የታሪካችን “ታሪክ” እና አዲስ አበባ (አቶ አቻምየለህ ታምሩ  ላቀረቡት ሀተታ የተሠጠ ምላሽ)  

ይህ ጽሁፍ ሰሞኑን አቶ አቻምየለህ ታምሩ “የነኦቦ በቀለ ገርባ መግለጫና አዲስ አበባ” የሚል ርዕስ ለሰጠው ሀተታ የተሠጣ ምላሽ ነው።

[ይህ ፅሁፍ የአዲስ አበባን ባለቤት ለመበየን አይቃጣውም፡፡  የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ከዚህ ይርቃል። የአቻሜለህን የአሸናፊነት ሀተታ፣ ከታሪክ አፃፃፍ፣ ከታሪክ እይታ፣ ከህዝቦች ግንኙነት፣ ከምንጮች አጠቃቀም እና ከመረጃ (fact) ግድፈት አንፃር በአጭሩ ለማንሳት ነው፡፡ የበለጠ የተረዳ ደግሞ፣ የሁለታችንንም ሀሳብ ተችቶና አዳብሮ በቀጣዩ ብንማርበት መፅፋፌን የበለጠ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ እርዝማኔ ለመቀነስ ሲባል፣ የአንዳንዱን ጉዳይ ፍሬ ነገር ብቻ የማነሳ ሲሆን የምጠቅሳቸውን መፃህፍትም አስፈላጊ ካልሆነ በጥናት ዘዴ ልክ አልዘረዝርም]፡፡

ባለፉት ሁለት ቀናት ከመኖሪያ ቤቴ ርቄ ስለነበር የራሴን አስተያየት ለመስጠት ዘግይቻለሁ፡፡  ከተከታዩ የአቻሜለህ አንቀፅ ልነሳ፡-

“ጥናትና ምርምር ሳያካሂዱ ተረት እየደገሙ ትውልድ ሊያሳስቱበት ይችላሉ ይሆናል፤ የአገራችንን ታሪክ ላነበብንና ለመረመርን ሰዎች ግን ይህ የነ ኦቦ በቀለ ገርባ የውሸት ታሪክ አታውቁም ደንቆሮ ናችሁ ብሎ ከመስደብ አይተናነስምና ዝም ብለን ልናየው አንሻም። ስለሆነም የመረመርነውን ዶሴ ልንመዝ ተገደናል።”

የኢትዮጵያን የታሪክ አተራረክ በሶስት አውዶች ያዩታል ምሁራኑ፤

አክሱማዊ፣ ሴም-ኦሪዬንታላዊ
እና ግራ ዘመማዊ እይታዎች
በማለት፤ አቻሜለህ በአቦሰጥ ሄዶ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ውስጥ ይደቅለዋል፡፡ በተለይ ሴም-ኦሪዬንታላዊ አውድ ኢትዮጵያን አቢሲኒያ አድርጎ ይስላል፤ ይህ እይታ ዋነኛው የኢትዮጵያ ትርክት ቦይ ፈጥሯል፡፡ ከብዙ መካከል፣ ትልቁ ችግሩ የፅሁፍ አምላኪ መሆኑ ነው፡፡ ተሸለ ጥበቡ በ“The making of Modern Ethiopia” ገፅ xiv “The scriptocentric bias of literary cultures is such that a dubious written work is given more credence than a reliable oral tradition” ይላል፡፡ ተሻለ በዚህ ፈር ቀዳጅ ሥራው የኢትዮጵያ ታሪክ ከአቢሲኒያ ስልጣኔ ውጪ ያሉ ዝቦችን ታሪክ ከግርጌ ማስታወሻ በዘለለ ጠልቆ እንደማያውቅ ተከራክሯል፤ የአቢሲኒያውንም ቢሆን በሸውራራ እይታ መዳኘቱን አበክሮ ነግሮናል፡፡

የኢትዮጵያ ታሪክ ግን በፅሁፍ ብቻ አይሟላም፡፡ “Ancient things remain in the ear” እንዲሉ ጋናውያን፣ አፈ ታሪክ በጥንቃቄ ተመርምሮ ቀዳዳ እየደፈነ ይሄዳል፡፡ የ Jan Vansena አይነቱን “Oral Tradition as History” በምልአት መመርመር ስለኦሮሞ ከመፃፍ የሚቀድም ተግባር ነው፡፡ አቻሜ ግን “የአገራችንን ታሪክ ላነበብንና ለመረመርን ሰዎች…” ብሎ ቢጀምርም በሰነድ ደረጃም ቢሆን የሙጥኝ ካለው የ Krafp ሰነድ ውጪ ያየ አይመስልም፤ እሱንም በምልአት እንዳላየ የሚያስጠረጥሩኝ ምክንያቶች አሉ፡፡

