“የቻይና ጅብ” ክፍል 3፡ የኢትዮጵያ የውጪ ዕዳ በ1% ከጨመረ ባቡር መስመሩ ለቻይና ተላልፎ ይሰጥ ነበር!

ከታች በምስሉ ላይ እንደሚታየው ያለባቸው የዕዳ ጫና በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከኢኮኖሚ አልፎ በሀገራቱ ሉዓላዊነት ላይ የህልውና አደጋ ተጋርጧል። ትላንት ባወጣሁት ሁለተኛ ክፍል የቻይና ጅብ ሲርላንካን እንዴት አድርጎ እንደበላት ተመልክተናል። እንደ ፓኪስታን (Pakistan)፣ ኔፓል (Nepal) እና ማይንማር (Myanmar) ያሉ ሀገራት ደግሞ እንደ ሲሪላንካ ሉዓላዊነታቸውን ላለማስደፈር የቻይና መንግስት የሚሰጠውን ፈንድና ብድር አንቀበልም ብለዋል። በእነዚህ ሦስት ሀገራት በ20 ቢሊዮን ዶላር ሦስት ሃይል ማመንጫ ግድብ ለመስራት የነበረውን ዕቅድ ውድቅ አድርገውታል። ሀገራቱ ቻይና በምትሰጠው ብድር ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ የገቡ ሲሆን የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቹን ውድቅ ያደረጉበት ምክንያት አንድና ተመሳሳይ ነው።

ፓኪስታንን መሃል ለመሃል አቋርጦ የሚሄደውን የንግድ መስመር (ኮሪዶር) 44 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል። አብዛኛው ብር ከቻይና መንግስት ፈንድና ብድር የተገኘ ሲሆን ፓኪስታንን ለከፍተኛ የዕዳ ጫና ዳርጓታል። የቻይና መንግስት ይህንን ምክንያት በማድረግ አዲስ ለሚገነባው የሃይል ማመንጫ የሚሰጠው የ14 ቢሊዮን ዶላር ብድር ዋስትና እንዲሆነው የሚገነባውን ግድብ ጨምሮ አንድ ሌላ ነባር የሃይል ማመንጫ ግድብን በማስያዣነት እንዲሰጠው ይጠይቃል። የፓኪስታን መሪዎችን ይህን በመቃወም አዲሱን ግድብ ለማስራት የነበራቸውን ዕቅድ ውድቅ ያደርጉታል።

የኔፓልና ማይንማር መንግስታት ደግሞ የሃይል ማመንጫውን ግንባታ የሚያከናውኑት የቻይና ኩባንያዎች አላስፈላጊ ጥቅምና ሙስና በመጠየቃቸው እንደሆነ ጠቁመዋል። ስለዚህ የቻይና መንግስት በሀር መንገድ ፕሮጀክት በሚሰጠው ብድር አማካኝነት በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ የወደቁ ሀገራትን እያደነ፤ እንደ ሲሪላንካ ሉዓላዊ መሬታቸውን ይቆጣጠራል፣ እንደ ፓኪስታን የሀገራቱን የተፈጥሮ ሃብት ለመቆጣጠር ይሞክራል፣ እንደ ኔፓልና ማይንማር ደግሞ የቻይና ኩባኒያዎች በሙስና እና ሕገ-ወጥ ተግባራት ይሰማራሉ።

ጅቡቲ ከስሪላንካ 4000 ከ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች። ልክ እንደ ቀድሞ የስሪላንካ መሪ ጅቡቲም አምባገነን የሆነ መሪ አላት። ከታች ባለው ምስል ላይ እንደሚታየው በቻይና የሀር መንገድ ዕቅድ መሰረት ከስሪላንካ የተነሱ ትላልቅ የንግድ መርከቦች በኬኒያ የላሙ (Lamu) ወደብ በኩል አድርጎ ወደ ጅቡቲ ይመጣል። በመሆኑም ከቻይና በተገኘ ብድር ጅቡቲና ኬኒያ ላይ ትላልቅ ወደቦች ተገንብተዋል። ከሁሉም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተሻለ ኬኒያ ዴሞክራሲያዊ ናት። ምንም እንኳን ኬኒያ ውስጥ ከፍተኛ ሙስና ቢኖርም የሀገሪቱ መንግስት ሥራና አሰራር ከየትኛውም የምስራቅ አፍሪካ የተሻለ ግልፅነትና ተጠያቂነት አለው። ለዚህ ደግሞ በቅርቡ የተካሄደውን ፕረዘዳንታዊ ምርጫ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

