“የቻይና ጅብ” ክፍል 8፡ በአሜሪካና አረቦች ድጋፍ መፈንቅለ-መንግስት ተደርጓል?

የቻይና ጅብ ክፍል 7 ላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ቻይና እና አሜሪካ ጅቡቲ ላይ የጀመሩት ፍጥጭ በኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በተለይ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ ህወሓት/ደኢህዴን የአስቸኳይ ግዜ በማወጅ የለውጡን እንቅስቃሴ በኃይል ለማፈን፣ ኦህዴድ/ብአዴን ደግሞ የኢህአዴግን ሊቀመንበርነት ቦታ በመያዝ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ሽኩቻ ውስጥ እንደነበሩ ይታወሳል።

በዚህ የኃይል ሽኩቻ ውስጥ ማንኛውም ዓይነት ድጋፍና ተቃውሞ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ከወትሮው የጎላ ነው። በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የአሜሪካና የአረብ ሀገራት ድጋፍ የኃይል ሚዛኑን እንደሚቀይረው ምንም ጥርጥር የለውም። በወቅቱ የአሜሪካ መንግስት ኃላፊዎችና ተቋማት ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ እንዲመረጥ በመጀመሪያ በውስጥ-ለውስጥ፣ ወደ መጨረሻ አከባቢ ደግሞ በግልፅ ድጋፋቸውን ገልፀዋል። ሳውዲ አረቢያና ዱባይ ኤሜሬት ደግሞ ከምርጫው ውጤት በኋላ የውጪ ምንዛሬ እጥረቱን በመቅረፍና የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ያሳዩትን ድጋፍ ተመልክተናል።

በዚህ መሰረት የአሜሪካኖች ድጋፍ እና የአረቦች ማበረታቻ ከምርጫው በፊት ህወሓት/ደኢህዴን የነበረውን የስልጣን የበላይነት እንዲያጣ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በመሆኑም ይህ አሜሪካኖቹና አረቦቹ በሂደቱ ውስጥ የነበራቸው ሚና እንደ መፈንቅለ መንግስት ሊወሰድ ይችላል? ይህን ጥያቄ ለመመለስ በ2010 ዓ.ም የመጋቢት ወር ሁለቱ ቡድኖች የነበራቸውን አቋምና የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የመፍታት አቅም መመልከት ያስፈልጋል።

በመጀመሪያ ህወሓት/ደኢህዴን በሀገሪቱ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ችግር በኢኮኖሚ እድገት መግታት/መፍታት ይቻላል የሚል አቋም አለው። ይህ ደግሞ ከ1997ቱ ምርጫ ጀምሮ በተግባር ሲከተለው የነበረ የቻይና ሞዴል ነው። ነገር ግን በዚህ ሞዴል መሰረት ሀገሪቱ ምንም ያህል ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ብትችል ከጥቂት (በአማካይ ከአስር) አመታት በኋላ የዴሞክራሲ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ በኢኮኖሚ እድገት አማካኝነት የሚገኘው ቁሳዊ ሃብትና ንብረት በሕብረተሰቡ ዘንድ ያላቸው ዋጋ እየቀነሰ ይሄዳል። ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ በተመሳሳይ የሽግግር ወቅት ላይ በነበረችበት ወቅት የተሰራ ጥናት ሁኔታውን እንደሚከተለው ይገልፃል፡-

“…it can be generalized that a bureaucratic authoritarian regime will not be efficient unless it can co-opt societal interests, especially when prolonged economic success nullifies the effectiveness of material gains at the cost of political freedom” LEE, J (1991) POLITICAL LIBERALIZATION AND ECONOMIC DEVELOPMENT IN SOUTH KOREA

ሁለተኛው ምክንያት የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት የሚኖረው አዳዲስ ፈጠራዎችና ቴክኖሎጂዎች፣ የምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ አዳዲስ ሥራዎችና አሰራሮች ሲኖሩ ነው። ነፃ የመረጃ ፍሰት በሌለበት፣ ዜጎች ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት መግለፅ፣ በራሳቸው ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ በማይቻሉበት ፖለቲካዊ ስርዓት ውስጥ ለአዳዲስ ፈጠራዎች እና ሥራዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር አይቻልም። በዚህ ምክንያት የኢኮኖሚ እድገቱ መቀዛቀዝ ይጀምራል። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት ከ2003 – 2014 (1995 – 2006) ዓ.ም ፍጥነት በምን ያህል ፍጥነት እየቀነሰ እንደመጣ ከታች ካለው ምስል መመልከት ይቻላል።

