የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች ወቅታዊ መግለጫ እና የአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) ጉዳይ

መንግሥቱ አሰፋ 

[ይህ ፅሁፍ የመግለጫውን ሙሉ መልዕክት አይተነትንም። ለሀሳብ ፍሰት ብዬ ያላነሳሁኣቸው ነገር ግን ለሚዛናዊነት ሊጠቅሙ የሚችሉ አንዳንድ ጉዳዮች አሉ፤ ይህም የሆነው ብዙ ሽፋን ተሰጥቷቸው ስለተነገሩ የሀሳብ ድግግሞሽ እና ለጽሁፉም ርዝመት ቅነሳ ተብሎ ነው። አዲስ አበባ የማን ናት የሚለውን ነገር “የፖለቲካ ግዛት ማስፋፋት” ወይም “በጉልበት እና በኮሎኒ ተያዝን” ከሚሉ ፅንፎች ባሻገር ተጨባጭ ችግሮችን መፍታት እና የወደፊት ተፈጥሯዊ የከተማ እድገትና አስተዳደር ጉዳይ ከማኅበራዊ እድገት ጋር መታየትንእንዳለበት የመሃል ቦታ ፍለጋ  (A quest for moderate position) ሙከራ ተደርጓል]


መግቢያ

እነዚህ ድርጅቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያወጡት መግለጫ ብዙ ጉዳዮችን ዳሷል። በዋናኛነት በቡራዩ እና በአሸዋ ሜዳ ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ በዐዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች በኦሮሞ ተወላጆች እና በኦሮሞ ንብረቶች ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዟል። የነዚህን ጥቃቶች የሚዲያ ሽፋን እና “የአቀራረብ ሸሮች”፣ “ርካሽ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር መሞከር” እና “በኦሮሞ ሕዝብ ትግል እና እሴት እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖራቸውን ገፅታ እና ሚና ያጎድፋል” ያሉትን የመደበኛ እና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ዘገባዎችና ትንተናዎችን ኮንነዋል። 

በተለይ ኢሳት የሟቾችን ቁጥር በማጋነን፣ የተፈናቃዮችን ብዛት ከ3050 ሆኖ ሳለ 27000 በማለት በማጋነን፣ “Burayu Ethnic Cleansing” ብሎ በመዘገብ ሟች ከሁለት ወገን ሆኖ ሳለ አንዱን ጎን ብቻ በማቀንቀን “የኦሮሞ ሕዝብ ላይ የጥላቻ ዘመቻ መክፈቱን” ተቃውመዋል።

ዐዲስ አበባ ከተማ የኦሮሞ ነች የሚል ሐሳብም አንስተዋል። 

የኔ አስተያየት

ድርጅቶቹ ያነሱኣቸውን ጉዳዮች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲተነተኑ እና ትችቶች ሲቀርቡባቸው ትንሽ ብዥታ፣ ትንሽ አለመግባባት እና ብዙ የአድልዎ እና ማንቋሸሽ ስላየሁ የግሌ አስተያየት ላቀርብ ወደድኩ። 

፩. ስለ ጥቃቶቹ እና የሚዲያዎች፣ የግለሰቦች እና የፖለቲካ ድርጅቶች ያቀረቡኣቸው ገፅታ በጥላቻ የተሞላ፣ የውሸት እና የማጋነን (ነገሩ በራሱ እጅግ ሰቅጣጭ ሆኖ ሳለ)፣ ያልተፈፀመን እንደተፈፀመ (ለምሳሌ ጡቷ የተቆረጠን ናይጄሪያዊት ሴት፣ አንገቱ የተቆረጠ Haitian በማቅረብ) ጉዳዩ ከመጠን በላይ የዘር እልቂትን እንዲቀሰቅስ በመደረጉ መኮነኑን ተገቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። 

