የትምህርት ጥራት የቀነሰበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው?

የትምህርት ጥራት ችግሮችን ወደ መዘርዝር ከማለፋችን በፊት ትምህርት በራሱ ምንድነው የሚለውን ማየት የሚያስፈልግ ይመስላኛል። በዚህ ረገድ፣ የቀድሞው የታንዛኒያ ፕረዜዳንት ጁሊዬስ ኔሬሬ እ.አ.አ በ1968 ባወጡት “Education for Self-reliance” በሚለው ፅሁፋቸው ስለትምህርት ዓላማ የሰጡትን ትንታኔ ጥሩ መነሻ የሚሆነን ይመስለኛል። እንደ ኔሬሬ አገላለፅ፤ የትምህርት መሰረታዊ ዓላማ ለረጅም ዘመናት ሕብረተሰቡ ያከማቸውን ጥበብና ዕውቀት ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ፣ ወጣቱን ትውልድ ለቀጣይ ማህበራዊ ሕይወት ማዘጋጀትና ማብቃት፣ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ህልውና እና ልማት በማረጋገጡ ረገድ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው ማስቻል ነው። ስለዚህ፣ የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ተግባራዊ ዕውቀት ያካበቱ እና በሕብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ሙያዊ ክህሎት ያላቸው፣ እንዲሁም በቀጣይ ሕይወታቸው ስኬታማ ለመሆን የሚያስችል ብቃት ያላቸው ተመራቂዎችን ማፍራት ሲቻል ነው።

ከዚህ አንፃር በአብዛኞቹ የሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በተለይ በማህበራዊ ሣይንስ ዘርፍ ያለው የትምህርት አሰጣጥ ሦስት መዋቅራዊ (መሰረታዊ) ችግሮች (Structural Problems) አሉበት። እነሱም፡- በፅሁፍ ላይ የተመሰረተ ዕውቀት (ፅንሰ-ሃሳብ)፣ የማስማሪያ ቋንቋና ተቋማዊ መዋቅር ናቸው (text-borne concepts, languages, and structures)። አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን እንደሚገልፁት፣ እነዚህ ችግሮች የቅኝ-ገዢ ኃይሎች የራሳቸውን ሥርዓተ-ትምህርት በአገዛዙ ስር ባሉ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ላይ በኃይል በመጫናቸው ምክንያት የመጣ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ነገር ግን፣ እንደ ኢትዮጲያ በቅኝ-አገዛዝ ስር ያልወደቁ ሀገሮች በነባራዊ እውነታ ላይ ያልተመሰረተ ሥርዓተ ትምህርት ከመቅረፃቸው ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮች እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንፃር ያሉትን ሦስት መሰረታዊ ችግሮች ከነባራዊ እውነታ ጋር አያይዞ በቀላሉ ማየት ይቻላል። ለምሳሌ፤ እኔ የማስተምረው የሥራ-አመራር (Business Management) ትምህርት ነው። በቀጣይ ሴሜስተር “Financial Management” የተባለ የትምህርት ዓይነት እንዳስተምር ተመድቤያለሁ። በዚህ የት/ት ዓይነት ስለ ካፒታል አፈጣጠር (Capital formation)፣ አክሲዮንና ቦንድ ዋጋ (Share and Bond Value)፣ አክሲዮን ገበያ (Stock Market)፣ …ወዘተ የመሳሰሉትን ፅንሰ-ሃሳቦች ከተቋሙ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች (Operational Activities) አንፃር ያላቸውን ተያያዥነትና ፋይዳ በተመለከተ አስተምራለሁ። ነገር ግን፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ የሰፈር ሱቆች እስከ የሀገሪቱ ዋና የገበያ ማዕከል፥ መርካቶ ድረስ ዋና የካፒታል ምንጭ የሆነው “ዕቁብ” እንጂ የአክሲዮንና ቦንድ ሽያጭ አይደለም።