ምስል 3፡ የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት፣ ከ2003 – 2014 (1995 – 2006) ዓ.ም
ምንጭ፡- www.tradingeconomics.com
በዚህ ምክንያት ዜጎች የሚያነሷቸውን የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በአግባቡ ላለመመለስ ፊቱን ከምዕራባዊያን ወደ ቻይና የመለሰው የህወሓት/ደኢህዴን ቡድን የአሜሪካኖች ድጋፍና የአረቦችን ዶላር ቢሰጠው እንኳን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠል አይችልም። በመሆኑም ላለፉት አስር አመታት ሲከተለው የነበረውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሞዴል ለማስቀጠል የሚሻው ቡድን የፈለገውን ያህል ድጋፍና ማበረታቻ ቢደረግለት የዜጎችን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ አይችልም።

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የተቀሰቀሰው አመፅና ተቃውሞ በ1997 የነበረው የዴሞክራሲ ጥያቄ ቀጣይ ነው። ስለዚህ በህወሓት የሚመራው ቡድን፤ አንደኛ፡- የኢኮኖሚ እድገቱን ማስቀጠል አይችልም፣ ሁለተኛ፡- የዜጎችን የዴሞክራሲ ጥያቄ ተቀብሎ ማስተናገድ አይችልም። የአንድን ሀገር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት የማይችል የፖለቲካ ቡድን ደግሞ በቁሙ ሞቱ የበሰበሰ ነው። እንዲህ ያለ ቡድንን መደገፍ ሆነ ማበረታታት ምንም ፋይዳ የለውም።

በእርግጥ ዛሬ ላይ ሆኖ “በህወሓት የሚመራው ቡድን በቁሞ የሞተ ነው” ማለት “የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል” የሚሉት ዓይነት ይመስላል። ሆኖም ግን እኔ በበኩል ዛሬ ላይ “በህወሓት የሚመራው ቡድን በቁሙ ሞቷል” ብዬ መናገር የምችል ይመስለኛል። ምክንያቱም ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ በማወጣቸው ፅሁፎች ህወሓት መራሹ ቡድን በቁሙ እየሞተ እንደሆነ ገልጪያለሁ። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን በግዜ ቅደም ተከተል በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

የኢህአዴግ መንግስት በ2002ቱ ምርጫ 99.6%፣ በ2007ቱ ደግሞ 100% ‘አሸነፍኩ’ ብሎ መሳለቁ ይታወሳል። በተለይ የ2007ቱ ምርጫ ውጤት ይፋ እንደተደረገ “100% የምርጫ ቅሌት እንጂ ውጤት አይባልም” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ “ይሄ 100% ተብዬ ነገር’ኮ…ህዝቡ ሰላማዊ ፖለቲካ፣ በሕግ የበላይነት እና በሌሎች ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ላይ ያለውን እምነት ሽርሽሮ በመናድ ዴሞክራሲን በጭቅላቱ ዘቅዝቆ ያቆመ ነው” ብዬ ነበር።

ከ2008 ዓ፣ም ጀምሮ ባለው ግዜ ውስጥ ብቻ በሕዝቡ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የታየው ለውጥ የሩብ ምዕተ አመታት ያህል ሰፊ ነው። 3ኛው ማዕበል በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ የህዝቡ ጥያቄና እንቅስቃሴ ተፈጥሯዊ የለውጥ ሂደትን ተከትሎ የመጣ እንደመሆኑ አይቀሬና አስገዳጅ ነው። በዚህ ፈጣን የለውጥ ሂደት ውስጥ ባለበት የቆመነገር ቢኖር የኢህአዴግ መንግስት ብቻ መሆኑን ጠቁሜያለሁ። የለውጥ ጥያቄ ለማስቆም መሞከር ከትውልድ ጋር ግጭት ውስጥ መግባት ነው። ስለዚህ በመሆኑም የኢህአዴግ መንግስት የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኛ ከሆነ የለውጡ መነሻና መድረሻ እና የለውጡ ዝርዝር ተግባራትን ለመጠቆም ሞክሬያለሁ።

ህወሓት/ኢህአዴግ በሀገሪቱ የፖለቲካ ላይ ያለውን የበላይነት ለማረጋገጥ ያለው ብቸኛ አማራጭ ለሕገ መንግስቱና መንግስታዊ ስርዓቱ ጥብቅና መቆም እንደሆነና ይህ ሀገሪቱን ወደ የእርስ በእርስ ግጭትና እልቂት ሊያስገባት እንደሚችል ጠቁሜያለሁ። የኢህአዴግ መንግስት “ጥልቅ ተሃድሶ” በራሱ ማላገጥ ሲጀምር “ኢህአዴግ እና ፀጉራም ውሻ አንድ ናቸው” በማለት የኢህአዴግ መንግስት ከለውጥ ይልቅ ሞትን እንደመረጠና እንደ ፀጉራም ውሻ ሳይታወቅለት ውስጥ-ውስጡ እየሞተ እንደሆነ ገልጩያለሁ። በመጨረሻም የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ከለውጥ ወይም ሞት ሞትን እንደመረጠ ገልጬያለሁ።