Doraleh Multipurpose Port, Djbouti

አሁን ላይ በስሪላንካ አፉን ከፍቶ የሚውለውን የ“Hambantota” ወደብ እና የጅቡቲን “Doraleh Multipurpose Port” የገነባው “China Merchants Ports Holding Company – CMPort” በመባል የሚታወቀው የቻይና ኩባንያ ነው። የቻይና እና ጅቡቲ መንግስት በጥምረት የሰሩት የዶራሌህ (Doraleh) ወደብ በጠቅላላ 3.4 ቢሊዮን ዶላር የፈጀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ወጪ የተሸፈነው ከቻይና መንግስት በተሰጠ ብድር ነው። በተመሳሳይ የቻይና መንግስት ለኬኒያ ከፍተኛ ብድር ያበደረ ቢሆንም እንደ ጅቡቲ የሉዓላዊነት አደጋ አልጋረጠም።

የጅቡቲ የብድር መጠን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የሀር መንገድ ከሚያልፍባቸው 68 የዓለም ሀገራት በተለየ የሀገሪቱ አመታዊ የምርት መጠን 88% ሆኗል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 90% የሚሆነው ብድር የተሰጠው ከቻይና ነው። አንድ ሀገር ያለበት የውጪ ብድር መጠን ከ50% ላይ ከሆነ የሀገሪቱ ተጨማሪ ብድር የማግኘት ዕድል በጣም አነስተኛ ይሆናል። የብድር መጠኑ ከ60% በላይ ሲሆን ግን የዕዳ ጫናው በሀገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ አደጋ ይጋርጣል። የጅቡቲ የብድር መጠን ከዚህ አልፎ 88% መድረሱና ከዚህ ውስጥ 90% ከቻይና መንግስት የተገኘ መሆኑ ያለ ምንም ጥርጥር የሀገሪቱ ሉዓላዊነት ተገፍፏል ብሎ መደምደም ይቻላል።

ነገር ግን የጅቡቲ ዋና የገቢ ምንጩ ኢትዮጵያ ናት። ከወደብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በአመት ለጅቡቲ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ትከፍላለች። ስለዚህ ጅቡቲ ውስጥ ትልቅ ወደብ ከመገንባት በተጨማሪ የኢትዮጵያን የውጪና ገቢ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ የሚያስችል የትራንስፖርት መስመር መዘርጋት አለበት።

በዚህ መሰረት ከቻይና ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ በተገኘ 3 ቢሊዮን ዶላር ብድር ከፍተኛ በሚባል የወለድ መጠን የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ተዘረጋ። የቻይና መንግስት ከሁሉም ሀገራት በተለየ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ብድር ሰጠ። በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ የብድር መጠን ከአመታዊ የምርት መጠን አንፃር ከአራት አመት በፊት ከነበረበት 46.8% ተነስቶ 59% ደረሰ። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የኢትዮጵያ የብድር ጫና ከፍተኛ “High” ደረጃ ላይ መድረሱን አስታወቅ። ከዚህ በኋላ አንድ ፐርሰንት ጨምሮ 60% ከሆነ የዕዳ ጫናው ኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ይጥለዋል።

በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትርፋማ አለመሆን እና የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ሥራ ከመጀመሩ ሁለት አመታት ቀደም ብሎ የብድር ዕዳው እንዲከፈል መደረጉ ዓይነተኛ ማሳያ ነው። በቻይና ኩባንያ የሚሰራ የባቡር ሃዲድ ተጠናቅቆ ስራ ከመጀመሩ ሁለት አመታት ቀደም ብሎ ከቻይና ባንክ የተገኘ ብድር እንዲከፈል የሚያደርግ አሰራር ኢትዮጵያን የዕዳ ጫና ውስጥ ለመክተት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ዓላማ ሊኖረው አይችልም።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጅቡቲ አንፃር በጣም ትልቅ ስለሆነ እንደ ምንም ተንገጫግጮ 59% ላይ ቆሟል። አንድ ፐርሰንት ተጨማሪ ብድር ቢወስድ ከ60% የዕዳ ጫና ቀይ መስመር ያልፋል፡፡ ልክ በፓኪስታን፣ ኔፓልና ማይነማር እንደጠየቀችው፣ በስሪላንካና ጅቡቲ በተግባር እንዳደረገችው የቻይና መንግስት የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር፣ የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መስመር ወይም የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መሬት ወይም የተፈጥሮ ሃብት ለሰጠችው ብድር በማስያዣነት እንዲሰጣት መጠየቋ አይቀርም ነበር። ባለፉት ሦስት አመታት በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እጥረት የተከሰተው ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው። “የቻይና ጅብ” ኢትዮጵያን እንደ የፍየል ቆለጥ “አሁን ከአሁን ወደቀች” እያለ አፉን ክፈቶ እየተጠባበቀ ሳለ ዶ/ር አብይ “ዱብ…” አለ።

One thought on ““የቻይና ጅብ” ክፍል 3፡ የኢትዮጵያ የውጪ ዕዳ በ1% ከጨመረ ባቡር መስመሩ ለቻይና ተላልፎ ይሰጥ ነበር!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