“በመንግስት አመራር ውስጥ ‘እኔ አውቅላችኋለሁ’ የሚል ደዌ ተጠናውቶን ቆይቷል” አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምሁራን መድረክ ያድረጉት የመክፈቻ ንግግር

============================

  • ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር
  • የተከበራችሁ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች!

እንኳን ወደ አማራ ክልል መዲና ውቢቷ ባህርዳር ከተማ በሠላም መጣችሁ!

ከነገሬ ሁሉ በማስቀደም የአማራ ክልል መንግስት እና ህዝብ የጐደለውን ትሞሉለት ዘንድ ምክራችሁን እና የሙያ ድጋፋችሁን በመሻት ለልጆቹ ያደረገውን ይህን ታሪካዊ ጥሪ ያለምንም ማቅማማት ተቀብላችሁ እዚህ በመካከላችን በመገኘታችሁ ከልብ የመነጨ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡

የአማራ ክልል ፕረዘዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

በረጅሙ የሃገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የአማራ ህዝብ በስልጣኔ፣ በተለይም በመንግስት አስተዳደር፣ በታሪክ፣ በኪነ-ጥበብ፣ በስነ-ፅሁፍ፣ በአርበኝነት ተጋድሎ እንዲሁም በኢኮኖሚ ዕድገት ለሃገር ያበረከተው ድርሻ ትልቅና አይረሴ ቢሆንም ያለፈው ግማሽ ምዕተ-ዓመት በዘመናዊ ትምህርት የጐለመሰው የክልሉ ተወላጅ ቁጥሩ ከፍ እያለ የመገኘቱን ያክል ተሣትፎው ግን እየቀዘቀዘ መጥቷል፡፡

ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ አሳታፊ /አካታች/ የመንግስት አስተዳደር አለመኖሩና በመንግስት አመራር ውስጥ “እኔ አውቅላችኋለሁ” የሚል ደዌ ተጠናውቶን መቆየቱ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በሁሉም የሙያ ዘርፍ አንቱ የሚባሉና ለሃገራችንም ሆነ ለዓለም የተረፋ ምርጥ ምሁራን ለፈለቁበት የአማራ ህዝብ “የዐባይን እናት ውሃጠማት” እንደሚሉት አይነት ሆኖበት ቆይቷል፡፡ በመመካከር ፈንታ መወቃቀስ፣ በመደጋገፍ ፈንታ መገፈታተር፣ በፍቅር አብሮ መሥራት እና አብሮ መብላት የአባት አደር ሆኖ ሳለ የአንድነትና ወንድማማችነት ጽዩፋን እየሆን እንገኛለን፡፡

ለዚህ ሁሉ ችግር ተወቃሽ ባይጠፋም ወቃሽ ሆኖ መቅረብ የሚችለው ግን ትልቁ የአማራ ህዝብ ብቻ በመሆኑና የህዝባችን ዐቢይ ፍላጐትም ሁላችንም የምንችለውን ያክል ሠርተን ከችግር እንድናወጣው ሥለሆነ ዛሬ በመካከላችሁ የቆምኩት ይህንኑ ጥሪ ለማሥተላለፍ ብቻ ነው፡፡

ወንድሞች እና እህቶች !!

መማር ማለት በርካታ መፃህፍትን ውጦ መቀመጥ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ መማር በዩኒቨርሲቲ በሚሰጥ የሊቅነት ማረጋገጫ ወረቀት ብቻ ሊገለጥ አይችልም፡፡ በእኔ እምነት መማር የህዝብን ህመም አብሮ ታሞ መፈወስ መቻል ነው፡፡

ትምህርት የተጨነቀን ህዝብ ከችግር ለማውጣት የሚያስችል መሣሪያ ሆኖ ካልተገኘ ልሂቃን ሲፈልጉት ብቻ የሚጠቀሙበት ተከቶ የተቀመጠ ትርፍ ሃብት ይሆናል፡፡ የክልላችን ህዝብም ይሁን ሃገራችን ዘመናትን ያስቆጠሩ በርከት ያሉ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ችግሮቹን መንግስት ብቻውን ታግሎ ሊፈታቸው እንደማይችል አሣምረን ተረድተናል፡፡ ዛሬ የሁላችሁንም በር ለማንኳኳት ስንወስን ሃገር በዕውቀት እንጂ በልበ ብርሃንነት እንደማይመራ ተገንዝበን ነው፡፡ ሃገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ህዝብ፣ መንግስት እና ባለሃብቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም በዕውቀትና በጥበብ ካልተሳሰሩና ካልተደጋገፋ ወንዝ መሻገር አይችሉም፡፡

ምሁራን ያለችውን እውቀት ወደ ተጨባጭ ጠቀሜታ መቀየር የሚችሉት ብቻቸውን በመጓዝ አይደለም፡፡ ከመንግስት ጋር አብሮ መሥራትም ፖለቲከኛነት አይደለም፡፡ ይልቁንም ዕውቀትን ወደ ህዝብ ለማድረስ ዋነኛ ድልድይ ከሆነው አካል ጋር አብሮ መስራት ነው፡፡ የፖለቲካ ሣይንስ ምሁራን እንደሚናገሩትም የአንፃራዊነት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከፖለቲካ ፈፅሞ ነፃ የሆነሰው የለም፡፡