የሚዲያ አዘጋጆች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችና ጦማሪያን story framing ከመሥራት ይልቅ የተፈፀመውን ችግር ለብሔራዊ ኅዘንና እርቅ እንዲጠቅም አድርገው የማያቀርቡ መሆን አለባቸው። በነገራችን ላይ ኢሳት እንዲህ ያሉ ተግባራትን ሲፈፅም የመጀመሪያው አይደለም። 

ከዐራት ወር አካባቢ በፊት ካሜሩን ላይ የተገደሉ የሽብር ሰለባዎች በጅምላ መቃብር ሲቀበሩ የሚያሳይ ቪዲዮ በአፋን ኦሮሞ ድምፅ በማቀናበር ኦሮሞ ሶሞሌ ወንድሙ ላይ እንደፈፀመ አድርጎ በቴሌቪዥን መስኮቱ አሳይቷል። ሲነቃበት ደግሞ በቴሌቪዥን ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ በፌስቡክ ገፁ ብቻ “ይቅርታ” ብሎ ተንቀሳቃሽ ምስሉን አነሳ። እሱን በቴሌቪዥን መስኮት የተመለከተ ዜጋ ስንቱ የፌስቡክ ተጠቃሚ ነው?  የመጀመሪያው አይደለም ለማለት ነው።  

እንደዚህ ያሉ ተግባሮች በማናችንም አልተወገዙም። ድርጅቶቹም ሲያወግዙ ከቁብ አልቆጠርንም። ለመሆኑ ይህ ነገር የኛ ጉዳይ፣ የሀገር ጉዳይ አድርገን ግን እንወስድ ይሆን? ከቡራዩ የተፈናቀለው በዘጠኝ እጥፍ ጨምሮ ሰዎች መሬት እና ቤት ፍለጋ ተፈናቀልኩ እያሉ፣  ከሽሮ ሜዳ ድረስ መጠለያ ገብተው “ለና መገርሳ ይጠየቅልን፣ ብሔር ይጥፋ፣ ባንዲራችን አረንጓዴ ብጫ ቀይ ነው” እያሉ ሲደመጡ “ፖለቲካ እና ሰብዓዊ ቀውስን አትቀላቅሉ” የሚል ሰው ጠፍቶ ነበር።

 የሚያሳዝነው ደግሞ በድሃ ግብር የሚንቀሳቀሱ የመንግሥት ሚዲያዎችም በዚህ መሳተፋቸው ነው። ለምሳሌ በኢቴቪ የተላለፈ እየዳነ ያለ ቁስልን “በቄሮ ተደብድቤ ነው” ሲል የነበረን ወጣት  አስተላልፎታል። መረጃን ማጣራት እና ትክክለኛውን ለሕዝብ ማቅረብ የተገባው ሚዲያ ሆኖ ሳለ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ መሆኑ መኮነናቸው ተገቢ እና ሁሉም ሀገር ወዳድ ድርጅት እና ዜጋ ማድረግ ያለበት ነው ብዬ አምናለሁ። 