የአሳሾች እና ተጓዦች መዛግብትን አተራረክ በምልአት ለማወቅ ሪቻርድ ፓንክረስት እኤአ በ1965 አሰናኝቶ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የሳተመው “Travellers in Ethiopia” እንዲሁም “The Travels of Jesuits in Ethiopia” ማየት እድል ይሰጣል፡፡ ሥራዬ ብሎ የያዘ ባለሙያ ደግሞ ከ50 የዘለሉ ተጠቃሽ የተጓዦች መዛግብት አሉለት፡፡ ብዙዎቹ ቤተ መንግሥት ደርሰው ነው ወደ አሰሳ የሚሰማሩት፤ ስለማን እንዴት እንደሚመለከቱ ሰልጥነው ነው የሚወጡት፤ ከጅምሩ ሚዛን ስተው፡፡ ከዚህ ጫና ያመለጡት የተለየ ነገር አሳይተውናል፤ የዲ ሳልቫይክ “ኦሮሞ” ጥሩ አብነት ነው፡፡

ሌላው መነሳት ያለበት ቋንቋውን ስለማትናገረው እንዲሁም ባህል እና ወጉን በምልዓት ስለማታውቀው ህዝብ መፃፍ ከሚበጀው ይልቅ የሚፈጀው ይበዛል የሚለው የባለሙያዎቹ አባባል ነው፡፡ ዘልዬ በመነሳት “The Amhara is a master of deception” ብዬ ዶናልድ ሌቪንን መጥቀስ እችላለሁ እንዴ? በምን መጠን? በምን አውድ? “The Amhara is at his happiest when he is in a position to order someone about” የሚለውንስ? ሙሉ ስዕል ካልሆነ ቁንፅል ሀሳብ ከፍ ያለ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ ብዙ ጊዜ ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር)፣ እና ጌታቸው ሀይሌ (ፕ/ር) ስለ ኦሮሞ የገደፉትን መሠረታዊ ነገር ማስነበቤን አስታውሳለሁ፡፡

አቻሜ አንድ ነገር ግልፅ አላደረገም፡፡ ክርክሩ አዲስ አበባን ፊንፊኔ ማለት አይቻልም የሚል ነው? ከሆነ አንድ አረፍተ ነገር ብቻ ይበቃ ነበር፤  ፊንፊኔ የተባለው ቦታ ዛሬ አዲስ አበባ ያረፈችበትን እንደማያካልል  ኦሮሞዎችም ይፅፋሉ፡፡ የአለማየሁ ኃይሌን “Seenaa Oromoo Hanga Jaarraa 20ffaa”  ተመልከት፡፡  አለማየሁ እንዲህ ይላል፤ ተርጉሜ ላቅርብ- “ፊንፊኔ የሚለው ስም ራሱ የሆራ (ሀይቅ) ስም ነው፡፡ ሆረ ፊንፊኔ ከላይ በጫካ፣ ነጭ ንጥፍ ድንጋይ እንዲሁም በታችኛው በኩል በረግረጋማ ትኙ መሬት የተከበበች ነበረች፡፡” በቃ፡፡ በዙሪያው የኖረው ፊታል (መን-ጉለሌ) ንዑስ ንዑስ ጎሳ ነው፡፡ ጉለሌ ቢሮ እና አቡ የተባሉ በልበላ (በር) አሉት፡፡ አቡ አምስት ወራ አለው፤ ፊታል (መን-ጉለሌ) አንዱ ነው፡፡ በቃ፡፡

አቻሜለህ “እነኦቦ በቀለ ገርባ በዛሬው መግለጫቸው አዲስ አበባን ፊንፊኔ አድርገው ለማቅረብ ቢኖክሩም ያቀረቧቸውን መንደሮች ስም ዝርዝር ለሰማ ግን እነ ኦቦ በቀለ አዲስ አበባ ማለት ፊንፊኔ ማለት እንዳልሆነ ሳይታወቃቸው ነግረውናል።” ይላል፡፡ እኔምለው፤ ይህን ማወቅ ባለቤትነቱን ለመወሰን ብዙ ይረዳል?

አቻሜለህ እንደጠቀሰው፣ ለመሆኑ ፊንፊኔን በአዲስ አበባ (ለሽፋን ሲባል) ሳይተኩ «ዛሬ ፊንፊኔ ከተማ የምትገኝበት ስፍራ የኤካ፣ የጉለሌና የገላን የኦሮሞ ጎሳዎች የዕምነት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዕከል እንደነበረች ማንም የሚክደው አይደለም። ነገር ግን እነዚህ ጎሳዎች የመኖሪያ፣ የእርሻና የግጦሽ መሬታቸውን በኃይል ተነጥቀው እንዲጠፉ ተደርገዋል» ማለታቸው መፈናቀሉን ውሸት ያደርጋል?