በአጠቃላይ ከፖለቲካ አንፃር ከ2010 ዓ.ም የጥቅምት ወር ጀምሮ የህወሓት/ደኢህዴን ቡድን በቁሙ ሞቷል። እንዲህ ያለ ቡድንን መደገፍ ኪሳራ ነው። በተመሳሳይ በእንዲህ ያለ ቡድን ላይ መፈንቅለ-መንግስት ማድረግ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” የሚሉት ዓይነት ነው። እነሱን ከስልጣን ለማውረድ የሚያስፈልግ ነገር ቢኖር በመከላከያና ደህንነት ተቋማት ላይ ተለጥፈው ኪራይ የሚሰበስቡና ኮንትሮባንድ ሲነግዱ ጥቂት ባለስልጣናትን ከኃላፊነት ማንሳት ብቻ ነበር። ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ የኢህአዴግ ሊቀመንበርነትን ቦታን የህወሓት መጠቀሚያ ከነበረው ደኢህዴን እጅ ማውጣት ነው። ይህ ደግሞ የሆነው አራቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተሳተፉበት ምርጫ ነው። ምርጫው የተካሄደው ህወሓትና ደኢህዴን አመራሮች ባሉበት እንደመሆኑ በምንም አግባብ መፈንቅለ-መንግስት ሊባል አይችልም።

በእርግጥ አሜሪካና አረቦቹ ለእነ ዶ/ር አብይ እና ለማ መገርሳ በውስጥ-ለውስጥና በይፋ ድጋፋቸውን ገልፀዋል። ምክንያቱም የእነሱ አመራር ኢትዮጵያን ከቻይና ጅብ ይታደጋታል። የህዝቡን ጥያቄ ከህወሓት/ደኢህዴን በተሻለ ይመልሳል። በዚህ ሂደት የአሜሪካና አረቦቹ ጥቅም ሊከበር ይችላል። ነገር ግን አሜሪካና አረቦቹ ድጋፋቸውን ለህወሓት/ደኢህዴን ቢሰጡ ኖሮስ? በመጀመሪያ ደረጃ ቀድሞ ወደ ቻይና ፊታቸውን ያዞሩት ከአሜሪካኖች የዴሞክራሲ ጥያቄና የብድር አሰጣጥ መስፈርት ለመሸሽ እንደመሆኑ እንዲህ በቀላሉ ከቻይናዎቹ አይላቀቁም፣ በአንፃሩ ከአሜሪካኖቹ ጋር አይቀራረቡም። ሁለተኛ ከህዝቡ እየተነሳ ያለውን የመብትና ዴሞክራሲ ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ መስጠት አይችሉም። ሦስተኛ የፖለቲካውን ጥያቄ ሳይመልሱ የኢኮኖሚ እድገቱን ማስቀጠል አይችሉም። በመሆኑም ከቻይና ተፅዕኖ ነፃ ከመውጣትም ሆነ የሀገሪቱን ሕዝብ ጥያቄ ከመመለስ አንፃር ቁርጠኛ አቋምና አስፈላጊው አቅም የላቸውም።

ስለዚህ አሜሪካኖቹና አረቦቹ፤ ባይደግፉት የሚወድቅ፥ ቢደግፉትም መቆም የማይችል የፖለቲካ ቡድን ላይ መፈንቅለ-መንግስት የሚያደርጉበት ምክንያት ምንድነው? በራሱ ግዜ የወደቀ ነገር ይገላበጣል እንጂ አይፈነቀልም። “በአሜሪካና አረቦች የተደገፈ መፈንቅለ-መንግስት ተደረገብን” የሚባለው ነገር ራሱን-በራሱ ገዝግዞ የጣለ ቡድን ሽንፈቱን አምኖ ላለመቀበል የፈጠረው ተረት-ተረት ነው።

One thought on ““የቻይና ጅብ” ክፍል 8፡ በአሜሪካና አረቦች ድጋፍ መፈንቅለ-መንግስት ተደርጓል?

  1. Smart conclusion. Thank u for sharing us your view. I know writing is difficult. Criticising ones work is easy. both run after benefit. Choosing both is like choosing from the worst. So what shall we do? ?? You cannot escape them

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