“የቻይና ጅብ” ክፍል 4፡ ከኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት በስተጀርባ ያለው ዶ/ር አብይ ወይስ ዱባይ ኤሜሬት?

የጅቡቲ ኢኮኖሚ አቅም በጣም ትንሽ ከመሆኑም በላይ በኢትዮጵያ ላይ ጥገኛ ነው። የቻይና ብድር ሲያጥለቀልቃት የዕዳ ጫናው በአንዴ ተስፈንጥሮ 88% ላይ መድረሱን በሶስተኛው ክፍል ተመልክተናል። በመሆኑም አሁን ላይ “የቻይና ጅብ” የጅቡቲን ሉዓላዊነት መቆረጣጠም ጀምሯል። ለምሳሌ ቀድሞ ከነበሩት ፈረንሳይና አሜሪካ በተጨማሪ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ኢጣሊያን፣ ጃፓን፣ ሳውዲ አረቢያ እና ቻይና በጅቡቲ የራሳቸውን የጦር ሰፈር እንዲከፍቱ ፈቅዷል። በዚህ መልኩ የሀገሪቱን መሬት ለውጪ ሀገራት ሸንሽኖ በማከራየት በአመት ከአሜሪካ 70 ሚሊዮን ዶላር፣ ከፈረንሳይ 30 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ከቻይና 20 ሚሊዮን ዶላር “ኪራይ” ይሰበስባል። በተመሳሳይ ከጃፓን፥ ኢጣሊያን እና ሳውዲ አረቢያ ተመሳሳይ የመሬት ኪራይ ይሰበስባል።

እነዚህ ሁሉ ሀገራት ጅቡቲ ላይ የጦር ሰፈር መክፈት ለምን አስፈለጋቸው? ምክንያቱም ጅቡቲ በየብስም ሆነ በባህር ቁልፍ የሆነች ስትራቴጂካዊ ቦታ ናት። በየብስ ከዚህ ማዶ ያልተረጋጋች ሶማሊያ፣ ከዚያ ማዶ ደግሞ ያልተረጋጋች የመን ነች። በባህር ደግሞ ከታች የህንድ ውቂያኖስ፣ ከላይ ቀይ ባህር ናቸው። የዓለም ትልቁ ባህር ንግድ መስመር ስዊዝ ካናል የሚሄዱ ሆነ ከዚያ የሚመጡ መርከቦች የሚያልፉት በኤደን ባህረ ሰላጤ ነው። ያልተረጋጋ ሀገር ለሽፍታ ያመቻል እንደሚባለው ያልተረጋጉት ሶማሌያና የመን ደግሞ የባህር ላይ ሽፍታ መደበቂያ መሆናቸው እርግጥ ነው። ይህንን በሶማሊያ የባህር ላይ ሽፍቶች በተግባር ተረጋግጧል።

ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ በጅቡቲ የጦር ሰፈር 4000 ወታደሮች አሏት። እነዚህ ወታደሮች በሶማሌያ እና የመን የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖችን ለመምታት የጦር መሳሪያና ሰው-አልባ አውሮፕላን ከጅቡቲ የጦር ሰፈር ታስወነጭፋለች። ሳውዲ አረቢያ ደግሞ በየመን የሚገኙ አማፂያንን ለመደብደብ ትጠቀምበታለች። ከቻይና በስተቀር እንደ ጃፓን፥ ፈረንሳይና ኢጣሊያ ያሉት ሀገራት ደግሞ የንግድ መርከቦቻቸውን ደህንነት በቅርብ ርቀት ይከታተላሉ። ቻይና በጅቡቲ የጦር ሰፈር ከ2500 በላይ ወታደሮች እንዳሏት ይገመታል። የእነዚህ ወታደሮች ስራ የንግድ መርከቦችን ደህንነት ከመጠበቅ የዘለለ ነው።

በጅቡቲ ያለው ጦር ሰፈር ከቻይና ውጪ የመጀመሪያው የጦር ሰፈር ነው። ይህ የጦር ሰፈር የተገነባው እንደ ሌሎች ሀገራት በመሬት ኪራይ አይደለም። ከዚያ ይልቅ በቅድሚያ ጅቡቲን በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ በማስገባትና ሀገሪቱን በማስጨነቅ የተገኘ ነው። የአሜሪካ እና የቻይና የጦር ሰፈር በዚህ ያህል ርቀት ያለበት ሌላ ሀገር ወይም ቦታ የለም። ጅቡቲ ለቻይና የጦር ሰፈር እንዳትፈቅ ከአሜሪካ ከፍተኛ ጫና ጉትጎታ አድርጋለች። ሆኖም ግን 88% የዕዳ ጫና ውስጥ ያለችው ጅቡቲ ለቻይና የጦር ሰፈር ከመፍቀድ ሌላ ምርጫና አማራጭ አልነበራትም።