በሌላ በኩል፣ “ፊንፊኔ ይባል የነበረው . . . ለከተማነት ከመቆርቆሩ በፊት በዚሁ ፊንፊኔ አካባቢ በተለያዩ ስሞች የሚጠሩ ተራርቀው የሚገኙ እንደ ጉለሌ፣ ኮተቤ፣ ኮልፌ፣ ላፍቶና አቃቂ የሚባሉ መንደሮች ነበሩ፡፡” ይላል በላይ ግደይ በ “አዲስ አበባ” መፅሀፉ (1997፣ ገ. 28)፡፡

በነገራችን ላይ ይህ ዓረፍተ ነገር “ጎሳ” እና “መንደር”ን ደባልቆ እንደመንደር ያያል፤ አቻሜለህም ከዚህ ችግር አያመልጥም፤ “እንግዲህ! ፊንፊኔ፣ የካ፣ ጉለሌና ገላን እዚያው አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የተለያዩ መንደሮች እንጂ” የሚለውን እንይ፤
መንደር እና ጎሳ ፍፁም የሚለያዩ ሀሳቦች ናቸው፡፡ በላይ ግደይ ከጠቀሳቸው ውስጥ ጎሳ “ጉለሌ” ብቻ ነው፤ አቻሜለህ መንደር ብሎ ከዘረዘራቸው ውስጥ አንድስ እንኳ መንደር የለም፡፡ ይህን ሳይለይ ነው ገፅ የፈጀው፡፡ የባለሙያዎቹ ምክር አግባብ ነበር፤ ስለማታውቀው ህዝብ አትፃፍ ማለታቸው፡፡

አቻሜለህ ለኦሮሞ ታሪክ ከአንድ አሳሽ ፈረንጅ የበለጠ እንዳልቀረበ ቀጥሎ ሙጥኝ ካለው Krafp የጠቀሰው እና የተረጎመው ይመሰክራል፤

«The first campaign which I thus made in January and February 1840 led me into the territories of the tribes of the Abeju, Woberi, Gelan, Dembichu, Finfini, and of the Mulofalada, Metta Robi, Wogidi, Metta and Kuttai, all Gallas»

“`በጥር እና የካቲት 1833 ዓ.ም. የጀመርነው የመጀመሪያው ዘመቻ የአብቹ፣ የገላን፣ የወበሪ፣ የደምብቹ፣ የፊንፊኔ፣ የሞሎፋላዳ፣ የሜታ ሮቢ፣ የወግዲ፣ የቤኤና የጉታይ ኦሮሞ ጎሳዎች በሚኖሩበት ወሰደኝን’ እንደማለት ነው።”

“ወበሪ” ማን ነው? “ደምቢቹ” ማን ነው? “ሙሎፈላዳ” ማን ነው? ኦቦሪ፣ ጉምቢቹ፣ ሙሎፈርዳ መሆናቸው ነው? ለዚህ ነው ከአሳሹ በበለጠ ለሀገር ታሪክ አልቀረብክም ማለቴ፡፡

ቀጥሎ ያለውን ደግሞ እንይ፤ “ለዚህ አንድ ምሳሌ የጉለሌውን ባላባት የደጃዝማች አበቤ ቱፋ አባት ቱፋ ሙናን መጥቀስ ይቻላል።” በሕግ!!


አቤቤ ቱፋ አረዶ
እና ቱፋ ሙናን ከየት አምጥተህ ነው ያገናኘኸው? ቱፋ ሙና ጉምቢቹ ነው፡፡ በጎሳም አንድ አይደሉም፡፡ አቤቤ ቱፋ ኋላ ላይ ከልጅ ኢያሱ ጋር ተሰልፈሀል ተብሎ ወደ አርሲ የተጋዘ የኤካ ሰው ነው፡፡

ሌላውን ግድፈት እነሆ፡- “የልጃቸው የአበቤ ቱፋ ቤት ዛሬም እዚያው ጉለሌ ውስጥ ይገኛል።” አቤቤ ቱፋ ጉለሌ ቤት የለውም፡፡“[አበቤ] ሱሉልታ ውስጥ የሚገኙ የጥንት ቤተ ክርስቲያኖችን ያሰሩት እሳቸው ናቸው። ከፍ ሲል እንዳመለከትሁት ቅርሳቸው ግን ከሱሉልታ ቤተ ክርስቲያኖች አልፎ ዛሬም ድረስ ጉለሌ በሚገኘው ግቢያቸው ውስጥ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ወልደው ተዋልደው አዲስ አበቤ ሆነው ይኖሩበታል።”