፪. የአዲስ አበባ ጉዳይ

በመጀመሪያ ደረጃ ፓርቲዎች የፖለቲካ ድርጅት እወክልሃለሁ የሚሉት ሕዝብ ያላቸው እንጂ በምርጫ የተመረጡ፣ ሕጋዊ የሕዝብ ውክልና ያላቸው አለመሀናቸውን እና የሚይዟቸው አቋሞች ለውይይት እና ለድርድር አጀንዳ ከመሆን ያለፈ ሌላ የጎላ ትርጉም ያለው፣ መንግሥታዊ አዋጅ ተደርጎ መቅረብ የለበትም። በሌላ መልኩ ደግሞ በሕገ መንግሥት የተቀመጠ፣ ለረጅም ዘመናት በብዙ ዜጎች ተይዞ የቆየ፣ ዛሬም የሚራመድ አቋም መሆኑም አይዘንጋ። እንደ ዱብ እዳ መታየት የለበትም። ይሄ ማለት ግን ጉዳዩ አቋም ብቻ እንጂ ታሪካዊ እና ተጨባጭ ዐንደምታ የለውም ማለት አይደለም። በተቃራኒው ጎራ የሚቀርበውንም ነገር አልዘነጋሁም።  ሌላው በሚመርጣቸው ሕዝብ የሚወሰን ይሆናል። “ገና ለገና ሥልጣን ይዘናል ብለው” የሚል  ነገር ስላየሁ እነዚህ ድርጅቶች የተለያዩ አቋም ያላቸው ከኦዴፓ ጋር ደግሞ በብዙ የሚርቁ መሆናቸውን ላስታውስ ፈለግኩ። የምን ሥልጣን ነው ያላቸው? አላስፈላጊ ውዝግቦች ፋይዳ ቢስ ብቻ ሳይሆኑ ጎጂም ናቸውና ነገሮች መያዝ ያለባቸውን መልክ እና መስመር ብቻ መያዝ አለባቸው የሚል አቋም አለኝ። 

የኦሮሚያ ክልል በኢስ አበባ ላይ አለው የሚባለውን ታሪካዊ እና ሕጋዊ ባለቤትነት (“ልዩ ጥቅም”) ድሮም የሚያራምዱት አቋማቸው ነው። 

በሽግግር ቻርተሩም፣ በኋላም በሕገ መንግሥቱ በግልፅ የተቀመጠ ነው።

ጉዳዩ ታሪካዊ እና ሕጋዊ እንዲሁም ፓለቲካዊ ሙግቶች ያሉበት DELICATE AREA መሆኑ ግልፅ ነው።  በ1994 ዓ.ም. የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ ሲቀየር ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር፣ በዚህም 400 የኦሮሞ ተማሪዎች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መባረራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው ። ተቃውሞው በማየሉ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ተመልሶ አዲስ እበባ ተደረገ። 

የኢሕአዴግ መንግሥት ለፖለቲካ ጥቅምም ይሁን ሌላ ጉዳይ ይጠቀምበት እንጂ ኦነግ ከድሮም ጀምሮ ይሄንን የባለቤትነት አቋም ሲያራምድ ኖሯል። 

በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው ኦሮሚያ በኢዲስ አበባ ላይ ያላት ‘ልዩ ጥቅም‘ በሕግ ሳይብራራ፣ ትርጉም ሳይሰጠው፣ ጉዳዩም ሳይነሳ ለ20 ዓመታት ቆይቷል። 

አሁን መነሳቱ እንደ ትልቅ ነገር ተደርጎ “መበርገግን” ማስከተሉ ብዙም ግልፅ አይደለም። እዚህጋ “ሕገ መንግሥቱ እኛን አይወክልም”፣ “ችግር ካለባቸው ጉዳዮች ይሄ የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም አንዱ ነው” የሚሉ ወገኖች እንዳሉ እረዳለሁ። 

ዋና የመግባቢያ መንገድ ብዬ የማስበው ግን ጉዳዩ የሕግም የታሪክም አለመግባባት እንዳለ ተረድተን መወያየቱ እና ችግሩን ከመሠረቱ መፍታት የመጀመሪያም የመጨረሻም አማራጭ ነው። የድርጅቶቹንም አቋም ለውይይት ማቅረብ እና ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ድርጅቶች ጋር መደራደር እና መወየት እንጂ እንደ እንግዳ ነገር አንዳንዴም ደግሞ “የባለቤትነት” የምትለው ቃል ትክክለኛ እና ተጨባጭ ችግሮችን እንዳትጋርድብን ማሳሳብ አወዳለሁ።

