“የቻይና ጅብ” ክፍል 6፡ አሜሪካኖቹ የፖለቲካ ድጋፍ፣ አረቦቹ ዶላር ይዘው መጡ!

በዚህ አመት መጋቢት ወር ላይ በአሜሪካ ምክር ቤት የጦር ጉዳዮች ኮሚቴ አባላት በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር ዋና አዛዥ ከሆኑት ጄኔራል ጋር ያደረጉትን ውይይት የሚያሳይ ቪዲዮ “የቻይና ጅብ” ክፍል አምስት ላይ ማውጣታችን ይታወሳል። የምክር ቤቱ አባላት ለጄኔራሉ ካነሱት ጥያቄና ካንፀባረቁት አቋም፣ እንዲሁም ጄኔራሉ ከሰጡት ምላሽና ማሳሰቢያ አንፃር የአሜሪካ መንግስት በጉዳዩ ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወስድ በቀላሉ መገመት ይቻላል። በተለይ አንድ ምክር ቤት አባል ጉዳዩ የአሜሪካን ጥቅም ከማስከበር ባለፈ የአፍሪካ ሀገራት በዕዳ ጫና ምክንያት ሉዓላዊነታቸው በቻይና እንዳይገፈፍ መከላከል እንዳለባቸው በግልፅ ተናግረዋል።

በእርግጥ ቻይና ጅቡቲን በዕዳ ጫና ውስጥ በማስገባት የራሷን የጦር ሰፍር ከመገንባት አልፎ የሀገሪቱን ወደብ ሲያስተዳድር የነበረውን የዱባይ ኩባንያ በማስወጣት በእጇ አስገብታለች። እ.አ.አ. ከ2000 – 2014 ባሉት አመታት ውስጥ አንጎላ 21.2 ቢሊዮን ዶላር፣ ኢትዮጵያ ደግሞ 12.3 ቢሊዮን ዶላር ከቻይና ብድር ወስደዋል። አንጎላ ነዳጅ ላኪ ሀገር እንደመሆኗ የዕዳ ጫናው ዝቅተኛ ነው። የኢትዮጵያ ዕዳ ጫና ግን 59% እንደመሆኑ የሉዓላዊነት ዕዳ (Sovereign debt) ለመሆን 1% ብቻ ነው የቀረው። ስለዚህ የአሜሪካ ምክር ቤት የጦር ጉዳዮች ኮሚቴ አባላት የአፍሪካ ሀገራትን ሉዓላዊነት ከቻይና የብድርና ዕዳ ጫና መከላከል አለብን ሲሉ ዋና ትኩረታቸው ኢትዮጵያ እንደሆነች ምንም ጥርጥር የለውም።

ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ወደብ ከሆነች ኢትዮጵያም የአፍሪካ ወደብ ናት። የቻይና መሰረታዊ ዓለማ የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ የሚካሄድበትን ወደብ መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መሪዎች መግቢያና መውጫ የሆነችውን ኢትዮጵያን በቁጥጥር ስር ማዋል ነው። ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤትን በራሷ ወጪ መስራቷ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። ይህንን የአሜሪካ ምክር ቤት የጦር ጉዳዮች ኮሚቴ አባላት ጭምር ቻይና በአፍሪካ ሀገራት ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ የተጠቀመችበት ስልት እንደሆነ ተናግረዋል። የኮሚቴው አባላት በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ጄኔራል ጋር ያደረጉት ውይይት ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ይታወሳል። በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ቻይና የአፍሪካ ሀገራትን በዕዳ ጫና በማንበርከክ ሉዓላዊነታቸውን እየገፈፈች እንደሆነ በግልፅ ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት የቻይናን የኢምፔራሊዝም ወይም የእጅ አዙር አገዛዝ ለመግታት በግልፅ እየተንቀሳቀሰ ጀምሯል። በዚህ ረገድ ቀዳሚው ተግባር የጀመረው ኢትዮጵያን ከቻይና ጅብ መታደግ ነው። በዚህ ረገድ “የአሜሪካ መንግስት ምን ዓይነት እርምጃዎች ሊወስድ ይቻላል?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በቅድሚያ በዚህ አመት የካቲትና መጋቢት ወር ላይ በኢትዮጵያ የነበረውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መለስ ብሎ መቃኘት ያስፈልጋል። በተደጋጋሚ ለመግለፅ እንደተሞከረው በተለይ ከቻይና መንግስት በተሰጠ ብድር የኢትዮጵያ ዕዳ ጫና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። በመሆኑም የኢህአዴግ መንግስት አንድ ተጨማሪ የብድር ስምምነት ቢፈርም የዕዳ ጫናው ከ60% በላይ ስለሚደርስ በቀጣይ ሀገሪቱ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ብድር መጠየቅ አትችልም።

