መለስ Vs አብይ: አገር፥ የመሪ ስብዕና እና ተቋማት!

የግለሰብ ስብዕና በአገር እና በሕዝብ ላይ ያለውን ፋይዳ ለመታዘብ መለስ ዜናዊን እና ዶ/ር አብይ አህመድን ማሰብ በቂ ነው።

በያሬድ ሃይለማሪያም

ሰሞኑን በድህረ ገጾችና በየዜና ማሰራጫው አፍቃሪ መለሶች ግለሰቡ የሰራውንም ያልሰራውንም እያነሱ ሲያወድሱት ሳይ ይህ ሃሳብ ወደ አዕምሮዮ መጣ። የአንድ አገር ጥንካሬ፣ የወደፊት ተስፋ፣ አስተማማኝ የሆነ ሁለንተናዊ እድገት አቅጣጫ፣ ብልጽግና እና ሰላም የሚወሰነው አገሪቱ ባፈራቻቸው እና በማይናወጥ መሰረት ላይ በተዋቀሩ ተቋማት እና በመርሆዎች ላይ በተመሰረተ ሥርዓት (system) ነው። ጠንካራ እና ገለልተኛ ተቋማት ባሉበት አገር መንግስት ቢገለባበጥ እና ፖሪቲዎች ቢለዋወጡም በሕዝቡ መሰረታዊ ኑሮ እና በአገሪቱ ህልውና ላይ የሚፈጥሩት ጫና እምዛም አይደለም። ሕዝብና አገረ በአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ፍላጎት ሲመራ እና እጣ ፈንታው በነሱ እሳቤ ብቻ ሲወሰን ግን ውጤቱ ሌላ ነው።

ለዚህም ከአውሮፓ አገሮች ቤልጂየም ጥሩ ምሳሌ የምትሆን ይመስለኛል። ከአመታት በፊት በአገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ ድርጅቶች አለመግባባት የተነሳ አንድ አመት ከመንፈቅ ለሚጠጋ ጊዜ አገሪቱ ውስጥ የመንግሥትን ሥልጣን ማንም ሳይዝ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሌሎች የመንግስት ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎች በማንም ሳይያዙ አገሪቱ ያለ መሪ ቆይታለች። ይሁንና እጅግ ጠንካራ፣ ገለልተኛ እና በዲሞክራሲያዊ እሴቶች የታነጹ ተቋማት ያላት አገር ስለሆነች አገር ሳይታመስ፣ የሲቪል ሰርቪሱ ሥራ ሳይስተጓጎል፣ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ እና ሌሎች የመንግስት ተቋማት በተለመደው አግባብ ሥራቸውን እያከናወኑ የፖለቲካ አለመግባባቱ ሰከን ብሎ ፖለቲከኞቹ ወደ ህሊናቸው ተመልሰው መንግሥት እሲኪያዋቅሩ ድረስ ሁሉም ነገር በነበረበት ቀጥሏል።

አገር ከተቋማት ይልቅ በግለሰቦች ትከሻና መዳፍ ውስጥ ሲወድቅ አደጋው ብዙ ነው። እንደ መለስ አይነት በክፋት፣ በዕብሪት፣ በማን አለብኝ ባይነት ስሜት እና በዘር ጥላቻ አይምሮው በታወረ ሰው እጅ ስትወድቅ የሕዝብ እጣ ፈንታ ግድያ፣ እስራት፣ በየማጎሪያ በቱ ስቃይ፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ በጎጥ ተቧድኖ መባላት፣ እርሃብ፣ እርዛት እና ጥቂት ስግብግብ ሆዳሞች ነጥቀውት ሲበሉ እያየ ተመልካች መሆን ብቻ ነው። ባጭሩ አገርን፣ ሕዝብን፣ ተቋማትን፣ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችን፣ ፖለቲከኞችን እና የአገር ሽማግሌዎችን ማዋረድ፣ ማዋከብ እና ማራከስ የሥርዓቱ መገለጫ ነው ። ስሌቱ ሁሉ መቀነስ ነው።

በተቃራኒው አገር እንደ ዶ/ር አብይ አገርን፣ ሕዝብን እና እራሱን አክባሪ ሰው እጅ ስትወድቅ ደግሞ መለስ በ27 አመታት ውስጥ ያሳደዳቸውን፣ ያዋረዳቸውን፣ የቀነሳቸውን፣ ያጣጣላቸውን እና እርስ በርስ ያባላቸውን ሰዎች፣ ድርጅቶች እና አገራዊ ተቋማት በአራት ወራት ውስጥ መደመር፣ መሰብሰብ እና በአገራዊ ፍቅር ማስተሳሰር ይችላል። ዶ/ር አብይ በአራት ወራት ውስጥ ያከናወናቸውን ነገሮች ባሰብኩ ቁጥር መለስ እና ግብረአበሮቹ በ27 አመት ውስጥ የበደሉንን፣ ያስመለጡንን እድሎች እና ያቃጠሉብን እድሜ እንዳስብ ያደርገኛል።