መግለጫውንና፣ ልዩ ጥቅሙንም  እንርሳውና አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ አለ። አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ጋር የሚኖራት ግንኙትነት ላይ ትኩረት ብናደርግ ይሻላል። አዲስ አበባ የዛሬ 130 ዓመት ስትቆራቆር እንደነበረች አይደለችም። የዛሬ 50 ዓመት እንደነበረችም አይደለችም። የክልል ፌዴራሊዝም ከመጣ እና በሕገ መንግሥት ሽፋን አግኝቶ መተዳደር ከጀመርን 23 ዓመታትን አስቆጥረናል። የዛሬ 23 ዓመት ሕገ መንግሥቱ ኦሮሚያን እና አዲስ አበባን የተለያዩ ግዛቶች ሲያደርግ ግልፅ ድንበር አላስቀመጠም።  እንቅጩን መታወቅ ያለበት ሌላ ጉዳይ ደግሞ አዲስ አበባ በዙሪያው ከሚኖሩ አርሶ አደሮች ጋር የማፈናቀል እና የማሳደድ ግንኙነት ነው የነበራት። ይሄንን በአግባብ የሚያስተካክልና በቀጣይም በፍትሕ ላይ የተመሠረተ የማኅበረኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርፆ አይታወቅም። የካሳ ጉዳይ ታስቦ አይታወቅም። የኢሕአዴግ መንግሥት በቅጡ ችግርን የማይፈታውን እና በግልፅ ያልተብራራውን “ልዩ ጥቅም” ምናልባት ስለማያመች አልያም በማወቅ ሌላ ውጥረት ፍለጋ አስቀምጧል። የባለፉት 24 ዓመታት የአዲስ አበባ መስፋፋቶች በኦሮሚያ መሬት መሆኑ ግልፅ ነው። የከተማ እድገት እና መስፋፋት ተፈጥሮኣዊ መሆኑ እየታወቀ አዲስ አበባ አትስፋ ማለት አንችልም። ግን ይሄንን የማስፋፋት ሥራ በመምራት አርሶ አደር ተፈናቅሎ  ከተማ ሲሰፋ ፍትሐዊነትን የሚያስጠብቅ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሕግም ሆነ ተቋም አልነበረም። ይህ ዝም ተብሎ ይታለፍ ማለት ሚዛናዊነት አይደለም። 

“የልዩ ጥቅሙ” ሌላ ገፅ ደግሞ ከተማይቱ በሰፋች ቀጥር የሚለቀቀው መሬት እና በአካባቢው የሚኖር በራሱ መሬት ላይ እንግዳ የመሆን በቋሚነት ማራመዱ ነው። 

ዛሬ አዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ክልል መካከል ድንበር ይደረግ ቢባል (በክልሎች መሃል እንዳለው) ድንበሩ የት ይሆናል? የድንበር አከላለል ሕጉ የትኛው ነው? የመቼው ነው? አቃቂ የማን ይሆናል? አያትስ? ቡልቡላስ? ከእስኮ ወዲያስ? 


ይህ ጉዳይ እልባት ማግኘት እንዳለበት ግን አንርሳ። በዚያ ላይ አዲስ አበባ ገናም ትሰፋለች።  ብዙ ፋብሪካዎች፣ ፎቆች እና መኖሪያ ቤቶች ገና በምትሰፋው አዲስ አበባ ላይ ይገናባሉ። የዛሬ አሥር ዓመት አዲስ አበባ ከዚህ ሰፍታ እንደምታድግ ሳይታለም የተፈታ ተፈጥሯዊ ሂደት ነው። ግን እንዴት ሊታይ ይገባል፤ እንዴትስ ለሁላችንም ጥቅም የምትወል ከተማ እንገነባለን?  ይህ ሲሆን ዙሪያዋ ካለው የኦሮሚያ ክልል ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ይኖራታል? ለዚህ ዕድገት የሚነሱ አርሶ አደሮች እንዴት ይሆናሉ? የከተማው የውሃ ፍጆታ እንዴት ነው የሚሆነው? ይከተማው ቆሻሻ የት ይሆናል? (ቆሼ ልብ ይሏል)። የከትማ እድገት የሀገር እድገት በመሆኑ ቢወደድ እንጂ አይጠላም። ይሄንን ከዚህ በፊትም ቢያንስ ብያንስ 23 ዓመታት ከመሬታቸው ተፈናቅለው፣ ራሳቸው ጭራሮ እየሸጡ አዲስ አበባን ያሳደጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ምስክር ናቸው። ግን አገር ስታድግ ለሁሉም ዜጎቿ እኩል እድል መስጠት አለባት፤ እኩል ተጠቃሚ ማድረግ አለባት። ለዚህ ደግሞ የሚሠራ የሕግ ማዕቀፍ እና ተቋማዊ አሠራር ያስፈልገናል። 