ስለዚህ የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመታደግ፣ ብሎም የአፍሪካ አህጉር በቻይና የእጅ አዙር ቁጥጥር ስር እንዳይወድቅ ለማድረግ በውጪ ምንዛሬ እጥረት እያቃተተ ያለውን ኢኮኖሚ መደጎም አለበት። አሁን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚፈልገው ብድር ሳይሆን ከወለድና ቅድመ-ሁኔታ ነፃ የሆነ “ድጎማ” (Subsidy) ነው። ነገር ግን አሜሪካ በየአመቱ ለኢትዮጵያ 1.11 ቢሊዮን ዶላር እንደምትሰጥ ይታወቃል። ከዚህ በተረፈ እንደ ቻይና የፈለገውን ብድር ሆነ እርዳታ መስጠት አይችልም። የቻይና መንግስት ግን ለምሳሌ እ.አ.አ. በ2012 ዓ.ም 78 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰጥቶ በቀጣዩ አመት ደግሞ 6.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር መስጠት አይችልም።

አሜሪካ፣ ሳውዲ አረቢያና ዱባይ ኤሜሬት
የአሜሪካ መንግስትና ተቋማት አሰራር በአብዛኛው ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበት በመሆኑ እንደ ቻይና የፈለገውን ያህል ዶላር በችሮታ ሆነ በስጦታ መስጠት አይችልም። ይሁን እንጂ፣ አሜሪካ እንደ ቻይና የፈለጉትን ያህል መዥረጥ አድርገው ለመስጠት የሚያስችል መንግስታዊ አሰራርና የሚሰጥ ዶላር ያላቸው ወዳጆች አሏት። እነዚህ የአሜሪካ ወዳጅ ሀገሮች ሳውዲ አረቢያና ዱባይ ኤሜሬት ናቸው። አሜሪካ፣ ሳውዲ አረቢያ እና ዱባይ ኤሜሬት በጅቡቲ ጉዳይ ከቻይና ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል።

U.S. President Donald Trump and Saudi Arabia’s King Salman bin Abdulaziz Al Saud attend the Arab Islamic American Summit in Riyadh, Saudi Arabia on May 21, 2017.JONATHAN ERNST / REUTERS)

