በመቀሌ የታገቱት ‹‹ፌዴራሎች›› እና ‹‹ፌዴራሊዝም››

በቢኒያም መንበረወርቅ

የፌዴራል መንግስቱ ሥልጣን በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ብቻ ታጥሮ የሚቀር፤ ከዛ ውጭ ባሉት የአገሪቱ ክፍሎች ያለው ተሳትፎ ግን በክልሎች በጎፍቃድ ላይ የሚመሰረት አድርጎ የሚያስብ ሰው ቁጥር በርከት ያለ ነው፡፡ ፌዴራል መንግሥት ማለት አዲስ አበባና ድሬዳዋ ብቻ የሚመስለውም ሰው እንዲሁ ትንሽ አይደለም፡፡ እውነታው ግን በፍጹም ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የፌዴራል መንግስት (የጋራው መንግሥት) እና የክልል መንግሥታት መካከል ያለው ክፍፍል ሥልጣንን እንጅ መልካምድርን መሠረት ያደረገ አይደለም፡፡ የፌዴራሉ መንግስት በሕገ-መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን የሚያወጣቸው ሕጎችና መመሪያዎች ተግባራዊነታቸው በመላው ኢትዮጵያና በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ ነው፡፡ የፌዴራሉ መንግስት የሚያስተዳድራቸው የተለዩ ፌዴራል ዜጎች የሉትም፡፡ የፌዴራሉ መንግስት ዜጎች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በተሰጣቸው ስልጣን የሚያስተዳድሩዋቸው ተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ (Assefa, 2007)

በቀላል አገላለጽ የዜጎች የተወሰነው ጉዳያቸውን የሚያስተዳድረው የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ ሲሆን ሌላው ደግሞ በክልሉ መንግሥት የሚገዛ ነው የሚሆነው፡፡ ለምሣሌ ያህል የፌዴራሉ መንግሥት ጥላ ስር የሚወድቁ የወንጀል ዓይነቶች (አንድ የሀገር መክዳት ወንጀል የተጠረጠረ ሰው ላይ (ወንጀሉ እንዲያ ከሆነ)) ፍርድ የመስጠት መብት የፌዴራሉ መንግሥት ፍርድ ቤቶች ነው የሚሆነው በውክልና ለክልሎች ካልተሰጠ በስተቀር፡፡ መቀሌ የሚገኝ የፌዴራሉ መንግስት አውሮፕላን ማረፊያ፣ ሆስፒታልና ዩኒቨርሲቲ በጀት የሚመድብለትም ሆነ የሚያስተዳድረው አለቃ የሚመርጥለትም (አመራረጡን የሚወሰነው) የፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ የአንድ የባህርዳር ተማሪን የአሥረኛና የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ፈተናን የሚያወጣውና የሚመዝነው የፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱን በመላው ኢትዮጵያ የሚያሰማራውና የሚያሰፍረው የፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ በአዋሳ ዱቄት ፋብሪካ ሠራተኛና አሠሪ መካከል አለመግባባት የሚዳኘው የፌዴራሉ መንግሥት ፓርላማ ባወጣው የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ነው፡፡ አውራ ጎዳናዎችን የሚሠራውና በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ቆንስላ ጽ/ቤት ወልዲያ ላይ መክፈት ቢከጅል በመሠረቱ ፍቃድ የሚሰጠው የፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ የባህርዳሩን ተማሪ የስምንተኛ ክፍል ፈተና የሚያወጣውና የሚመዝነው፤ የገበሬውን የመሬት ግብር የሚወስነው፣ መጋቢና የገጠር መንገዶችን የሚሠራው የክልል መንግሥት ነው፡፡

የአሉላ አባነጋ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ መቀሌ

በአንዳንድ የፌዴራል መንግሥታት (በእኛ አገር የሕግ-አውጭው የፌዴራልና የክልል ተብሎ በግልጽ እንደተቀመጠው) አስፈጻሚው የክልልና የፌዴራል ተብሎ ከማዕከል እስከ ወረዳ ጎን ለጎን በየስልጣኑ የሚደራጅ ነው፡፡ የፌዴራል አስፈጻሚ ተቋማት ዋና ከተማ ላይ ተንጠለጥለው አይቀሩም ማለት ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች የክልል አስፈጻሚ አካላት የፌዴራሉን መንግሥት ሕግና ፖሊሲዎችን ደርበው ይሠራሉ፡፡ ፍርድ ቤቶችም እንደዛው፡፡ በኢትዮጵያ ጉምሩክ፣ የማኅበራዊ ዋስትና፣ መብራት ኃይል፣ ውኃና ፍሳሽና ኢሚግሬሽንን የመሰሉ የፌዴራል ተቋማት የራሳቸው የሆነ ከክልሎች የተነጠለ ተቋም መሥርተው ከአዲስ አበባ እስከ ወረዳ የሚደርስ አደረጃጀት ፈጥረው የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም አብዛኞቹ የፌዴራል መንግሥት ሥራዎች የሚፈጸሙት በክልል ሲቪል ሰረቫንትስ ነው፡፡ የፍርድ ቤቶች ሁኔታም በአሁኑ ወቅት የፌዴራሉ መንግሥት ፍርድ ቤት ለራሱ ብቻ ተለይተው በተሰጡት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚሰጡ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን በየክልሎች እያቋቋመ ሲሆን ባልተቋቋመባቸው ክልሎች ጉዳዮቹ የሚታዩት ለክልሎች በተሰጠ ውክልና ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የወንጀል ምርመራ ጉዳይና የመቀሌዎቹ ‹‹ፌዴራሎች›› ጉዳይስ እንዴት ይታያል?