ስለሆነም ተገቢነት የሌለውን የፖለቲካ ሃሜት በመፍራት ወይም ይህንኑ ሰበብ በማድረግ መራራቅ ለማናችንም አይበጀንም፡፡ ተራርቀን አይተነዋል፤ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ገድል መፈፀም የሚያስችል እውቀትና ችሎታ እያለን “የጋን መብራት” ከመባል አላለፍንም፡፡ መለያየት፣ ፊት መዟዟር፣ በአለፈው ታሪካችን መወቃቀስም ሆነ የይስሙላ መቀራረብ ይብቃን፡፡

የአማራ ህዝብ ችግር የሚፈታው ከልብ የመነጨ ፍቅር፣ አንድነት፣ እውነተኛ እህትማማችነትና ወንድማማችነት በመካከላችን ሲገነባ ነው፡፡ አማራ ክልል ፀጋው ያልተጓደለበት፣ ሁሉም ዘርፍ እንስራ ብንል ልማትን ለማምጣትና ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ወሳኝ የሚባል የሃብት መሠረት ያለው ክልል ነው፡፡ በእስካሁኑ ጉዟችን በገባን ልክ ህዝቡን ከድህነት ለማላቀቅ ያቅማችንን ተፍጨርጭረናል፡፡ ያም ሆኖ ያስመዘገብነው ውጤት ህዝባችን ሙሉ በሙሉ ከችግር ያላቀቀ አይደለም፡፡ የምናደርገው ሩጫ ብልሃት ቢጨመርበት፣ በዕውቀት ቢደገፍ ድህነት ከክልላችንና ከሃገራችን የሚቆይበት እድሜ በብዙ እጥፍ ሊያጥር ይቻል እንደነበር አሣምረን እንገነዘባለን፡፡

የምናደርግላችሁ ጥሪ የይስሙላ አይደለም፣ ታሪካዊ ግዴታችሁ የሆነውን ይህን የአብረን እንስራ የጥሪ ደወል ሠምታችሁ በአንድነት በመሠባሰብና በተግባር አብሮ ለመራመድ ለቆረጣችሁ ምንጊዜም ከጐናችሁ በመሆን ለዚህ ተግባር የሚያስፈልገውን የመንግስት አገልግሎት በቀናነት ለመስጠት ዝግጁ ነን፡፡ ይህ አጋጣሚ ለእናንተ ግዴታ አይደለም፡፡ ይልቁንም ለረጅም ጊዜ ስትመኙት የነበረ ዕድል እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ዕድሉን መስጠት እና ሁኔታውን ማመቻቸት የመንግስት ድርሻ ቢሆንም መጠቀም ግን የእናንተ ብቻ ነው፡፡ ለመተባበርም ታሪክ ለመቀየርም እኔና እናንተ ከማንም አናንስም፡፡ ሳናጣ የጐደለብን፣ ሣይነጥፍ የደረቀብን፣ እያለን እንደሌለን የምንቆጠር ደካሞች አይደለንም፡፡

እኛ የጠፋውን የማልማት፣ የጐበጠውን የማቃናት፣ የተቋጠረውን የመፍታት፣ የተወሳሰበውን መልክ የማስያዝ ብቃትና ተሠጥኦ ያለን ልዩ ልጆች ነን፡፡ አንድ ሆነን በመስራት ከእኛ አልፈን ለሃገርም የሚበቃ ትሩፋት መፍጠር እንችላለን፡፡ እነሆ መንገዱ ተከፍቷል፣ የጥላቻ መጋረጃውም ተቀዷልና በመሃሉ በመመላለስ ቤታችንን ቤት እናድርገው፡፡

በድጋሜ አክብራችሁን ስለተገኛችሁ እያመሰገንኩ በዚህ አጋጣሚ ይህ ታሪካዊ የምሁራን መማክርት ጉባዔ እንዲቋቋም ምሁራን ለክልሉ ህዝብ ዕድገት የቻሉትን ሁሉ እንዲሰሩ በሚያዚያ ወር በዚሁ በባህር ዳር ከተማ ተገናኝተው ታሪካዊ መሠረት ድንጋይ ያስቀመጡ ምሁራንና በዚሁ ጉባዔ በተላለፈው ውሣኔ መሠረት የመማክርት ጉባዔ ለማዘጋጀት አስፈላጊ የሆኑ መነሻ ጽሁፍ ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ እና ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ትክክለኛ የሆነውን የምሁራን ትጋት በአሣዩን እና የአንድነት ተምሣሌት በመሆን ሌት ተቀን ለሰሩ የኮሚቴ አባላት ያለኝን ምስጋና ለማቅረብ ቃላት የለኝም፡፡ በተጨማሪም ከዚህ መማክርት ጉባኤ መክፈቻ ቀን ቀደም ብሎ በሙያቸው በመደራጀት የክልሉን የግብርና ልማት ዘርፍ ለማገዝ ሥራ ለጀመሩ የግብርና ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች ላሳዩት ቁርጠኝነት ከልብ የመነጨ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡
=አመሰግናለሁ!!!=
ምንጭ፦ የአቶ ንጉሱ ጥላሁን ፌስቡክ ገፅ