“የቻይና ጅብ” ክፍል 5፡ “ጅቡቲ ተበልታለች፣ አፍሪካን (ኢትዮጵያ) እንዴት እንታደጋት?” የአሜሪካ ጦር አዛዥ

በቻይና ጅብ ተከታታይ ፅሁፍ አራተኛ ክፍል ቻይና ለጅቡቲ ወደብ 1 ቢሊዮን ዶላር ብድር በመስጠት በዕዳ ጫና ሲጥ… እንዳደረገቻት ገልጩያለሁ። የዕዳ ጫናው ጅቡቲን አስጨንቋት ወደላይ ያስመልሳት ጀምሯል። በዚህ ምክንያት ሉዓላዊ መሬቷን ለመጣ ሀገር ሁሉ የጦር ሰፈር እንዲገነባበት ማከራየት እያከራየች ነው። ይህን በመጠቀም ቻይና ከሀገሯው ውጪ የመጀመሪያውን የጦር ሰፈር በጅቡቲ አቋቁማለች። በዚህ አመት የየካቲት ወር ላይ ደግሞ ጅቡቲ ወደቡን ለማስተዳደር ከዱባይ ኤሜሬት ኩባንያ ጋር የገባችውን ውል በማፍረስ ለቻይና መስጠቷ ተገልጿል። በዚህ ምክንያት ዱባይ ኤሜሬት ጅቡቲን በለንደን ፍርድ ቤት ለመገተር ጥድፊያ ላይ ናት።

በሌላ በኩል የህወሓት/ኢህአዴግ ሊቀመንበር ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ህልፈትን ተከትሎ ቻይና እ.አ.አ. በ2013 (2005) ዓ.ም ብቻ ለኢትዮጵያ 6.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ሰጥታለች። ቻይና እ.አ.አ. ከ2000 2014 ዓ.ም ለኢትዮጵያ የሰጠችው ብድር በጠቅላላ 12.3 ቢሊዮን ዶላር ነው። ከዚህ ውስጥ ግን ከግማሽ በላይ የሚሆነው (6.533 ቢሊዮን ዶላር) ብደር የተሰጠው በ2013 (2005) ዓ.ም ብቻ ነው። ከዚህ አመት ጀምሮ ባሉት አራት አመታት (ከ2014 – 2017) ውስጥ የኢትዮጵያ የዕዳ ጫና በ13% አሻቅቦ 59% ላይ ደርሷል። በዕዳ ጫና ምክንያት በተፈጠረ የውጪ ምንዛሬ እጥረት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ቁርጠት ይዞታል። በዚህ አመት የመጋቢት ወር ላይ ኢትዮጵያም እንደ ጅቡቲ ሊያሰመልሳት እያጥወለወላት ነበር።

“የቻይና ጅብ” ኢትዮጵያ አጥወልውሏት እስክትወድቅ በጉጉት እየጠበቀ ባለበት የመጋቢት ወር ላይ የአሜሪካ ምክር ቤት የጦር አገልግሎት ዋና ኮሚቴ (House Armed Service Committee) ተቀምጧል። የኮሚቴው አባላት፤ ጅቡቲ እንዴትና ለምን “በቻይና ጅብ” ተበላች፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍረካ ሀገራትን ቀረጣጥፎ እንዳይበላቸው የአሜሪካ መንግስት ምን ማድረግ አለበት? “የቻይና ጅብን” ለመግታት አሜሪካ ምን ዓይነት ስትራቴጂካዊ ስልት መከተል አለባት? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በአፍሪካ የአሜሪካ ኮማንድ (U.S. Africa Command) ዋና አዛዥ የሆኑትን ጄኔራል “Thomas D. Waldhauser” ላይ እያከታተሉ ያዘንቡባቸዋል። ጄኔራሉ ደግሞ የዓይን እማኝነታቸውን በተረጋጋ መንፈስ ይገልፃሉ።

በዚህ አመት የመጋቢት ወር ላይ በአፍሪካ የአሜሪካ ኮማንድ ዋና አዛዥ ጄኔራል “Thomas D. Waldhauser” ለአሜሪካ ምክር ቤት የጦር አገልግሎት ዋና ኮሚቴ (House Armed Service Committee) አባለት የሰጡት የዓይን-እማኝነት መረጃ በጉዳዩ ዙሪያ የሀገሪቱ መንግስት ምን አይነት አቋም እንዳለው ለማወቅ ያስችላል። በመሆኑም የኮሚቴው አበላት ቻይና በምስራቅ አፍሪካ እያደረገችው ስላለው እንቅስቃሴ እና በቀጣይ መወሰድ ሰላለበት እርምጃን አስመልክቶ ከጄኔራል “Thomas D. Waldhauser” ጋር ያደረጉትን ውይይት ለብቻው ለይተን በማውጣት እንደሚከተለው አቅርበናል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በዶላር እጥረት ስትቃትት፣ በህዝባዊ አመፅ ስታቃስት ቻይና ጅቡቲ ቁጭ ብላ እየተመለከተች። ኢትዮጵያ ከምትውጠው በላይ የጎረሰችው ዕዳ አስጨንቋት ኢኮኖሚያዋ የዶላር ቁርጠት ይዞታል። የገቢና ወጪ ንግዷ የሚተላለፍበት ደም-ስር በቻይና ቁጥጥር ስር ውሏል። አንዴ ተዝለፈልፋ ከወደቀች የቻይና ጅብ ዘልሎ ከላይ ይከመርባታል። ዱባይ ኤሜሬት አንዴ የኤርትራን አሰብ ወደብ፣ ሌላ ግዜ የፑንትላንድን ወደብ ለማልማትና ለመጠቀም ወዲያና ወዲህ ትራወጣለች።

የአሜሪካ ምክር ቤት የጦር ጉዳዮች ኮሚቴ በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ጋር ከተወያየ በኋላ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ከቻይና ጅብ ለመታደግ ወስኗል። የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባልደረቦች ወደ አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ መመላለስ ጀምረዋል። በዚህ አመት የመጋቢት ወር ላይ የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አፍሪካዊያን ከቻይና የዕዳ ወጥመድ ራሳቸውን እንዲጠብቁ አስጠንቅቀው ሄደዋል፡፡ በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳይ ሃላፊዎች ወደ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሳውዲ አረቢያ እና ዱባይ ኤሜሬት መመላለስ ቀጥለዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካን ኢምባሲ ባልተለመደ መልኩ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ በይፋ አቋሙን ማንፀባረቅ ጀምሯል። በተለይ በየካቲት ወር የፀደቀውን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በይፋ ተቃውሟል። በየካቲት ወር መጨረሻ አከባቢ ደግሞ የህወሓቶችን አቋም በመተቸት ለእነ ለማ መገርሳ ድጋፉን ገልጿል፡፡ የቀድሞ ጠ/ሚ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣን እንደሚለቁ ማሳወቃቸውን ተከትሎ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችና ምሁራን አንጋፋ የህወሓት ባለስልጣናትን በይፋ “kleptocrats” ብለው እስከመዝለፍ ደረሱ፡፡ በአንፃሩ ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር መሆን አለባቸው ሲሉ ድጋፋቸው ገለፁ፡፡ በእርግጥ “የአሜሪካኖቹ ተግባር ህወሓቶችን መግፍት ነው ወይስ መፈንቅለ መንግስት ነው?” የሚለውን በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን፡፡

2 thoughts on ““የቻይና ጅብ” ክፍል 5፡ “ጅቡቲ ተበልታለች፣ አፍሪካን (ኢትዮጵያ) እንዴት እንታደጋት?” የአሜሪካ ጦር አዛዥ

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