡፡ ምንጭ፦ Addis Fortune Newspaper

ለመሆኑ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ማዕቀብና እገዳ ስለማድረግ የሚወራበት ምክንያት ምንድነው? በእውነት በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ “የተሳሳቱ” መረጃዎች በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ለሚከሰቱ ግጭትና ብጥብጥ መንስዔ ናቸው? በኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት እና የማህበራዊ ሚዲያዎች አጠቃቀም ላይ የሚደረግ ቁጥጥርስ ችግሩን በዘላቂነት መቅረፍ ያስችላል? ወደፊትስ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ያደርጋል? እነዚህን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ በቅድሚያ ጥያቄዎቹ የተመሰረቱበትን እሳቤ በጥሞና ማጤን ያስፈልጋል።

በመጀመሪያ ደረጃ ዛሬ ከማህበራዊ ሚዲያዎች ፋይዳና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚነሱት ጥያቄዎች ትላንት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ በኃይል ለማፈንና ለማዳፈን ሲታትር ከነበረው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ይፋዊ አቋም ጋር አንድና ተመሳሳይ ናቸው። ምክንያቱም ዛሬ የሚነሱት ጥያቄዎች እና ትላንት የነበረው አቋም በአንድ ዓይነት እሳቤ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የቀድሞ ጠ/ሚ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በጉዳዩ ዙሪያ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ያደረጉትን ንግግር መጥቀስ በቂ ነው፡-

“Social media offered a platform to enhance popular participation, but misinformation could go viral and mislead, especially the youth. It had empowered extremists to exploit genuine concerns and spread messages of hate.” H.E. Mr Hailemariam Dessalegn, General assembly of the United Nations, General Debate of the 71st Session.

ከላይ ከተጠቀሰው ንግግር ውስጥ፤ “misinformation” (የተሳሳተ መረጃ) እና “mislead” (ማሳሳት) የሚሉትን ቃላት እንደ ማሳያ በመውሰድ ከማህበራዊ ሚዲያዎች ፋይዳ እና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ትላንት የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ሲያራምድ የነበረው አቋም እና ዛሬ የሚነሱት ጥያቄዎች በተሳሳተ እሳቤና ግንዛቤ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል። የህወሓት/ኢህአዴግ አቋም ሆነ ዛሬ የሚነሱት ጥያቄዎች “በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት የሚለቀቁ ‘የተሳሳቱ’ መረጃዎች ዜጎችን ‘ያሳስታሉ’” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

በመሰረቱ “በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ የተሳሳቱ መረጃዎች ወጣቶችን ወደ ተሳሳቱ ተግባራት (ድርጊቶች) ይመራሉ (mislead)” የሚለው እሳቤ ስህተት ነው። እንደ “John Stuart Mill” አገላለፅ፣ ሰዎች የተሰጣቸውን መረጃ ትክክለኝነት ሳያረጋግጡ እንደ መጣላቸው ተቀብለው ተግባራዊ አያደርጉም። ከዚያ ይልቅ የመረጃን ትክክለኝነት ማጣራትና ማረጋገጥ መረጃውን መረጃውን ተቀብሎ ተግባራዊ ከማድረግ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው፡-

“…the usefulness of an opinion is itself matter of opinion: as disputable, as open to discussion, and requiring discussion as much as the opinion itself. The truth of an opinion is part of its utility. Those who are on the side of received opinions never fail to take all possible advantage of this plea; you do not find them handling the question of utility as if it could be completely abstracted from that of truth: on the contrary, it is, above all, because their doctrine is “the truth,” that the knowledge or the belief of it is held to be so indispensable.” John Stuart Mill, On Liberty, Page 18.

በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚለቀቁ መረጃዎች ላይ መንግስት ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርግ መፍቀድ የተሳሳቱ መረጃዎች እንዳይታረሙ፣ ዜጎች ከተሳሳተ ተግባር እንዳይታቀቡ የሚያደርግ ነው። ምክንያቱም “ለሃጢያን የመጣ እርግማን ለፃድቃን ይተርፋል” እንደሚባለው ሁሉ ለስህተት የመጣ ቁጥጥር ለእውነት ይተርፋል። በመሆኑም የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት በተለይ ከመንግስት ፋላጎትና ጥቅም አንፃር “ሰህተት” የሆኑ ወይም የሚመስሉ ነገር ግን በተጨባጭ ትክክልና ለብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች ይገደባሉ። ይህ ትክክለኛ መረጃ ለህዝቡ እንዳይደርስ ከማድረጉም በላይ የተሳሳቱ መረጃዎች እንዳይታረሙ እቅፋት ይሆናል። ትክክለኛ መረጃን በመገደብ ዜጎች የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና ከተሳሳቱ ተግባራት እንዳይታቀቡ ያደርጋል።

በመጨረሻም “በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት የሚለቀቁ ‘የተሳሳቱ’ መረጃዎች ዜጎችን ‘ያሳስታሉ’” የሚለው እሳቤ “በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚለቀቁ የተሳሳቱ መረጃዎች ዜጎች እንዳይሳሳቱ መንግስት ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል” ወደሚል ድምዳሜ ይወስዳል። ይህ ደግሞ በተራው “በፍፁም ትክክለኝነት” (infallibility) አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ የጨቋኞችና ጭቆና መፈልፈያ ቋት ነው። “በፍፁም ትክክለኝነት” እሳቤ ላይ በተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ውስጥ፤ እውነትን መጠየቅና ማወቅ ጥፋት፣ የተለየ ነገር መናገርና መፃፍ ወንጀል ይሆናል። ስለዚህ የተሳሳተ መረጃ በመልቀቅ ዜጎችን ያሳስታሉ በሚል ስጋት መንግስት ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዲቆጣጠር መፍቀድ ራስን ለጭቆና እና ጨቋኞች አሳልፎ እንደ መስጠት ነው።

በአጠቃላይ ከማህበራዊ ሚዲያዎች ፋይዳና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ሰሞኑን የሚነሱት ጥያቄዎች ላለፉት 27 አመታት በራሳችን ለመንደን የተላመድነው አፈና ተመልሶ እንዲመጣ መጠየቅ ነው። በዚህ ረገድ መንግስት ቁጥጥርና ክትትል እንዲያደርግ መጠየቅ ከሃሳብና አመለካከት ነፃነት ይልቅ የኖርንበትን ባርነትና አፈና እንደ መናፈቅ ነው። ባለፉት ሦስት አመታት ብቻ ብዙዎች የታገሉለትን ነፃነት በሦስት ወር በቃኝ ብሎ እንዲገደብ መጠየቅ የቀድሞ ጭቆና ተመልሶ እንዲመጣ መሻት ነው። ነፃነትን ማወቅ፣ መግራትና መምራት እንጂ ባርነትና ጭቆናን መመኘት በምንም አግባብ ተቀባይነት የለውም።