የቻይና ጦር ሰፈር በተከፈተ ማግስት ወደ መደበኛ ስራው ገባ። ይኸውም በአከባቢው ዘመናዊ የስለላ መሳሪያ በመትከል የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖችን መሰለል ጀመረ። አሜሪካኞች ጉዳዩን አስመልክቶ ለጅቡቲ መንግስት አቤቱታ ሲያሰሙ ቻይናም ብሶተኛ ሆና አቤቱታ አቀረበች። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የጅቡቲ መንግስት ቀድሞ በዚህ አመት የካቲት ወር ላይ “Doraleh Multipurpose Portን የኮንቴነር ተርሚናል ሲያስተዳድር ከነበረው “Dubai Ports World – DP World” የዱባይ ኤሜሬት ኩባኒያ ጋር የነበራቸውን ውል በመሰረዝ ለቻይና ኩባኒያ ሰጡት። ይህን የጅቡቲ ወደብ ደግሞ ከኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ በተጨማሪ የአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ኢጣሊያ፣ ሳውዲ አረቢያ እና ጃፓን ጦር ይገለገሉበታል። የቻይና ጦር ደግሞ “Doraleh” ወደብ ላይ ቁጭ ብሎ ወደ አሜሪካ የጦር ሰፈር የሚገባውን እና የሚወጣውን ይሰልላል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ሌሎቹ ሀገራት የጦር ሰፍር የሚገባውንና የሚወጣውን ይቆጣጠራል።

ከሁሉም አገራት በላይ ግን ጅቡቲ ኢትዮጵያን ትፈልጋለች። ምክንያቱም አንድ ቢሊዮን ዶላር የወደብ አገልግሎት ክፍያ ከወለድ ነፃ በየአመቱ ትከፍላለች። ስለዚህ በኢትዮጵያ የመጣ በጅቡቲ ዓይን የመጣ ነው። 95% የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ የሚካሄደው በጅቡቲ ወደብ በኩል ነው። ከ20 አመት በፊት ግን ታሪኩ የተገላቢጦሽ ነበር። ከሃያ አመት በፊት የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ 5% በጅቡቲ፣ 5% በምፅዋ፣ የተቀረው 90% ደግሞ በአሰብ ወደብ በኩል እንደነበር ይታወቃል። የሰይጣን ጆሮ አይስማና ኢትዮጵያና ኤርትራ ድንገት ቢታረቁና ኢትዮጵያ እንደ ቀድሞ የአሰብ ወደብን መጠቀም ብትጀምር አምባገነኑ የጉሌ መንግስት ተንኮታኩቶ ይወድቃል።

ባለፉት ሦስት ወራት ዱባይ ኤሜሬት በምስራቅ አፍሪካ ከሶማሌያ እስከ ኤርትራ በጥድፊያ የምትወራጨው የጅቡቲ መንግስት “ከDubai Ports World – DP World” ጋር የነበረውን ውል ሰርዞ ከሀገሪቱ ስላባረራት ነው። “ዱባይ ኤሜሬት ለምን ከጅቡቲ ተባረረች?” ለሚለው የአንድ ቢሊዮን ብር ጥያቄ መልሱ በሚገርም ሁኔታ በጣም ቀላል ነው። እሱም ዱባይ ኤሜሬት ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማስታረቅ ስትሞክር ተደርሶባት ነው። እውነትም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የሰላም ስምምነት የተጀመረው ጠ/ሚ አብይ አህመድ እና ፕ/ት ኢሳያስ አፍወርቂ በአቡ-ዲያቢ ከተማ ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ነው።

የኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነቱ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ ተከትሎ ደግሞ የዱባይ ኤሜሬቱ መሪ ለጠ/ሚ አብይ አህመድ እና ለፕ/ት ኢሳያስ አፍወርቂ የሀገሪቱን ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ መሸለማቸው ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪ በአስመራ ቤተ መንግስት በተደረገ የራት ግብዣ ላይ ጠ/ሚ አብይ የተባበሩት መንግስታት በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳ እንደሚሰሩ መናገራቸው ይታወሳል።

በእርግጥ በቃላቸው መሰረት ዶ/ር አብይ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ አምባሳደር በኩል ጥያቄ አቅርበዋል። ሆኖም ግን የጅቡቲ መንግስት ባቀረበው ተቃውሞ ምክንያት ማዕቀቡ ሳይነሳ ቀረ። ከኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት በስተጀርባ ያለው ማን ነው፤ ደ/ር አብይ ወይስ ዱባይ ኤሜሬት? በዚህ ረገድ የሳውዲ አረቢያና አሜሪካ ሚና ምን ይመስላል? ከዚህ ጋር በተያያዘ ቻይና እና ጅቡቲ ምን ዓይነት አፍራሽ ሚና ሊኖራቸው ይችላል? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን።

3 thoughts on ““የቻይና ጅብ” ክፍል 4፡ ከኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት በስተጀርባ ያለው ዶ/ር አብይ ወይስ ዱባይ ኤሜሬት?

  1. Remember Abiy’s first parliament speech . you should not have connected the reconciliation of the two countries with the Arab Emirate. It is well articulated article and a nice perspective

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