ትልቁ ቁምነገር ያሳለፍነው ሳይሆን ወደፊት የምንኖረው ነውና እንቅልፍ ሊነሳን የሚገባው የትላንቱ ሳይሆነ የነገው ነው። የኋላውን ለታሪክና ለትምህርት ትተን ዛሬ በምናደርጋቸው ነገሮች የነገዋን ኢትዮጵያ ማሰቡ ይበጃል። ከዚህ በኋላ እንኳን 27 አመት፤ 27 ቀንም ቢሆን ከእድሜያችን ላይ ለአንባገነኖች፣ ለሥርዓት አልበኞች፣ ለሙሰኞች፣ ለመብት እረጋጮች፣ በጎጥ ለሚከፋፍሉን መሰሪዎች፣ ለሰነፍ እና ድንቁርና ለተጫናቸው ፖለቲከኞች የምንሰጠው ጊዜ የሌለን መሆኑን ለራሳችን ቃል ከገባን እና ተግተንም ልንሰራ ይገባል። እንደ አንድ ኃላፊነት የሚሰማ ዜጋ ግዴታችንን በወቅቱና በተገቢው መንገድ ከተወጣን አዲዎስ ብለን የሸኘነው አንባገነናዊ ሥርዓት እና ጨፍላቂ አስተሳሰብ ዳግም በኢትዮጵያ ምድር ሥፍራ አይኖረውም።

ዶ/ር አብይ የአገሪቱን ተስፋ እና የለውጥ መንገድ ሊሸከሙና ከገባንበት ቅርቃር ሊያወጡን የሚችሉ ሕዝባዊ ተቋማትን ለመገንባት ለሚያደርጉት ጥረት እገዛ ማድረግ ኢሕአዴግን መደገፍ ሳይሆን ኢትዮጵያን በማይናወጥ የዲሞክራሲ መሰረት ላይ የማስቀመጥ ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት ሰለሆነ ሁሉም የድርሻውን እንደየአቅሙ በመወጣት እውን እንዲሆን ማድረግ ይኖርብናል።

የአገር ጉዳይ እስታዲዮም ገብቶ ኳስ ጨዋታ እንደ መመልከት አይደለም። ሁሉም ዜጋ ተጫዋች ነው መሆን ያለበት። ዋናው ነገር ሁሉም አጥቂ፣ ሁሉም በረኛ፣ ሁሉም ተከላካይ መሆን ስለማይችል እንደ የአቅምና ችሎታ ሁሉም ለጨዋታው ስኬት አስተዋጽዎ ይኑረው። የጤናማ አገር መገለጫውም እያንዳንዱ ዜጋ በአገር ግንባታው ሂደት ላይ የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ አሳታፊ እና እኩል እድል መፍጠር የሚችል ሥርዓት መዘርጋት ሲችል ነው። ሁሉም ዜጋ በሰውነቱና በዜግነቱ እኩል ክብር ከተሰጠው ሌላው በእውቀት እና በችሎታ የሚደረጉት መበላለጦች የጤናማ ውድድር መገለጫዎች ስለሆኑ ሃኪሙ ዳኛ፣ ጠበቃው መሃንዲስ፣ መሃንዲሱ የፖለቲካ ሊቅ፣ ፖለቲከኛው የኃይማኖት ሰባኪ ካልሆንኩ አገር ትፈርሳለች ብሎ አይፎክርም።

ሁሉም በየሙያው ከራሱ አልፎ ለአገሩ የሚበጅ ዜጋ ይሆናል። ወቅቱ የአገር ግንባታ እና አገርን ከቀማኞች የመታደጊያ ጊዜ በመሆኑ ጤናማ ያልሆኑ ፉክክሮች፣ አገራዊ ፋይዳ የሌላቸው ነገር ግን አጥፊ፣ ከፋፋይና ቅራኔን የሚያሰፉ ብሽሽቆች ከወዲሁ ቢገቱ መልካም ነው። በፓርቲዎች መካከል የሚካሄደው ፉክክር ተፈጥሯዊ ሂደቱን ጠብቆ ይመጣል። ዋናው እራይ ያለው ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መገኘት ነው።

በቸር እንሰንብት

Yared Hailemariam

One thought on “መለስ Vs አብይ: አገር፥ የመሪ ስብዕና እና ተቋማት!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