ቻይና ጅቡቲን በዕዳ ጫና ሰቅዛ በመያዝ ዱባይ ኤሜሬትን አስወጥታለች። የአሜሪካ ምክር ቤት የጦር ጉዳዮች ኮሚቴ አባላት “AMISOM” ዋና አዛዥ ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች አንዱ “ጅቡቲ የተስማሙበትን ውል በመጣስ ዱባይ ኤሜሬትን ከሀገሯ ካስወጣች፣ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ስምምነት በመጣስ ከጅቡቲ ብታስወጣንስ?” የሚል ነበር። የዱባይ ኤሜሬትን ዕጣ ፈንታ የተመለከተችው ሳውዲ አረቢያ ተመሳሳይ ጥያቄ ማንሳቷ አይቀርም። ስለዚህ አሜሪካ፣ ሳውዲና ዱባይ ጅቡቲ ውስጥ የጋራ ጠላት አላቸው። ከዚህ በተጨማሪ ጅቡቲ ለሦስቱም ሀገራት ስትራቴጂካዊ ቦታ ናት። ምክንያቱም ሦስቱ ሀገራት በየመን ከሚንቀሳቀሱ አማፂያን ጋር በሚያደርጉት ጦርነት በጦር ጀትና ሰው-አልባ አውሮፕላን ድብደባ የሚፈፅሙት ጅቡቲ ከሚገኘው የጦር ሰፈር ነው። በዚህ አመት የካቲት ወር ላይ ግን ዱባይ ኤሜሬት ከጅቡቲ ስትባረር፣ አሜሪካና ሳውዲ አረቢያ ደግሞ ተመሳሳይ አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለቻይና ያለባት የብድር ዕዳ በሚፈለገው ግዜ መክፈል ካቃታት በመጀመሪያ ከቻይና በተገኘ 3 ቢሊዮን ዶላር የተሰራውን የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር በብድር ማስያዣነት እንዲሰጣት መጠየቋ አይቀርም። ይህን ደግሞ ቻይና በፓኪስታን፣ ኔፓልና ማይነማር ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን በሲርላንካ እና ጅቡቲ በሰጠችው ብድር የተገነቡ ወደቦችን በቁጥጥሯ ስር በማዋል በተግባር አረጋግጣለች። ስለዚህ ይህ የኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ-ፋንታ መሆኑ አያጠራጥርም። ኢትዮጵያ ለቻይና ያለባትን ዕዳ መክፈል ካቃታትና የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርን ወይም ሌላ ማስያዢያ ለመስጠት ፍቃደኛ ካልሆነች ደግሞ በጅቡቲ በኩል ያለውን የወጪና ገቢ ንግዷ በቻይና ሲጥ ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪ ጅቡቲ ካለው የቻይና የጦር ሰፈር ወታደራዊ እርምጃ እስከመውሰድ ልትደርስ ትችላለች።

በዚህ መሰረት ቻይና ጅቡቲ ውስጥ እያደረገችው ያለው ነገር ለአሜሪካ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ዱባይ ኤሜሬት፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቀጥተኛ አደጋ አለው። ቻይና ከጅቡቲ አልፋ ኢትዮጵያን መቆጣጠር ከቻለች ደግሞ አሜሪካና አጋሮቿ በአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ያላቸውን አቅምና የበላይነት ሙሉ በሙሉ ያበቃለታል። ስለዚህ የቻይናን እንቅስቃሴ ለመግታት ኢትዮጵያን ከዕዳ ጫና ነፃ ማውጣት ምርጫና አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። በዚህ መሰረት አሜሪካ ዋናነት በፖለቲካው ረገድ፣ ሳውዲ አረቢያና ዱባይ ኤሜሬት ደግሞ በነዳጅና ዶላር ኢትዮጵያን ለመታደግ መረባረብ ጀመሩ። በዚህ አመት መጋቢት ወር ላይ አሜሪካኖቹ እና አረቦቹ የፖለቲካ ድጋፍ እና ዶላር ተሸክመው ሲመጡ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ለሁለት ጎራ ላይተው እርስ-በእርስ የለየለት ግብግብ ውስጥ ገብተዋል። አሜሪካኖቹና አረቦቹ ይዘውት የመጡትን ድጋፍና ዶላር ለማን እንደሚሰጡት ጋራ ገባቸው።

2 thoughts on ““የቻይና ጅብ” ክፍል 6፡ አሜሪካኖቹ የፖለቲካ ድጋፍ፣ አረቦቹ ዶላር ይዘው መጡ!

  1. 6ቱንም ከፍል በጥሞና አነበብኩት ውስጤ በመገረም ሳይሆን በንዴት ጦፈ
    ስዩሜ ለጥረትህ የበዛ ምስጋና ይገባሀል እውነተኛ መምህር እንዲህ ነው

    Like

  2. ዘይገርም ነው!ሀገሪቷ እንዲህ ብሄራዊ አደጋ እስኪጋረጥባት ድረስ የብድር ፓሊሲ አልነበራትም? ብሎ መጠየቅ ማላገጥ ነው የሚሆንብኝ..ጽሁፎችህን ግን በተለያየ መንገድ ህዝቡጋ እንዲደርስ ማድረጉ አስፈላጊ ነው።እናመሰግናለን!

    Liked by 1 person

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