አቤቤ እና ሱሉል አይያያዙም፤ ጉለሌም ግቢ የለውም፡፡ ልጆቹ አዲስ አበቤ ስለሆኑ ቱለማ በአዲስ አበባ ታቅፏል ማለት ግን አይደለም፡፡ በ
ኋላ ላይ አሳያለሁ፡፡

ሌላ ደግሞ፡- “ወርዶፋ ጨንገሬም ሌላው አዲስ አበባ ውስጥ ፈረስ የሚያስጋልብ ርስት የነበራቸው የአካባቢው ባላባት ነበሩ።”

ሆርዶፋ ጨንገሬ የሊጋባ በቀለ አባት ነው፡፡ መሰረቱ ኤጄሬ (አዲስ አለም) ሲሆን አዲስ አበቤ የሆነው ልጁ ነው፡፡ የነበረው አቻሜለህ የሚለው መሬት ሳይሆን መኖሪያ ቤት እንደሆነ አቶ አለማየሁ ሀይሌ መኩሪያ አረጋግጠውልኛል፤ አለማየሁ ሀይሌ የኦሮሞን የጎሳ ውቅር እና አሰፋፈር እንደእጆቻቸው መዳፍ ያጠኑ በህይወት ያሉ ተረት የመሰሉ ሰው ናቸው፡፡

ውድ አቻሜ! ታሪክ በዚህ መጠን ብቻ አይመረመርም፤ ቢመረመርም እንደገና ይመረመራል፡፡ ዶናልድ ክሩሜይ እንደኢትዮጵያ ያሉ ረዥም ግን አከራካሪ ታሪክ ያላቸው ሀገራት፣ ታሪካቸውን እያፈረሱ እና እየጠገኑ የመስራት ሰፊ የቤት ስራ አለባቸው ይላል፡፡
አቻሜለህ የተለመደውን አንድዬ Krafp ጠቅሶ “የቱለማ፣ የከረዩና የሜጫ ኦሮሞዎች የጉራጌና የሸዋን አካባቢዎች ኗሪዎች ግራኝ ሲያፈናቅላቸው ኦሮሞዎች ወረሩና ለምለሙን ምድር የራሳቸው አደረጉት» ይላል፡፡

አቻሜለህ “ታሪክ መረመርን”i ቢልም ከአናቱ ጀምሮ የመዘነ ይመስለኛል፡፡ ከመሀል ቢጀምር እንኳ እንቆቅልሹ አይፈታም ነበር፡፡
ስለኦሮሞ በዚህ አከባቢ መኖር ለማወቅ ከግራኝ ጦርነት መጀመር ፈፅሞ ስህተት ነው፡፡ የኩሽ ህዝቦች የቅድመ ታሪክ እና የጥንታዊ ታሪክ ስእል ግድ ነው፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ በሰሜን እና ምስራቅ አፍሪካ ከነሱ የቀደመ ሕዝብ አይታወቅም፡፡ የማቲው በርናል “Black Athena” የመጀመሪያዎቹ 34 ገፆች የኩሽ ህዝቦች አሰፋፈርን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ኢትዮጵያ ማእከል ሆና ትታያለች፡፡ በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ከነበሩ ኩሾች ኦሮሞ ጥንታዊውም ትልቁም ነው፡፡ መስፍን ወልደማርያም “Black Athena”ን በአዳፍኔ “የምናምነውን ሁሉ ገልብጦ ታሪክ የቀየረ ስራ ነው” (ቃል በቃል አይደለም) ይሉታል፡፡

ኦሮሞ ዘመኑን በጃተኒ ይቆጥራል፤ አንድ ጃተኒ አምስቱ የገዳ ፓርቲ ከሁለቱ የገዳ ክዋኔ (ከ1-48 እና ከ49-80) ጋር ተባዝተው የሚገኘው 400 አመት ነው፡፡ ተፈሪ ንጉሤ (PhD) ባደረገው ጥናት ገዳ እስከ ዛሬ 9 ጃተኒ አሳልፏል፡፡  የኢትዮጵያ ታረክ ከ1522 ጀምሮ ከታደሰው የቦረና ጃተኒ ጀምሮ ነው ኦሮሞን በወሽመጥም ቢሆን ለማስገባት የሞከረው፡፡ በገዳ የኖረበትን ቀሪ 3200 ዓመታት ከነአካቴው አያውቅም፡፡ እዚህ ላይ ከገዳ በፊት ኦሮሞ አልነበረም ለማለት አይደለም፡፡ አቻሜ እንደሁነኛ እና በያኝ አድርጎ የወሰደው የKrafp ማስታወሻ በዚህ የጊዜ ምህዋር ውስጥ ጨቅላ ነው፡፡

