“የቻይና ጅብ”- ክፍል 1: አሜሪካና ቻይና ጅቡቲ ውስጥ ምን እየሰሩ ነው? (Geopolitics)

1፡ የአሜሪካ ሃያልነት ከጃፓን እስከ ቻይና

ላለፉት አንድ መቶ አመታት አሜሪካ የዓለም ልዕለ-ሃያል ሀገር መሆኗር እርግጥ ነው። የአሜሪካ ሃያልነት ግን ያለ ተቀናቃኝ በብቸኝነት የዘለቀ አይደለም። ከዚያ ይልቅ በየግዜው ከሚመጡ ተቀናቃኝ ሀገራትና ቡድኖች ጋር ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጦርነት ውስጥ ገብታለች። ስለዚህ የአሜሪካ ሃያልነት እነዚህን ጦርነቶች በአሸናፊነት በማጠናቀቅ ላይ የተመሰረተ ነው። ባለፉት መቶ አመታት ከአሜሪካን ጋር የሃያልነት ትንቅንቅ ውስጥ ከገቡት ሃይሎች መካከል የመጀመሪያው ከ1930ዎቹ ጀምሮ ከጃፓን ጋር የተደረገው ነው። በዘመኑ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተካሄደው ትንቅንቅ በመጨረሻ ጃፓንን ለኒኩለር ቦንብ ዳርጓታል። ይህን ተከትሎ ደግሞ አሜሪካ ከሶቬት ህብረት ሩሲያ ጋር የሃያልነት ትንቅንቅ ውስጥ ገባች። የሶቬት ህብረት ተቀናቃኝነት እ.አ.አ. በ1989 ዓ.ም ከጀርመን ግንብ ጋራ አብሮ ወደቀ።

ከዚያ በመቀጠል አሜሪካን በግሎባላይዜሽን ስም በዓለም ሀገራት ላይ እንዳሻት ስትፈነጭ ሀገርና ድንበር የሌለው ተቀናቃኝ ኃይል የመጣ ሲሆን እሱም “ሽብርተኝነት” ይባላል። በተለይ በኒውዮርክ መንትያ ህንፃዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የአሜሪካን መንግስት ዓለም-አቀፉን የፀረ-ሽብር ዘመቻ አወጀ። “ከእኔ ጎን ያልቆሙ የአሸባሪዎች ደጋፊ ናቸው!” በሚል በዋናነት ምስራቅና ሰሜን አፍሪካን፣ ምዕራብና ደቡባዊ አውሮፓን፣ መካከለኛው ምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ኢሲያ ሀገራትን ማተራመስ ጀመሩ። አሜሪካ የምትከተለው የውጪ ፖሊሲና ለደሃና ታዳጊ አገራት የምታደርገው ድጋፍና ትብብር በዋናነት ከዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ዘመቻ ጋር የተቆራኘ ሆነ። አሜሪካ ከፍተኛ እርዳታ የምትሰጣቸውን ሀገራት እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

ከላይ በምስሉ ላይ እንደሚታየው ከአሜሪካ ከፍተኛ እርዳታ የሚያገኙት ሀገራት ዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ዘመቻ በስፋት በሚካሄድበት የዓለም ክፍል ነው። ለምሳሌ ኢራቅና አፍጋኒስታን በቀጥታ በአሜሪካ ጦር ወረራ የተፈፀመባቸው ናቸው፣ እስራኤል በፍልስጤሞች ላይ በምትፈፅመው ግፍና በደል በመካከለኛው ምስራቅ ሽብርተኝነት እንዲፈጠርና በመላው ዓለም እንዲስፋፋ አድርጋለች፣ ግብፅ፥ ጆርዳን፥ ሲሪያና ፓኪስታን የሽብርተኞች መፈልፈያ ቋት ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ፥ ኬኒያና ኡጋንዳ ደግሞ በዓለም አቀፉ የፀረ-ሽብር ጦርነት የአሜሪካ አጋሮች ናቸው። በአጠቃላይ የአሜሪካ ወታደራዊና ዴፕሎማሲያዊ ግንኙነት በዋናነት በሽብርተኞችና ሽብርተኝነት ላይ ብቻ ያጠነጠነ ነበር ማለት ይቻላል።

