እንደ አቶ በረከት ስምዖን ያለ ሰው “ለምን አለ?” እንጂ “ምን አለ?” አይባልም!

በብአዴን መታገዳቸውን ተከትሎ አቶ በረከት ስምዖን በተለያዩ ሚዲያዎች ብዙ ነገር ተናግረዋል፡፡ አቶ በረከት የተናገሩትን ነገር ብቻ ወስዶ ምላሽ ለመስጠት መሞከር ስህተት ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ የግለሰቡን ማንነት፥ ስብዕና እና ግል-ታሪክ መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህ አቶ በረከት ስምዖን ማን ናቸው? ምን ዓይነት ስብዕና አላቸው?

አቶ በረከት ስምዖን

ስለ በረከት ስምዖን ማንነት ለማወቅ በቅድሚያ የቀድሞ የስራ ባልደረባቸው አቶ ኤርሚያስ ለገሰ “ጥላሁን ያረፈ ቀን” ከሚለው መጽሐፉ ቀንጭቦ በፌስቡክ ገፁ ያወጣውን ፅሁፍ እንመልከት፡፡ እንደ ኤርሚያስ አገላለፅ አቶ በረከት ከወላጆቹ የመጤነት ስሜት የሚሰማቸው፣ ከአስተዳደጋቸው ጀምሮ የበታችነትና የተፈላጊነት ስሜት የተጠናወታቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አቶ በረከት ከ11ኛ ክፍል ማለፍ የተሳናቸው ሆኖ ሳለ በተጭበረበረ መንገድ የሁለተኛ ድግሪ እንዳላቸው ተገልጿል፡፡

ከላይ በተገሰፀው መሠረት አቶ በረከት ባህሪያትና ስነ-ልቦና ስልጣን ላይ ሙጭጭ እንዲሉ ያደርጋቸዋል፡፡ እንደ በረከት ያሉ ሰዎች ስልጣንን ለሕዝብ ጥቅምና አገልግሎት ከማዋል ይልቅ እንደ ክብርና ዝና ስለሚቆጥሩት፣ ከስልጣን ውረዱ ሲባሉ ክብርና ሞገሳቸው ተገፎ እርቃናቸውን የቆሙ ይመስላቸዋል። በመሆኑም ከስልጣን መውረድ ልክ እንደ ሞት ያስፈራቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አቶ በረከት “የአመራር ወጥመድ” (Leadership Trap) የተጠለፉ ናቸው። በአመራር ወጥመድ ተጠልፈው የወደቁ ባለስልጣናት መሰረታዊ ችግር ከማህብረሰቡ የሚሰጣቸውን ትችትና አስተያየት ለመቀበል ዝግጁ አይደሉም። እንደ አምላክ ፍፁም መሆን ይቃጣቸዋል። በዚህ ምክንያት በስህተት ላይ ስህተት እየሰሩ፤ “ተሳስታችኋል” ሲባሉ አይሰሙም፣ “ተሳስተናል” ብለው አያምኑም።

ከላይ በተገለፀው መሠረት የአቶ በረከት አስተዳደግ፣ ስብዕና እና የዕውቀት ደረጃ ለፖለቲካ አመራርነት አያበቃም፡፡ በበታችነት ስሜት ውስጥ ያደገ ሰው ስር-የሰደደ የጥላቻ አመለካከት እና የቂም-በቀል ስሜት ይኖረዋል፡፡ የተፈላጊነት ስሜት ወደ አጎብዳጅነትና ቃላባይነት ይቀየራል፡፡ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ደግሞ በሂደት አስመሳይነትና አገልጋይነት ያስከትላል፡፡ እንግዲህ አቶ በረከት ስምዖን ማለት በጥላቻና ቂም-በቀል የሚመራ፣ አስመሳይና በውሸት የተካነ፣ አጎብዳጅና በአገልጋይነቱ የሚመፃደቅ ሰው ነው፡፡