ኢትዮጵያ “የራሴ” የዘመን አቆጣጠር አለኝ ትላለች፤ ዋናውን ኦሪጅናሌ፣ የቦረናን “Dhaha” ግን አታውቅም፡፡ Eike Haberland ከአድናቆት አልፎ ሄዶ “ምንጩን ከኢትዮጵያ ውጪ መፈለግ ሳይሻለን አይቀርም” እስከማለት ያደረሰውን ውድ ፈጠራ፡፡

መሀመድ ሀሰን (ፕ/ር) “The Oromo and The Christian Kingdom of Ethiopia, 1300-1700” መፅሀፉ፣ የህዝቦች ዝምድና እና መስተጋብር በተለምዶ ከምንጠቅሰው የጊዜ አውድ ብዙ ወደ ኋላ እንደሚሄድ በብዙ ማስረጃ አስደግፎ አሳይቷል፡፡ በርግጥ ከምንም በላይ የመጽሀፍ ቅዱስ፣ ቅዱስ ቁርዓን፣ ገድላት እና አረቢኛ ቋንቋ እውቀቱ በጅጉ ረድተውታል፡፡ ዮዲት ጉዲት እና በኦሮሞ አፈ ታሪክ ውስጥ የገነነችው አኮ መኖዬን ምን ያክል ርቀት ሄዶ እንዳቀረረበ (አንድ ሊሆኑ እንደሚችሉ) ለተመለከተ፣ የነዚህን ህዝቦች ግንኙነት ከአንድ መፅሀፍ በተቃረመ አረፍተ ነገር ለመበየን መሞከር ግዙፍ ስህተት እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ ኦሮሞ ቢያንስ ከ11ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሸዋ (እስከ ወሎ ጠረፍ) አከባቢዎች ነዋሪ እንደነበር መፅሀፉ በስፋት ተርኳል፤ የታሪክ ጥናት እንደመሆኑ የሚቃረን አሊያም የሚያጠናክር ሌላ ጥናት እንጠብቃለን፡፡ታደሰ ታምራት (ፕ/ር) በ “ተረትና ታሪክ በኢትዮጵያ” ጥናቱ (ውይይት መፅሄት 3ኛ ሴሪ፣ ቅፅ 1፣ ቁ. 2) የመሀመድ ሀሰንን “የኢትዮጵያ ኦሮሞ” መፅሀፍ ካደነቀ በኋላ፣ እንደትቺት ያቀረበው የኦሮሞ ህዝብን እንቅስቃሴ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት መጀመሩን፣ ጥንትም በነዚሁ አካባቢዎች በእርሻ እና በከብት ርቢ እንደሚተደደር በስፋት አልተረከም ሲል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የምንለውም ተረትና ታሪክ የተጋቡበት እና ከፍተኛ የመለየት ስራ እንደሚጠብቀን ነው ያወሱት፡፡ ለበለጠ ዝርዝር ተሰማ ታአ በ “Contested terrain” ውስጥ ተመልከት፡፡

አቻሜለህ ብቻ ሳይሆን ባህሩ ዘውዴም ኦሮሞ ወደ ማእከላዊ ደጋ የመጣው የግራኝ “ወረራ”ን ተከትሎ ነው ብሎ ፅፏል፤ ነገር ግን የግራኝ የውሎ ከታቢ ሽሀብ አዲንን (አረብ ፋቂህ) ወሎ ሲደርስ “ወረ ቃሉ”፣ “ለገ ቦሩ” … የሚሉ የቦታ ስሞች እንደሰማ መፃፉን ይዘነጉታል፡፡ ዝርዝር አንድምታው “Travellers in Ethiopia” ውስጥ በመጀመሪያው ክፍል አለልህ፡፡አንድርዘይ ባርትኒስኪ እና ዮዓል ማንቴል ኒያችኮ
ፅፈው አለማየሁ አበበ ወደ አማርኛ በመለሰው “የኢትዮጵያ ታሪክ” መፅሀፍ ውስጥ፣ በዛጉዌ ሥርወ-መንግሥት ወራሾች መካከል በተነሳ አለመግባባት ከተማዋን ከመታመስ የመለሷት የኦሮሞ ወታደሮች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ የባህረ ነጋሽ ገዥን ከሀገሪቱ ሁለተኛ የስልጣን እርከን- ከዐቃቤ ሰዓቱ (እጨጌው) ጋር እኩል አድርጎ ነበር፤ በዚህ ቦታ ላይ ኦሮሞ መሾሙን በዚህ መፅሀፍ ተጠቅሷል፡፡