2፡ የቻይና ሃያልነት እና ስልት

አሜሪካ ከሽብርተኞች የተቃጣባትን ጥቃት ለመመከት በምትሯሯጥበት ወቅት ግን ሌላ ተቀናቃኝ ኃይል ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ አቅሙን አሳድጎ ከአሜሪካን ጋር ጫማ መለካካት ጀመረ። ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ጃፓን፣ ሶቬት ሩሲያ እና ሽብርተኝነት ቀጥሎ የአሜሪካንን ልዕለ-ሃያልነት መቀናቀን የጀመረው ሃያል ሀገር “ቻይና” ይባላል። ቻይና በዓለም ሀገራት ላይ በወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ስር የምታሳርፈው ከመሰረተ ልማት ግንባታና የብድር አሰጣጥ፣ እንዲሁም በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት ነው። ቻይና ይህን ፖሊሲ ተግባራዊ ባደረገችበት ወቅት የቀድሞ የዝምባብዌ ፕረዜዳንት ሮበርት ሙጋቤ “We turn our face to east where the sun rises, give our back to the west where the sun sets” ማለታቸው ይነገራል።

በዚህ መሰረት እንደ ዓለም-አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF)፣ የዓለም ባንክ (World Bank) እና ምዕራባዊያን ሀገራት ለሚያስቀምጧቸው ፍ መስፈርቶች ተገዢ መሆን የማይሹ፣ እንዲሁም በውስጥ ጉዳዮቻቸው ጣልቃ-ገብነት አጥብቀው የሚቃወሙ ጨቋኝና አምባገነን መንግስታት ያሏቸው ነገር ግን ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት ፍላጎት ያላቸው ደሃ ሀገራት በቀላሉ በቻይና ተፅዕኖ ስር ይወድቃሉ። በዚህ መልኩ በቻይና ተፅዕኖ ስር እየወደቁ ያሉት ሀገራት አሜሪካ በዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ዘመቻ የምታተራምሳቸው የምስራቅና ሰሜን አፍሪካ፣ ምዕራብና ደቡባዊ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና የደቡብ ምስራቅ ኢሲያ ሀገራት ናቸው።

ቻይና እነዚህን ሀገራት በተፅዕኖዋ ስር ለማድረግ የተነሳቸው “One Belt, One Road” በሚል በጥንታዊ ቻይና ስልጣኔ የነበረውን ዓለም-አቀፍ የንግድ መስመር መልሶ በመዘርጋት ነው። ይህ የንግድ መስመር “የሀር መንገድ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን ከቻይናዋ ዚያን (Xi’an) ከተማ ተነስቶ በካዛኪስታን፣ ኢራንና ቱርክ አድርጎ ሩሲያ ሞስኮ ከደረሰ በኋላ በጀርመንና ቤልጂዬም በኩል አድርጎ የኢጣሊያን ቬኒስ ከተማ ይደርሳል። ይህ የየብስ (መሬት) መንገድ የሚገነባው “Silk Road Economic Belt” በሚባል የግንባታ ፕሮጀክት ነው። ከኢጣሊያኗ ቬኒስ ከተማ ጀምሮ ደግሞ በግሪክ፣ ግብፅ፣ ጅቡቲና ኬኒያ አድርጎ ወደ ኢሲያ በመሻገር በሲሪላንካ፣ ህንድ፣ ማሌዢያና ቬትናም በኩል አድርጎ የቻይናዋ “Guangzhou” ከተማ ይደርሳል። ይህን የባህር ላይ የንግድ መስመር እውን ለማድረግ ደግሞ “Maritime Silk Road Initiative” የተባለ ፕሮጀክት ተግባራዊ ተደርጓል። ከታች ያለው ምስል ቻይና “One Belt, One Road” በሚል የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ወታደራዊ ተፅዕኖ ለማሳረፍ የምትንቀሳቀስበትን የዓለም ክፍል ያሳያል።

ከላይ በተጠቀሱት የየብስና የባህር ላይ የንግድ መስመር 68 ሀገራትን ያካትታል። ከእነዚህ ሀገራት ውስጥ 14 ሀገራት በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኢሲያ፣ 13 ሀገራት በመካከለኛውና ደቡብ ኢሲያ፣ 24 ሀገራት በአውሮፓና ዩሮኢዥያ፣ እንዲሁም 17 ሀገራት ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ የሚገኙ ናቸው። በመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ከሚገኙት 17 ሀገራት የሚከተሉት ናቸው። እነሱም፡- ባህሬን፣ ጅቡቲ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ እስራኤል፣ ጆርዳን፣ ኬኒያ፣ ኩዌት፣ ሌባነን፣ ኦማን፣ ኳታር፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ሲሪያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜራት እና የመን ናቸው።

