አዙሪት፡ መማር – ማስተማር – መማር

አንድ አሜሪካዊ ወዶ ዘማች (ፒስ-ኮር) ማላዊ በምትባለዋ አፍሪካዊ ሀገር ለረጅም አመት ተመድቦ ሲሰራ የቀሰመውን ተሞክሮ ለመነሻ ያህል በአጭሩ እንመልከት። ይህ አሜሪካዊ ለመጀመሪያ ግዜ ማላዊ ተመድቦ ሲሄድ የአከባቢ ነዋሪዎች ኑሮና አኗኗር በጣም የተጎሳቆለ መሆኑን ይገነዘባል። በመሆኑም የማህብረሰቡን ኑሮና አኗኗር ለመቀየር ሕዝቡን ማስተማር እንዳለበት አምኖ ይንቀሳቀሳል። ለሁለተኛ ግዜ ተመድቦ ሲሄድ ግን ማህብረሰቡን ማስተማር ብቻ ሳይሆን እሱም ከማህብረሰቡ መማር እንዳለበት ይወስናል። ለሦስተኛ ግዜ ተመድቦ ሲሄድ ደግሞ ማህብረሰቡን ለማስተማር የሚያስችል ዕውቀትና ግንዛቤ እንደሌለው፣ ከዚያ ይልቅ እሱ ራሱ ከማህብረሰቡ መማር እንዳለበት ይገነዘባል።

ከላይ የተገለፀው የተግባር ተሞክሮ፤ በግለሰቦች መካከል፣ በግለሰብና ማህብረሰብ፣ እንዲሁም በተለያዩ ማህብረሰቦች መካከል ያለውን ልዩነትን ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ ማህበራዊ ችግሮች ምን ያህል ውስብስብና ከማህብረሰቡ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጠላለፉ እንደሆነ ይጠቁማል። ስለዚህ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትና በዚህም የሰዎችን የኑሮና አኗኗር ዘይቤ ለማሻሻል በቅድሚያ የማህብረሰቡን ተጨባጭ ሁኔታ መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን የአስተማሪው ዕውቀትና ግንዛቤ፣ እንዲሁም የሚያስተምረው ትምህርት በተጨባጭ እውነታ ላይ የተመሰረተ ይሆናል። በዚህ መሰረት በማህብረሰቡ ኑሮና አኗኗር ላይ ለውጥና መሻሻል ማምጣት ይቻላል።

በዚህ መሰረት በማህብረሰቡ ውስጥ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው አሜሪካዊ ወዶ ዘማች አካሄዳችን የተገላቢጦሽ መሆን የለበትም። በየትኛውም ማህብረሰብ ዘንድ ቢሆን ለውጥና መሻሻል ለማምጣት ጥረት ማድረግ ከመጀመራችን በፊት የማህብረሰቡን ነባራዊ ሁኔታ፥ ባህል፥ ልማድ፥ ስነ-ልቦና እና ሌሎች ተያያዥ ነገሮችን በጥሞና ማጤንና መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህን ሳናደርግ የምናደርገው የለውጥ እንቅስቃሴ እንደ አዙሪት መንገድ የተነሳንበት ቦታ ላይ ይመልሰናል። በዚህ መሰረት ለውጥ የሚጀምረው የማህብረሰቡን ኢኮኖሚያዊ፥ ፖለቲካዊ፥ ባህላዊ፥ ስነ-ልቦናዊ፥ መንፈሳዊ፥ … ወዘተ ጉዳዮች በማጥናት ነው። አንድን ማህብረሰብ ከማስተማራችን በፊት ከማህብረሰቡ መማር ይቀድማል። ስለዚህ ከለውጥ በፊት ማስተማር፣ ከማስተማር በፊት ደግሞ መማር ይቀድማል።

One thought on “አዙሪት፡ መማር – ማስተማር – መማር

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