ባጭሩ ለመጥቀስ፣ በዜና ማርቆስ ገድል ውስጥ ስለተጠቀሱት ኦሮሞች፣ በተክለ ሀይማኖት ገድል ውስጥ ስለተጠቀሰው እኔን ያጠጣኝ የተልተሌ ውሃ እና የዶ/ር Mengistu D. Assefa ትውልድ መንደር ያያ ሀሮ፣ በአቡኑ ትውልድ መንደር ስለነበረው “ኤላ” ኩሬ፣ በወሎ እና ሸዋ መካከል እንደነበር በአሳሾች የተገለፀው “ፍር-ኩታ”፣ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቾ ወረብ የተነሳ ፀብ (የዋቄፈና ገልማ አፍርሰው ደብረ ፅዮን ቤተ ክርስቲያን እንደሰሩበት)፣ ሁሉ አቻሜ የጀመረበትን ጊዜ ቀድመው የሆኑ ናቸው፡፡ በእውቀቱ ሥዩም በ “ከአሜን ባሻገር” መፅሀፉ በስእል ጭምር ስላቀረበው እና አቻሜ ደግሞ በፍራሹ ላይ የምንሊክ ቤተ መንግስት ተሰርቶበታል ስላለው የ19ኛው ክ/ዘ ቤተ ክርስትያን ፍራሽ ቅድመ ታሪክ፣ ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ምን እንደ ነበር (ጋልማ ጎልቦ) ድርቢ ደምሴ እግር ስር ቁጭ ብለህ እንድትሰማ እመክርሀለሁ፡፡

ስለቱለማ ኦሮሞ እስካሁን ባለው መረጃ ላይ ተመስርቼ የሳሳ ሥዕል ለመስጠት ልሞክር፤
የኦሮሞ ባላባቶች በአዲስ አበባ ርስት መያዝ አዲስ አበባ ኦሮሞን አቃፊ ናት አያስብልም፡፡ በተለይ ገና ከጅምሩ ከሳኅለሥላሴ ጋር በአምቻ ተዛምዶ አማራ የሆነው የጉዲሳ Dhaaባ ነገዎ የዘር ሀረግ ጉዳይ እንደ ማስረጃ አይቀርብም፡፡ 
የ Krafp ዘመነኛ የሆነው Harris የፃፈውን ስናስተያይ ሌላ ስዕል ነው የሚሰጠን፡፡
ሌላ የቱለማና አዲስ አበባ ግንኙነትን እንይ፤ በ1873 ከጎንደር እና ከወሎ የመጣው ጦር ቀለቡን እንዲያገኝ በአንድ ኦሮሞ አባ ወራ አምስት ወታደር ተመድቦ ነው ባዶ ያስቀረው፡፡ አለማየሁ ሀይሌ ታሪክ አዋቂዎችን በማናገር ከላይ በተጠቀሰው መፅሀፉ እንደዘገበው የምደባው ውጤት እንደሚከተለው ነበር፡፡  በመሀል የገዳ ክብረ በኣል ስለደረሰ አባ ዋራ (እና አንዳንዱ እማ ወራ ተያይዘው) ወደ ኦዳ ነቤ ሄዱ፡፡ በየቤት የተመደበው ወታደር ያገኘውን የእርሻ በሬ እና የእርባታ ግደር እያረደ መሰልቀጥ ተያያዘ፤ አልፎ ተርፎ ቤት የቀሩትን ሴቶች አስገድዶ ደፈረ፤ ሴቶቹም “እንግዴህ ባል በየቤቱ አስቀምጣችሁልን የሄዳችሁት እናንተው ናችሁና ተመልሳችሁ አትምጡ” የሚል መልዕክት ባሉበት ላኩባቸው፡፡ 

ተመልሰው Caffee Tumaa Gosaa (ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት) ላይ ተገናኙ፤ ከ5 ቀን በኋላ በጃቸው የሚገኙትን ወታደሮች ለመቃወም ተስማሙ፡፡ ነገር ግን ንጉሱ አድማውን ሰሙ፤ በጉለሌ ኦሮሞ ላይ ጦርነት አወጁ፤ ማምለጥ የሆነላቸው ወደ አርሲ፣ ካራዩ፣ ሜታና በቾ ተሰደዱ፤ ሌሎች ቸርቸር ጎዳና በሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርሲትያን ተጠለሉ፡፡ የተቀሩት አረጋውያን፣ ሴቶችና ህፃናት በባርነት ተጋዙ፡፡ ዱላ አረኤ እና ሰዎቹ ከዳለቲ ተነሱ፤ ወደ ቃሊቲ፣ ቡራዩ (ከዚያም ሆለታ እና ኤጀሬ (አዲስ አለም) ተሰደዱ፡፡

