የትምህርት ብቃት የሌለው ማን ነው: ተማሪዎች ወይስ መምህራን?

“የከፍተኛ ት/ት ተቋማት ተመራቂዎች በቂ ብቃትናክህሎት ሳይዙ ነው የሚመረቁት እና የተመራቂዎች ብቃትና ክህሎት ከግዜ ወደ ግዜ እያሽቆለቆለ ነው” የሚሉ አስተያየቶች በተለያዩ መድረኮች ሲሰጡ ይሰማል። ነገር ግን፣ እንደዚህ ያሉ አስተያየቶች ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ “የትውልድ አድልዎ” (Generation Bias) በሚባለው የተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። “የትውልድ አድልዖ” በአብዛኞቻችን የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች ላይ የሚስተዋል የተሳሳተ እሳቤ ነው። በዚህ እሳቤ መሰረት፣ እያንዳንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂ ከእሱ በፊት የተመረቁ ተማሪዎች (Senior batches) የተሻለ አቅም፡- ብቃትና ክህሎት ሊኖራቸው እንደሚችል ይገምታል። በተመሣሣይ የእሱ ክፍል ጓደኞች (Batch) ደግሞ ከእነሱ ቀጥሎ ካሉት ተመራቂዎች (Junior batches) የተሻለ ብቃትና ክህሎት ሊኖራቸው እንደሚችል ያስባል። “የተመራቂዎች ብቃትና ክህሎት ከግዜ ወደ ግዜ እያሽቆለቆለ ነው” የሚለው አስተያየት የዚህ ነፀብራቅ ነው።

ለምሳሌ እኔ ዩኒቨርሲቲ በገባሁበት በ1994 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የዩኒቨርሲቲዎች አጠቃላይ የቅበላ 12ሺህ ተማሪዎች ነበር። ከእኛ በፊት በ1993 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡት ተማሪዎች ብዛት 6ሺህ አከባቢ እንደነበር አስታውሳለሁ። ይኼን የማነሳልህ፣ አንድ መምህራችን በዚህ ጉዳይ ተበሳጭቶ፤ “እንዴት ‘ተግበስብሳችሁ’ እንደገባችሁ እኮ እናውቃለን!” ያለንን ላስታውስህ ፈልጌ ነው። ስለዚህ፣ እንደ እሱ ግምት እኔና የክፍል ጓደኞቼ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ብቁ አልነበርንም። በ1997 ዓ.ም በሥራ-አመራር ሙያ በመጀመሪያ ድግሪ (BA in Management) ተመርቀን ስንወጣ እንደ እሱ በቂ ብቃትና ክህሎት ሳንይዝ እንደወጣን ያስባል። አሁን አብዛኞቹ የክፍል ጓደኞቼ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በመምህርነት እየሰሩ ይገኛል። የአብዛኞቻችን አቋም ከቀድሞ አስተማሪያችን ጋር ተመሣሣይ ነው ማለት ይቻላል። የእኔም ተማሪዎች ከእነሱ ቀጥሎ ለሚመረቁት ተማሪዎች ተመሣሣይ ግምት ሊኖራቸው እንደሚችል እገምታለሁ።

ነገሩን ይበልጥ በዝርዝር ለማስረዳት፤ “የሕይወት አጋጣሚዎች በቀጣይ ትውልድ ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል?” በሚል የተሰራን አንድ የቤተ-ሙከራ ጥናትን እንደ ማሳያ ልጠቀም። ይህ ጥናት የተለየ የምግብ ሽታን ከኤሌክትሪክ ንዝረት ጋር በማጣመር ለአይጦች በመስጠት ከእነዚህ አይጦች በሚወለዱ ግልገሎች ላይ ያለውን ተፅዕኖ የማጥናት ዓላማ ነበረው። በዚህ መሰረት፣ በቤተ-ሙከራ ውስጥ የተለየ የምግብ ሽታን በተደጋጋሚ ከኤሌክትሪክ ንዝረት ጋር አብሮ በመልቀቅ፣ በሂደት አይጦቹ ይህን የምግብ ሽታ ከአደጋ ጋር የሚያይዝ ስሜታዊ ግንዛቤ እንዲያዳብሩ ይደረጋል።