3፡ የቻይና የዕዳ ጫና

በቻይና የሀር ንግድ መስመር ላይ ያሉት 68 ሀገራት አመታዊ የምርት መጠን (GDP) በድምሩ $25 ትሪሊዮን ዶላር ነው። ነገር ግን፣ ከ25 ትሪሊዮን ዶላር ውስጥ 45%ቱ የቻይና ድርሻ አመታዊ የምርት መጠን ነው። ስለዚህ የተቀሩት ሀገራት በቻይና የሀር ቀበቶ (Silk Belt) ተጠፍንገው የሚታሰሩ ናቸው። አብዛኞቹ ሀገራት ቻይና በምትሰጠው ብድር የዕዳ ጫና አለባቸው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 23 ሀገራት በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ የሚገኙ ናቸው። በክፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ካሉት ሀገራት፤ 3 ሀገራት በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኢሲያ፣ 7 ሀገራት በመካከለኛውና ደቡብ ኢሲያ፣ 6 ሀገራት በአውሮፓና ዩሮኢዥያ፣ እንዲሁም 7 ሀገራት ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ የሚገኙ ናቸው።

“Center for Global Development” የተባለ ድርጅት በሰራው ጥናት ከላይ የተጠቀሱት 23 ሀገራት የቻይና የሀር መስመርን ለመዘርጋት ከመደበው ገንዘብ ተጨማሪ ብድር የሚወስዱ ከሆነ የዕዳ ጫናው ሉዓላዊነታቸውን ሊያሳጣ የሚቻል አደጋ ያስከትላል። ቻይና ብድር ምክንያት ሉዓላዊነታቸው አደጋ ላይ የወደቀ የመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ሀገራት የሚከተሉት ናቸው፡- ጅቡቲ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራቅ፣ ጆርዳን፣ ኬኒያ እና ሌባኖን ናቸው። ከላይ የተጠቀሰው ተቋም ባደረገው ጥናት መሰረት ከላይ ከተጠቀሱት ሀገራት መካከል ከቻይና በተጣለባት የዕዳ ጫና ምክንያት በሉዓላዊነቷ ላይ ከፍተኛ ስጋትና አደጋ የተጋረጠባት ሀገር ጅቡቲ ናት። ከጅቡቲ በመቀጠል ኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ግብፅ ከቻይና በተሰጠ ብድር ምክንያት በተፈጠረ የዕዳ ጫና ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ስለዚህ የቻይና መንግስት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመግፈፍ ያቆበቆበ የዕዳ ጅብ ነው።

በዓለም ልዕለ-ሃያል ለመሆን በአሜሪካ እና ቻይና መካከል የሚደረገው ትንቅንቅ የጀመረው ጅቡቲ ላይ ነው። ጅቡቲ በአሜሪካና ቻይና መካከል ስትራቴጂካዊ ውጊያ የሚካሄድባት የጦር አውድማ ናት። ሁለቱ የዓለም ሃያላን መንግስታት ፍልሚያ የገጠሙት በኢትዮጵያ አፍንጫ ላይ ነው። ሁለቱ ሀገራት ግብግብ ሲገጥሙ ኢትዮጵያ ያስነጥሳታል። ምክንያቱም ጅቡቲ ላይ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ በወታደራዊ የጦር ሰፈር ጭምር የተደገፈ ነው። ከታች በምስሉ ላይ እንደሚታየው ጅቡቲን በምታክል ትንሽ ሀገር ላይ ከፈረንሳይና ቻፓን በተጨማሪ የአሜሪካና ቻይና የጦር ሰፈር ማዶ-ለማዶ ተገንብቷል። በሁለቱ ሃያላን መንግስት መካከል የሚደረገው ፍጥጫ በኢትዮጵያ፣ አፍሪካ፣ ብሎም የዓለም ፖለቲካ ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል የሚለውን በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን።

ማጣቀሻዎች(በከፊል)