ብዙዎቹ የኦሮሞ ባላባቶችም ወይ በድብደባ አሊያም በእስር ነው የተስተናገዱት፡፡ እንኳን በዚህ አካባቢ እስከ ሰላሌ ያለው ቱለማ፣ ከጨካኙ ራስ ዳርጌ (አርሲ ላይ ባሳየው ጭካኔ ምንሊክ ነው አለው የሚባለው) ጀምሮ ያስተናገዱትን መከራ Tsegaye Zeleke, እኤአ በ2002 ለታሪክ ሁለተኛ ድግሪ ማሟያ የሰራውን “The Oromo of Salaalee: A History, 1840-1936” ተመልከት፤ የ Krafp ዘመንንም ይሸፍናል፡፡
Sii bayee biyyaa sii bayee
Yoo mujjaan ollaa sii ta’ee
Yoo quriin daboo sii bahee
” በግርድፉ ሲተረጎም
“ይሀው ለቀቅሁልህ የገዛ ሀገሬን
ሙጃ እንደሁ ጎረቤት
ዝንጀሮ እንደሁ ደቦተኛ
ይሆኑህ እንደሆን” የሚል እንጉርጉሮ  ነው፤ ከዚሁ ታሪክ ጋር እንደሚያያዝ በልጅነቴ ነው የማውቀው፡፡

ጉለሌን በዚህ መልኩ ካፀዳ በኋላ ምንሊክ በ1879 ዓ.ም. ከዲልዲላ (እንጦጦ) ወደ ሸገር ወረደ፡፡ አቻሜ “ ‹በኃይል ተነጥቀው እንዲጠፉ ተደርገዋል› የሚለውን የኦነግ ተረት የፈጠራ ወሬነት ማረጋገጥ ይቻላል።” ማለቱ ተራ ድምዳሜ ነው፡፡
“[1898 ዓ.ም.] ከንቲባ ወልደፃድቅ የሆሳዕናን በዓል ድግስ እንዲደግሱና በቅሎይቱን ጠብቀው ቀልበው እንዲያኖሩ ግብሩ ይኸው የሆነ 12 ጋሻ መሬት የተተከሉ የደብሩ ትክለኛ ናቸው፡፡” (በላይ፣ 1997፣ ገ. 38)  አንድ ጋሻ አርባ ሄክታር ነው፡፡ የማእከላዊ ስታቲስትክስ ኤጀንሲ እኤአ በ2008 ባወጣው ሪፖርት መሰረት የኢትዮጵያ ገበሬ አማካይ የመሬት ይዞታ 1.2 ሄክታር ነው፡፡ ሆኖም ከግማሽ በላይ- 55.13% የሚሆኑት ያላቸው ይዞታ ከአንድ ሄክታር በታች  ነው፡፡ እኛ ያተኮርንበት ማዕከላዊ የሀገሪቱ አካባቢ ደግሞ የይዞታው መጠን ከዚህም በብዙ ያንሳል፡፡ https://en.wikipedia.org/wiki/Central_Statistical_Agency_(Ethiopia.
በአሁኑ ሰዓት፣ በዚህ አካባቢ እስከ 120 አባወራ ገበሬ የሚያስተናግድ መሬት ነው ባንድ ሰው የተወሰደው፡፡
ችግሩ ከቱለማም ይዘላል፤ ለአብነት ያክል አንድ ከመንዝ የተነሳ፣ ማፈኛ በላቸው የተባለ ልጅ፣ አሰበ ተፈሪ ደርሶ የሀገሩን ሁሉ መሬት ሲቆጣጠር (ከ9 ልጆቹ ጋር ብቻ 20 ጋሻ ወስዷል፤ ሎሌች ደግሞ አሉ፣) ለመመልከት የማርካኪስን Anatomy of Traditional Polity ተመልከት፤
***

ወደ በረራ ልመለስ

አቻሜለህን መርዳት እፈልጋለሁ፡፡ አዲስ አበባ በረራ ናት ለማለት እስከ አክሱም ድረስ ወደ ኋላ መሄድ ይችለል (በርግጥ የአማራ ታሪክ ከ13ኛው ክ/ዘ ወደ ኋላ ብዙ ስለማይሄድ፣ “እኛ አማሮች” እንዲል አቻሜ- ከግዕዝ ስልጣኔው ጋር በማስተሳሰር)፤ በላይ ግደይ አጽብሃ በሸዋ  የረር ጋራ ላይ ቤተ-መንግሥቱን ሰርቶ፣ ደቡብ፣ ምዕራብና ምስራቅ ኢትዮጵያን ገዛ፤ አብረሃ አክሱም ላይ ሆኖ ሰሜኑን ገዛ፡፡ አዲስ አበባ የሚገኘውን ዋሻ ሚካኤልም ሰራ ይላል፡፡ (በላይ፣ 1997፣ ገ. 4)፡፡  ሆኖም ለማረጋገጫ አንዳች የታሪክ ማስረጃ አያቀርብም፡፡