እዚህ ሀገር የአክሲዮን ገበያ የለም፣ ወይም እኔ ወደ ሌላ ሀገር ሄጄ ስለማስተምረው ትምህርት ተግባራዊ ዕውቀት የመቅሰም ዕድል አላገኘሁም። ስለዚህ፣ በዕቁብ ብር ለሚማር ተማሪ ስለአሜሪካው “City Bank”፣ እና የእንግሊዙ “Barklays” ባንኮች የአክሲዮን ዋጋ መጨመርና መቀነስ ምሳሌ እሰጣለሁ። እኔ እንደ መምህር ስለአከሲዮን ገበያ በተግባር ላይ የተመሰረተ ልምድና ዕውቀት የለኝም። ስለዚህ፣ እንደ መምህር የእኔ ዕውቀት በተግባር ያልተደገፈ ፅሁፍ-ወለድ (text-borne concept) ዕውቀት ነው። የማስተምረው እኔም ሆንኩ ተማሪዎቼ በዕለት-ከዕለት ግንኙነታችን በማንጠቀምበት የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተጠቅሜ ነው። በደንብ በማንግባባበት የባዕድ ሀገር ቋንቋ በተግባራዊ ዕውቀት ያልተደገፈ ትምህርት አስተምራቸዋለሁ። እኔ እንደ መምህር የሌለኝን ለተማሪዎቼ አልሰጥም። እነሱም እንደ ተማሪ ያልተሰጣቸውን ከየትም ሊያመጡት አይችሉም።

ከመማር ማስመሩ ጋር በተያያዙ ካሉት የተግባራዊ ዕውቀት እና የማስተማሪያ ቋንቋ ችግሮች በተጨማሪ ሦስተኛው ችግር ከጥናትና ምርምር ሥራ ጋር የተያያዘ ነው። ከሞላ-ጎደል በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በጥራዝነት የሚያያዝ በእንግሊዘኛ እና በአማርኛ፥ ኦሮምኛ ወይም ሌላ የሀገር ቤት ቋንቋ ተተርጉሞ የተዘጋጀ የመረጃ መጠየቂያ (Questionnaire) ቅፅ አለ። ይህ የመጠይቅ ቅፅ በሀገር ቤት ቋንቋ የተዘጋጀበት ምክንያት ከሕብረተሰቡ ወይም በጥናቱ መፍትሄ ሊሰጠው ስለታሰበው ችግር ሕብረተሰቡ በሚግባባበት ቋንቋ ትክክለኛውን መረጃ ለመሰብሰብ እንዲቻል ነው። ከመጠይቁ በስተቀር ያሉት የጥናቱ ክፍሎች፤ የጥናቱ ትንታኔ፣ መደምደሚያና የመፍትሄ ሃሳብ የሚፃፈው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው።

በእርግጥ ይሄ ችግርን በሚያግባባ ቋንቋ ጠይቆ መፍትሄውን በማያግባባ ቋንቋ እንደመናገር ይቆጠራል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ብዙሃኑ የሀገራችን ማህብረሰብ በሚግባባቸው እንደ አማርኛና ኦሮምኛ ባሉ ቋንቋዎች የተሰሩ ጥናትና ምርምር ውጤቶች የሚታተሙባቸው የሣይንስ ጆርናሎች አሉ? የሉም። በተመሣሣይ፣ የችግሩ ባለቤት ለሆነው አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍልና ውሳኔ ሰጪ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆን በሚያስችል መልኩ በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የጥናትና ምርምር ሥራ ሰርቶ ያቀረበ ተመራማሪ የሙያና የደረጃ እድገት ያገኛል? አያገኝም። ታዲያ እንዲህ ያለ ሥራና አሰራር ይዞ እንዴት ነው ችግር-ፈቺ የሆነ ጥናትና ምርምር መስራት የሚቻለው?


ይህ ፅኁፍ ለመጀመሪያ ግዜ ለህትመት የበቃው ከሁለት አመት በፊት ውይይት በተሰኘ መፅሄት ላይ ሲሆን ፀሃፊው መምህርና ጦማሪ ስዩም ተሾመ ነው።