“የቻይና ጅብ” ክፍል 7፡ አሜሪካኖች ኦህዴድን በመደገፍ ህወሓትን ገፍተዋል!

የቻይና መንግስት “አዳኝ” (Predatory) ነው። የሚያድነው ደግሞ የምዕራቡ ዓለም ፊት የነሳቸውን ጨቋኝና አምባገነን መንግስታት ነው። ከምዕራባዊያን መንግስታት ጋር የተጠናከረ ዲፕሎማሳያዊ ግንኙነት ለመመስረት የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ቅድመ-ሁኔታ ተደርጎ ይቀመጣል። በምዕራቡ ዓለም ከሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ብድር ለማግኘት ኢኮኖሚው ገበያ መር መሆን አለበት። ጨቋኝና አምባገነን መንግስታት ደግሞ የዜጎችን ፖለቲካዊ መብትና ነፃነት አያከብሩም፥ አያስከብሩም። በመሆኑም በዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ጥሰት ይፈፀማል።

ሌላው በኢኮኖሚ ሴክተሩ ላይ ያላቸውን ቁጥጥርና የበላይነት ስለሚያሳጣቸው ገበያ መር ስርዓት ለመዘርጋት ቁርጠኛ አይደሉም። ከዚህ በተጨማሪ እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክ እና ሌሎች የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት በተለይ ከጨረታና ግዢ አሰራር ጋር በተያያዘ የሚጠይቁትን ግልፅነትና ተጠያቂነት መስፈርት አይቀበሉም። ምክንያቱም ጨቋኝና አምባገነን መንግስታት የዜጎች መብትና ነፃነትን ከመገደብ በተጨማሪ በሙስና እና ብልሹ አሰራር የተዘፈቁ ናቸው። ስለዚህ ጨቋኝና አምባገነን የሆኑ መንግስታት ከምዕራባዊያን መንግስታት እና የፋይናንስ ተቋማት ጋር ዓይና እና ናጫ ይሆናሉ። ምዕራባዊያን ፊት የነሷቸው ጨቋኝና አምባገነን መንግስታት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍና ብድር ለማግኘት ሲንከራተቱ የቻይና ጅብ ዓይን ያርፍባቸዋል።

ይህን ግዜ የቻይና ጅብ በሀገራቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ በመግለፅ በመሰረተ ልማት ግንባታና በብድር አቅርቦት ትብብርና ድጋፍ ለማድረግ ፍቃደኝነቱን ይገልፃል። በመጀመሪያ ደረጃ በሀገር-አቀፍ ሆነ ዓለም-አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ “ገለልተኛ” የሚባል ኃይል የለም። “በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አልገባም” በሚል ከጨቋኝና አምባገነን መንግስት ጋር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማድረግ በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን በደልና ጭቆና ከመደገፍ ተለይቶ አይታይም። እዚህ’ጋ “ትልቅ ዝሆን አይጥን ረግቶ ቆሞ ሳለ ‘ገለልተኛ’ ነኝ ብሎ ማለፍ በአይጧ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ቸል በማለት ጉልበተኛውን ዝሆን መደገፍ ነው” የሚለውን የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ የነበሩት የዶዝሞን ቱቱ አባባልን መጥቀስ ይቻላል።

በአጠቃላይ ከሰብዓዊ እርዳታና ድጋፍ በዘለለ ከአምባገነን መንግስት ጋር ትብብርና ድጋፍ ማድረግ በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ግፍና በደል እንደማበረታታት ሊወሰድ ይገባል። የቻይና መንግስት ግን በምዕራባዊያን ፊት ለተነሳቸው ጨቋኝና አምባገነን መንግስታት የፖለቲካና ኢኮኖሚ ድጋፍ በማድረግ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። ለዚህ ደግሞ ከቬኑዙዌላው “Hugo Chavez” እስከ ስሪላንካው “Mahinda Rajapaksa”፣ ከኢትዮጵያው መለስ ዜናዊ እስከ ጅቡቲው “Ismail Omar Guelleh” ያሉ አምባገነን መሪዎችን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። ቻይና ለእነዚህ አምባገነን መሪዎች ከፍተኛ ብድር ሰጥታለች፤ ለቬኑዙዌላ 65 ቢሊዮን ዶላር፣ ለለስሪላንካ ወደ 8 ቢሊዮን ዶላር፣ ለኢትዮጵያ ወደ 12.3 ቢሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ለጅቡቲ 1 ቢሊዮን ዶላር።