እንደ አቶ በረከት ዓይነት አስተዳደግና ስብዕና ያለው ግለሰብ በሸርና አሻጥር፣ በክፋትና ውሸት የተካነ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አቶ በረከት ስምዖን ከተለያዩ ሰዎች ጋር የነበራቸውን ግንኙት እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አቶ በረከት ለቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ፍፁም አጎብዳጅና አገልጋይ ነበሩ፡፡ የአቶ መለስ አምላኪ ከመሆናቸው በተጨማሪ በንፁሃን ላይ በሚፈፀም ሸርና ደባ በቀጥታ ይሳተፋሉ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን የሚታወቁት አቶ አሰፋ ጫቦ ከሀገር እንዲሰደዱ ለማድረግ የተሸረበውን ደባ የጠነሰሱት አቶ መለስ ዜናዊ እና በረከት ስምዖን መሆናቸውን የቀድሞ ባልደረባቸው አቶ ተስፋዬ ገብረዓብ “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” በሚለው መፅሃፉ ላይ በዝርዝር ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አቶ በረከት ስልጣንና ሃላፊነታቸውን ተጠቅመው የግል ጥቅማቸውን የሚያጋብሱ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ አይን-እማኝ ናቸው፡፡ በቅርቡ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የአቶ በረከት ስምዖን ባለቤት በህገወጥ መንገድ ዘመናዊ የፊልም ካሜራ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ አቶ በረከት ደግሞ በሼህ መሃመድ አል-ኣሙዲ ድጋፍ በውጪ የታተመ መፅሃፋቸውን በህገወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሀገር ልክው ይሸጡ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ አቶ መላኩ ፈንታ ይህን ህገወጥ ተግባር ለማስቆም በመሞከራቸው ምክንያት አቶ በረከት በቂም-በቀል እንዳጠቋቸው በቃለ-ምልልሱ ተጠቅሷል፡፡

የአቶ በረከት ስምዖን መፅሃፍ ሽያጩ ብቻ ሳይሆን የታተመውም ከባለሃብቶች ጋር ባላቸው ያልተገባ የጥቅም ትስስር አማካኝነት ነው፡፡ አቶ በረከት ከሼህ መሃመድ አል-ኣሙዲ ጋር ያላቸው የጥቅም ትስስር በጣም ስር የሰደደ መሆኑ ከአመታት በፊት የወጣ የአዲስ አድማስ ዘገባ ያስረዳል፡፡ በህገወጥ የጥቅም ትስስር የታተመውና በህገወጥ መንገድ ለሽያጭ የቀረበው የአቶ በረከት መፅሃፍ በአቶ መለስ ዜናዊ አመልኮና በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጥላቻ የታጨቀ መሆኑ በዘገባው ተገልጿል፡፡

አቶ በረከት ሰሞኑን ከብአዴን መባረራቸውን ተከትሎ በተለያዩ ሚዲያዎች በሰጡት አስተያየት ዙሪያ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ባወጡት ፅሁፍ ግለሰቡ ከላይ በተጠቀሱት እኩይ ተግባራት ተሰማርተው እንደነበር ገልፀዋል፡፡ እንደ አቶ በረከት ስምዖን ያለ ሰው “ለምን እንጂ ምን አለ?” አይባልም፡፡ እንዲህ ያለ ስብዕና ያለው ሰው የሚናገረው ሆነ የሚያስበው የበታችነት ስሜቱን ለማስታመም፣ ቂም-በቀል የሰነቀ፣ በየተፈላጊነት ስሜት የናወዘ፣ በአጎብዳጅነት የታጀበ፣ በውሸት የታጨቀ፣ ዓይን ያወጣ አስመሳይነትና አገልጋይነት ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለ ሰው “እንዴት የፖለቲካ አመራር ሆነ እንጂ ምን አለ?” ተብሎ አይጠየቅም፡፡

One thought on “እንደ አቶ በረከት ስምዖን ያለ ሰው “ለምን አለ?” እንጂ “ምን አለ?” አይባልም!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