መቀሌ ታግተው ከሰሞኑ የተለቀቁት የፌዴራል ፖሊስ አባላት ለምን ወደ መቀሌ እንደሄዱ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ዝርዝር ጉዳዮች ቢታወቁ ኖሮ ጉዳዩን በሚገባ ለመተንተን መልካም ሁኔታ ይፈጥር ነበር፡፡አንድ የክልል መንግሥት የፌዴራል መንግሥት የፖሊስ አባላት ወደ ክልሌ መምጣታቸው ‹‹አጠራጥሮኛል›› ብሎ ሊያግት ይችላል ወይ? ምንም እንኳ ክልሎች የክልላቸውንና ሰላምና ጸጥታ የመጠበቅ ጥቅል ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን ቢኖራቸውም የፌዴራሉ መንግሥት በሕገ-መንግሥቱ የፌዴራል ፖሊስ የማደራጀትና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚታዩ ወንጀሎችን የመመርመር ሥልጣን እንዳለው መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት የፌዴራል ፖሊሲን ሲያደራጅና ሲያሠማራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

አሁን በሥራ ላይ ያለው የፌዴራል ፖሊስን የሚያቋቁመው አዋጅ ቁጥር 720/2011 አንቀጽ 6 የተቋሙን ሥልጣንና ኃላፊነት ይዘረዝራል፡፡ ከሌሎች መካከል ‹‹በሕገ-መንግሥቱና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ፣ በመንግሥትና በሀገር ፀጥታ እና በሰብዓዊ መብት ላይ የሚፈፀሙ ማናቸውም ዓይነት የወንጀል ስጋቶችና ድርጊቶችን ይከላከላል፣ ይመረምራል፤›› ‹‹በፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን ትእዛዞችና ውሳኔዎች ይፈፅማል፤›› ‹‹በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሥልጣን ክልል ስር የሚወድቁ ወንጀሎችን ይከላከላል፣ ይመረምራል፤›› ‹‹ከመረጃ መረብና ከኮምፒዩተር ሥርዓት ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን ይመረምራል፤›› ‹‹ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና እገታ፣ የአደገኛ ዕፆች ዝውውርና ስርጭት፣ የአውሮፕላን ወይም የመርከብ ጠለፋ /ለምሳሌ ጣና ሐይቅ ላይ ጀልባ ቢጠለፍ ሎል/፣ የተደራጀ ዘረፋ፣ ውንብድና፣ አሸባሪነት እና የፀጥታ ማደፍረስ ወንጀሎችን ይከላከላል፣ ይመረምራል፤›› ‹‹አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ሥር የሚወድቁ የወንጀል ጉዳዮችን እንዲከላከሉና እንዲመረምሩ ለክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች የውክልና ስልጣን ይሰጣል፤ በውክልናው መሠረት ስለተፈጸሙ ጉዳዮች ሪፖርት ይቀበላል፤›› ‹‹ከሽብርተኝነት ድርጊት ጋር በተያያዘ ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመመርመር የሚረዳ መሆኑ የታመነበትን መረጃ ወይም ማስረጃ ከማንኛውም ሰው ጠይቆ ይወስዳል፤›› ‹‹የኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ሆኖ እንደአስፈላጊነቱ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን በማናቸውም ሥፍራ ሊያቋቁም ይችላል፡፡›› የሚሉ ጉዳዮች ተጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች በውክልና የሠጣቸው የወንጀል መከላልና ምርመራ ሥልጣኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግምት ሊወሰድ የሚችል ቢሆንም እንኳን ፖሊስ ወደ ክልሎች ለመንቀሳቀስ (በአገሩ ላይ ለመንቀሳቀስ የክልሉ ፍቃድ ባያስፈልገውም) ከተዘረዘሩት ኃላፊነቶች አንዱ መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ በእኔ ግምት ‹‹የመቀሌዎቹ ፌዴራሎች›› ፌዴራል ፍርድ ቤት የእሥር ማዘዣ የወጣላቸውን ሰዎች ለማምጣት ወደ ክልሉ ተንቀሳቅሰዋል የሚል ነው፡፡ በክልሉ ሥልጣን ሥር ያለ ሕገ-ወጥ ተግባር ሲከውኑ ካልተገኙ ወይም ካልተጠረጠሩ በስተቀር የክልሉ ፖሊስ ከአውሮፕላን የሚወርዱ የፌዴራል ፖሊሶችን ገና ለገና ‹‹ጥርጣሬ›› አድሮብኛል ብሎ የማገትም ሆነ በሕግ የተሠጣቸውን ኃላፊነት እንዳይወጡ የማስተጓጎል ሥልጣን የለውም፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕገ-ወጥ ተግባር የተጠረጠረ ሰው ደግሞ በተገቢው ሰዓት ወደ ፍርድ ቤት መቅረብና ምርመራ ሊከናወንበት ይገባል እንጂ ሊታገት አይገባውም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር የክልሎችን አጉራዘለልነት ካልሆነ በስተቀር ሕገ-መንግሥታዊ፣ የፌዴራል አወቃቀር መንፈስን የተከተለ አይመስልም::

ቢኒያም መንበረወርቅ (ፀሃፊ)

Source: Biniyam Menberework’ Facebook Page