በመሰረቱ ጨቋኝና አምባገነን መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ማክበርና ማስከበር የተሳነው ነው። ከላይ በማሳያነት የተጠቀሱት አምባገነን መንግስታት ምዕራባዊያን ፊት የነሷቸው በዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ላይ ጥሰት በመፈፀማቸው ነው። እነዚህ መንግስታት ከምዕራባዊያን ፊታቸውን ያዞሩት በሀገራቱ ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሥር-ነቀል ለውጥና መሻሻል ለማድረግና የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ነው። ስለዚህ ጨቋኝና አምባገነን መንግስታት ከምዕራባዊያን ሀገራትና የገንዘብ ተቋማት ፊታቸውን በማዞር ከቻይና ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የሚመሰርቱት፤ አንደኛ፡- በፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ ለውጥና መሻሻል ላለማምጣት ነው፣ ሁለተኛ፡- የቻይናን ሞዴል በመከተል በሀገራቸው ውስጥ ያለውን የዴሞክራሲ ጥያቄ በኢኮኖሚ እድገት ለመሸንገል ነው። ለዚህ ደግሞ የኢህአዴግ መንግስት ላለፉት 10 አመታት “ኒዮ-ሊብራሊስቶች” እና “በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት” ሲል የነበረውን ማስታወስ ብቻ በቂ ነው።

የኢህአዴግ መንግስት በተለይ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ፤ የምዕራቡ ዓለም መንግስታትን፣ እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ አበዳሪ ተቋማትን፣ በተለይ ደግሞ እንደ “Human Rights Watch” እና “Amnesty International” ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን፣ በምዕራቡ ዓለም የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ የሚዲያ አውታሮችን ጨምሮ ወደ በኢትዮጵያዊያን የተመሰረቱ እንደ ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN) እና የኢትዮጵያ ሳተላይት (ESAT) ያሉ የቴሌቭዥን ጣቢያዎችን፣ እንዲሁም በስደትና በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጦማሪያንን፣ ጋዜጠኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችን፣ …ወዘተ “ኒዮ-ሊብራሊስቶች እና ተላላኪዎቻቸው፣ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ኃይሎች” እያለ በጅምላ ሲፈርጅ እንደነበር የማይካድ ሃቅ ነው። በአንፃሩ ደግሞ ቻይና መንግስት ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነትና ትብብር መስርቶ እንደነበር ይታወሳል።

የኢህአዴግ መንግስት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ከምዕራባዊያን መንግስታት፣ የገንዘብ ተቋማትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ላይ ፊቱን በማዞር የቻይና ጋር የጠበቀ ግንኙነት መስርቶ ነበር። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭትና አለመረጋጋት የኢህአዴግን መንግስት ለሁለት ከፍሎታል። በመጀመሪያ ደረጃ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው አመፅና ተቃውሞ በኦህዴድ ውስጥ የአመራር ለውጥ እንዲመጣ ምክንያት ሆነ። አዲሱ አመራር ደግሞ ከመሪው ድርጅት ኢህአዴግ፣ በተለይ ደግሞ ከህወሓትና ደኢህዴን የተለየ አቋምና አመለካከት ማንፀባረቅ ጀመረ። በመቀጠል ሌላው የኢህአዴግ አባል ድርጅት ብአዴን ከኦህዴድ ጋር የጋራ አቋም ያዘ።