እስካሁን በተስፋፋው እና ገናም በሚስፋፋው የአዲስ አበባ ክፍሎች የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ የመሬት አስተዳደር፣ የፖለቲካ ውክልና፣ ብዙ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም፣ አግበብም ነው። ታሪካዊ እና ሕጋዊ ባለቤትነቱ ቢያከራክርም ይህንን ጉዳይ ግን ችላ ማለት ወይም ደግሞ በሌላ ጥያቄ ተበሳጨተን ጫፍ ረግጠን የምናልፈው ጉዳይ አይደለም። 

 

 እንደ ትክክለኛ ሁሉንም ዜጋ እኩል እንድሚያይ ሀገር ብንሆን ኖሮ የአዲስ አበባ እና የዙሪያውን  ሕብረተሰብ ግንኙነት፣ እንዲሁም በከተማው እድገት የሚደርስበትን ጫና መከላከል እና ፍትሐዊ የሆነ ተጠቃሚነት እንዲኖር ለመጠየቅ የኦሮሞ ድርጅቶች ድርሻ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነበር። ግን ለዚያ አልታደልንም። ምናልባት አምስቱ ድርጅቶች የያዙት አቋም በታሪክም በሕግም “ፅንፍ” ሊሆን ይችል ይሆናል። ጉዳዩ ፅንፍ ብቻ ሳይሆን ግን የመሃል ሥጋት፣ ትክክለኛ ድምፀቶች፣ የቅርብ ጊዜ ትውስታ የሆኑ በደሎች፣ መፈናቅሎች እና አግባብነት ያላቸው አሠራሮች እንደሌላቸው ማሰብም ሌላ ፅንፍ ነው። አንድ የመጨረሻ ጉዳይ ላስቀምጥ 

ይሄ ጉዳይ አሁን መነሳቱ ከማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ፖለቲካዊ ዐንደምታው እንደሚያይል፣ የመፃዒ ኢትዮጵያ ፖለቲካ የኃይል አሰላለፍን በእጅጉ የሚቀይር መሆኑን በደንብ አድርጌ አረዳለሁ። ይህ የፖለቲካ ጡዘቱ ደግሞ ትክክለኛውን ችግር እንዳንፈታ፣ የከተማው መስፋፋት እና የበፊቱ በዙሪያዋ ያሉ አርሶ አደሮች  ተደራራቢ ችግሮች እንዲቀጥሉ እና እንዲብሱ ማድረጉ አይቀሬ ነው። በምርጫም አሸንፎ ይሄንን ጉዳይ አሽቀኝጥሮ የሚጥል የፖለቲካ ኃይል ካለ ይዋል ይደር እንጂ ይህ ጉዳይ ከማኅበራዊ ቀውሱ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናው እንደገና ሌላ  ፖለቲካዊ ቀውስ ማምጣቱ ግልፅ ነው።
ሌላ መረሳት የሌለበት ነገር ቢኖር በከተማው ዙሪያ የሚኖሩ ሕዝቦችም ኢትዮጵያዊያን ሰዎች መሆናቸው ነው። እቆምላቸዋለሁ የሚለው የዘውጉ የፖለቲካ ድርጅት “ፅንፈኛ” ያልነውን አቋም ያዘ ማለት ችግር ግን የለም፣ በከተማዋ መሪዎችና መስፋፋት ታሪካዊ በደል አልተፈፀምበትም፣ ነገም አይፈፀምበትም ማለት እውነታን መካድ፣ ሀገርን አለመወደድ እንደሆነ  ነው። የአዲስ አበባ እድገት እና መስፋፋት አስፋላጊ ቢሆንም በዚህ ምክንያት የተጎዳ እና ነገም የሚጎዳ ሕዝብ ከምንም በላይ ሀገር ነው። መፍትሔ