ከእነዚህ አይጦች የተወለዱት ግልገሎች፣ ምንም እንኳን የምግቡ ሽታና የኤሌክትሪክ ንዝረቱ በሌለበት ሁኔታ ቢያድጉም፣ የዚያን የተለየ የምግብ ሽታ ከአደጋ ስጋት ጋር የሚያይዝ ስሜታዊ ደመ-ነፍስ በዘረ-መላቸው ውስጥ እንደሚገኝ ተረጋግጧል። በዚህ ጥናት ውጤት መሰረት፣ ከወላጆቻችን በዘረ-መልና በአስተዳደግ ያገኘነውን ልምድና ዕውቀት በራሳችን ካገኘነው ጋር አንድ ላይ በማቀናበር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ/ማሳለፍ የማይቀየር ተፈጥሯዊ ህግ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። ነገር ግን፣ ከላይ በጥያቄው የተነሳው “የተመራቂዎች ብቃትና ክህሎት ከግዜ ወደ ግዜ እያሽቆለቆለ ነው” የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ከዚህ ተፈጥሯዊ ሂደት ጋር የሚጋጭ ነው።

Exam and class of BSc Horticulture at Jimma University College of Agriculture and Veterinary Medicine, March 30, 2010, Ethiopia

በእርግጥ ሕይወት በራሱ የተሻለውን ነገር ለቀጣዩ ትውልድ በማሳለፍ ላይ የተመሰረተ ነው። በየትኛውም ደረጃ ላይ የሚሰጥ ትምህርት በልምድና በትምህርት ያገኘነውን ጥበብና ዕውቀት ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፊያ መንገድ፣ በዚህም ከላይ የተጠቀሰው ተፈጥሯዊ ሂደት አካል ነው። በእርግጥ የእኔ መምህራን ከእኔ የተሻለ ብቃትና ክህሎት ካላቸውና ከአስተማሩኝ፣ ከእነሱ በተማርኩት ላይ እኔ በግሌ ያዳበርኩት ልምድና ዕውቀት ሲደመርበት፣ በአጠቃላይ ከእነሱ የተሻለ ብቃትና ክህሎት ሊኖረኝ ይገባል። እያንዳንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪ፤ በራሱ፣ ከቤተሰቡና ከማህብረሰቡ የሚያገኘው የተለየ ልምድና ዕውቀት ይኖረዋል። እንደ እኔ ያሉ መምህራን ደግሞ በሙያው ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት በአግባቡ ከአካፈሉት፣ ይህ ተማሪ ከእኛ ከመምህራኑ የተሻለ ብቃትና ክህሎት ሊኖረው ይገባል። አንድ ተማሪ ምንም ነገር ሳያውቅ ዩኒቨርሲቲ አይገባም። በዚህ ላይ የእኛ ዕውቀትና ክህሎት ተጨምሮበት እንዴት ከእኛ የተሻለ ላይሆን ይችላል?

ሃሳቤን ለማጠቃለል፤ የተማሪዎች ብቃት የእኛ መምህራን ብቃትና ክህሎት መመዘኛ መስፈርት እንደመሆኑ መጠን፣ የተመራቂዎች ብቃትና ክህሎት ከሚፈለገው ደረጃ በታች ነው ሲባል፣ በሌላ አነጋገር፣ የእኛ ብቃትና ክህሎት ከዚያም በታች ነው እንደማለት ነው። የተመራቂ ተማሪዎች ብቃትና ክህሎት ከቤተሰብና አስተማሪዎቻቸው ያገኙት እንደመሆኑ፣ ምንም ያህል ዝቅተኛ ቢሆን ከእነሱ ብቃትና ክህሎት በታች ሊሆን አይችልም። “የተመራቂዎች ብቃትና ክህሎት ከግዜ ወደ ግዜ እያሽቆለቆለ ነው” ስንል “ከየት-ወደ-የት ነው የሚያሽቆለቁለው?” የሚል ጥያቄ ያስነሳል። እንዲህ ያለው አመለካከት በመሰረቱ ስህተት ነው። ከዚያ ይልቅ፣ ተማሪዎቻችን ከእኛ የተሻለ ዕውቀት፣ መረጃና ክህሎት አላቸው። “ከግዜ ወደ ግዜ እያሽቆለቆለ ነው” የሚለው አስተያየት ላልሰጠነው ብድር ወለድ እንደ መጠየቅ ይቆጠራል።


ይህ ፅኁፍ ለመጀመሪያ ግዜ ለህትመት የበቃው ከሁለት አመት በፊት ውይይት በተሰኘ መፅሄት ላይ ሲሆን ፀሃፊው መምህርና ጦማሪ ስዩም ተሾመ ነው።