በዚህ መልኩ ልዩነቱ እየሰፋ ሄዶ በ2010 አጋማሽ ላይ የቀድሞ ጠ/ሚ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣን እንደሚለቁ አስታወቁ። ይህን ተከትሎ የተወሰኑ የደኢህዴን ከፍተኛ አመራሮች ከኦህዴድና ብአዴን ጋር በመሆን በአንድ ጎን ሲቆሙ፣ የቀሩት የደኢህዴን አመራሮችና ጥቂት የብአዴን አመራሮች ከህወሓት ጋር በመሆን በሌላ ጎን ቆሙ። በተለይ ከየካቲት ወር አጋማሽ ጀምሮ የኢህአዴግ መንግስት በኦህዴድ እና ህወሓት መሪነት በሁለት አንጃዎች እየተናጠ ነበር። በእነ ለማ መገርሳ እና ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው ቡድን የህዝቡን ጥያቄ ተቀብለን ተገቢ ምላሽ መስጠት አለብን የሚል አቋም ይዟል። በእነ ዶ/ር ደብረፂዮን እና ሽፈራው ሽጉጤ የሚመራው ቡድን ደግሞ የተጀመረው የለውጥ ንቅናቄ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል የሚንድ ስለሆነ መቀልበስ አለበት የሚል አቋም ይዘዋል።

በዚህ መሃል ቻይና ጅቡቲ ላይ ተቀምጣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተንገዳግዶ እስከሚወድቅ እየጠበቀች ነው። በቻይና ጅብ ስደስተኛ ክፍል በተገለፀው መሰረት አሜሪካኖቹ የፖለቲካ ድጋፍ፣ አረቦቹ ደግሞ ዶላር ተሸክመው በር ላይ ቆመዋል። በህወሓት የሚመራው ቡድን የሀገሪቱን ኢኮኖሚና ፖለቲካ ለአደጋ የዳረገውን መንገድና አካሄድ ላለመልቀቅ ይታገላል። በእነ ዶ/ር አብይ የሚመራው ቡድን ደግሞ ከህወሓት ጋር ያለውን ትንቅንቅ በአሸናፊነት በመወጣት የሀገሪቱን ኢኮኖሚና ፖለቲካ ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በዚህ ግብግብ ውስጥ የፖለቲካ ድጋፍና ዶላር ይዞ የመጣ ወዳጅ ከሰማይ እንደተላከ መና ነው።

አምባሳደር ያማማቶ እና ጠ/ሚ አብይ አህመድ (ከግራ ወደ ቀኝ)

በኢህአዴግ መንግስት ውስጥ የተፈጠረውን ክፍፍል በውይይትና ድርድር ለመዳኘት መሞከር ፈፅሞ የማይቻል ነገር ነው። ምክንያቱም የለውጥና ፀረ-ለውጥ ቡድኖች በምንም አግባብ ሊስማሙና ለጋራ ዓላማ ሊሰሩ አይችሉም። አንዱ ለሌላኛው ወገን ጥያቄና ፍላጎት ትኩረት እንዲሰጥ ለማድረግ እንኳን ከሁለቱ አንዱ አሸናፊ ሆኖ መውጣት አለበት። ስለዚህ አሜሪካኖቹ እና አረቦቹ ከህወሓት/ደኢህዴን እና ከኦህዴድ/ብአዴን አንዱን መደገፍና ሌላውን መግፋት አለባቸው።

በዚህ መሰረት በመጋቢት ወር ላይ በተካሄደው የኢህአዴግ ሊቀመንበር ምርጫ ላይ አሜሪካኖቹ የእነ ለማ መገርሳ እና ገዱ አንዳርጋቸውን ቡድንን በመደገፍ ዶ/ር አብይ አህመድ እንዲመረጥ ያላሳለሰ ጥረት አድርገዋል። በአንፃሩ ለእነ ዶ/ር ደብረፂዮን እና ሽፈራው ሽጉጤ ቡድን ድጋፋቸውን ነፍገዋል። ከዚህ በተጨማሪ የእነ ለማ መገርሳ ቡድን አሸናፊ ሆኖ ከወጣ በኋላ ሳውዲ አረቢያና ዱባይ ኤሜሬት ያዘጋጁትን ዶላር ለዶ/ር አብይ እንሆ በረከት ብለውታል። ከዚህ አንፃር “የእነ ለማ መገርሳ ቡድን አሸናፊ የሆነው በአሜሪካኖች ድጋፍ እና በአረቦች ዶላር ነው” የሚባለው ነገር እንዴት ይታያል። ይህን ደግሞ በቀጣዩ ክፍል በዝርዝር እንመለከታለን።