የታሪክ፣ የሕግ እና የፖለቲካ ማስረጃዎች እና አጀንዳዎች ተቀምጠው በዚህ ጉዳይ ላይ መሬት የረገጠ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት የሚችል ተከታታይ ውይይት መደረግ አለበት። ከሁለቱም ፅንፍ ጉዳዩን ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ከተውነው እነሱ ምርጫ ሊያሸንፉበት ይችሉ ይሆናል። የሕዝብ ጥያቄ ግን አይመለስም። የሀገራችን ፖለቲካ ባህል በአመዛኙ በአሻጥር፣ በግል ፍላጎቶች እና በቡድን ጥቅም ወገኝተኝነት፣ እውነት እና ፍትሕ ሳይሆን ማንነት እና ተከትለውትንየሚመጡ ጉዳዮች ተዓማኑነት የሚያገኙበት ነው። ይህ የዘውጌ ብሔርተኛውን ብቻ ሳይሆን “የአንድነት ኃይል” በሚባሉ ቡድኖች ዘንድም በእኩል የተስፋፋ ነው። ይህ ባህል በሰክነ እና በሰለጠነ መልኩ በሚደረግ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ፣ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ የወቅቱን ነገረፖለቲካል ኢኮኖሚ ግንዛቤ ውስጥ ባስገባ ተራማጅነት ባለው ውይይት እና ምክክርን መሠረት ባደረገ የፖለቲካ ባህል መተካት አለበት። ለዚህ ደግሞ ከአዲስ አበባ ጉዳይ ብንጀምር ጥሩ ይመስለኛል። ያለውፉትን፣ አሁን ያለውን ሁኔታ እና የነገ ነገርን በዘለቄታነት የሚፈታ የዘመናዊ ከተማ እድገትና አስተዳደርን መሠረት ያደረገ እና የሀገራችንን እና የከተማይቱን ሁናቴ ግምት ውስጥ ያስገባ ፍትሐዊ የፖሊሲ ማዕቀፍ መዘጋጀት አለበት ብዬ አምናለሁ። 

የውይይቱ ዓላማም ታሪካዊ፣ ሕጋዊ እና ተጨባጭ የሕግም የታሪክም ክፍተትና ግድፈት ያለባቸው ነገሮችን ከማጥራት ባለፈ ዘመናዊ የከተማ እድገትና አስተዳደር ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አዋህዶ ፍትሐዊ የሆነ የከተማዋ እና የአካባቢዋን ሕዝቦች ግንኙነትን የሚያሰፍን፤ ያለፈውን እና የሚመጣወን ጉዳይ በካሳ መልክም ቢሆን የሚያስተካክል የማኅብረፖለቲካ እና የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ መቅረፅ መሆን አለበት የሚል ግምት አለኝ። ለዚህ ደግሞ ፅንፍን የማውገዝ ፅንፍ ከመያዝ ይልቅ ለጋራ ጥቅም ሲባል ማመቻመችን (Compromise) መርኅ ማድረግ ይበጃል እላለሁ። 


ለአስተያየትዎ በኢ-ሜይል  servezking@gmail

ወይም

 በፌስቡክ ገጼ Mengistu D. Assefa ሊያድርሱኝ ይችላሉ። One thought on “የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች ወቅታዊ መግለጫ እና የአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) ጉዳይ

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