ምንሊክ ከአንኮበር ወደ እንጦጦ በ1874 ዓ.ም. ነው የመጣው፡፡ ርቀቱ 174 ኪ.ሜ. ነው፡፡ መጀመሪያ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ የሚገኘው ረዥሙ ወጨጫ ተራራ ላይ ሰፈሩ፡፡ (በላይ፣ 1997፣ ገ. 22)፡፡ ኋላ በ15ኛው ክፍለ ዘመን “አፄ ዳዊት ከተማቸውን አንጦጦ ላይ አድርገው ይቀመጡ ነበር የሚል የብራና ፅሁፍ በዝዋይ ደሴ ስለተገኘ ወጨጫ ተራራን ትተው የአፄ ዳዊት ከተማ ወደነበረችው እንጦጦ ወጥተው ሰፈሩ
አሁን ጥያቄ ላንሳ፡- 1ኛ የትኛው ብራና? 2ኛ ማን ጠቀሰው? 3ኛ የታሪክ ባለሙያዎች ስለሰነዱ ምን አሉ? አንዱም ጥያቄ ከግምት ሳይገባ ነው የተጠቀሰው፡፡

በዚህ ትረካ፣ ስለአዲስ አበባ መቆርቆር እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው የሳኅለሥላሴ ህልምም ተረስቷል፡፡ አክሱማዊ የታሪክ አተያይ ማለት ይህ ነው፡፡

ቀጥታ ወደ በረራ ስንመለስ፣ ብዙ አሳሾች ስለ በረራ ፅፈዋል፡፡ ሽፈራው በቀለ (ፕ/ር) ስለከተማዋ የሚለውን፣ ከግርጌ ማስታወሻ በስተቀረ ሙሉ በሙሉ ወስጄ ላብቃ፡-

በዚያ ዘመን [14ኛው ክ/ዘ] ዋና ከሚባሉት ውስጥ የነበረችው በረራ፣ የተባለች የመንግስት ከተማ፣ በ16ኛው ምዕተ አመት ጦርነቶች እና ውድመቶች ምክንያት ደብዛዋ ጠፋ፤ ነገር ግን በ15ኛው ክፍለ ዘመን የአለምን ማፕ የሰራው የቬነስ (ኢጣሊያ) ተወላጅ ፍራ ማውሮ፣ ለጉባኤ ሄደው ከነበሩ የኢትዮጵያ መነኮሳት በሰበሰበው ማስረጃ መሰረት መሃል ኢትዮጵያ ውስጥ ዋና ዋና ብሎ ከጠቆማቸው ቦታዎች መህል የዝቋላን ገዳምና በረራን አቀራርቦ አስቀምጧቸዋል፡፡ በረራ ትልቅ የመንግስት ከተማ እንደሆነችም ይጠቅሳል፡፡ […] የግራኝ ዜና መዋዕል ፀሀፊ የበረራን ትልቅነት ይመሰክርና የግራኝ ሰራዊት እንዳወደማት ዘግቧል፡፡ ከገለፃው መገንዘብ እንደሚቻለው በረራ እጅግም ከዝቋላ ያልራቀች እንደነበረች ነው፡፡ የፍራ ማውሮን ማፕ እና ሽሀብ አዲንን በመንተራስ አያሌ ተመራማሪዎች በሞጆ፣ በአዋሽ፣ በዝቋላና በየረር መካከል ሲያስሱ ኖረዋል፡፡ ብዙ ከደከሙት መካከል አንዱ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ በቅርቡ [እኤአ 2009] ባሳተሙት መጣጥፍ በረራ እስካሁን እንዳልተገኘች ፅፈዋል፡፡”

አቻሜለህ ደግሞ ከበረራ ጋር አስታኮ ያለውን እንይ፡-

“አዲስ አበባ እንደገና የተቆረቆረችው ፍል ውሃ አካባቢ የተገኘውን በግራኝ ዘመን የፈረሰ የማርያም ቤተ ክርስቲያን መሠረት አድርጎ የተሰራውን የንጉሠ ነገሥቱን ቤተ መንግሥት [የዳግማዊ ምኒልክን ቤተ መንግሥት] ማዕከል በማድረግ ነው።”
በሌላ በኩል የአፄ ዳዊት መናገሻ ላይ ነው እያለ ነው፡፡

ወደ ሽፈራው ልመለስ፡-
አሁን ግን ቢያንስ፣ ዝቋላ፣ ሞጆና የረር አካባቢ እንዳልነበረች በርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ገድለ አበው ወአኀው ግልፅ እንደሚያደርገው፣ በመካከለኛው ዘመን ወጅ (ወይም ወጊ) ተብሎ ይጠራ የነበረው ግዛት ውስጥ ነበረች፡፡ ከሌሎች ምንጮች እንደምንረዳው የደቡብ ኢትዮጵያ ጳጳሶች መዲና እንደነበረች ነው፤  ከአቡነ ገብርኤል በኋላ የመጡት ይስኀቅና ማርቆስ እዚያ ኖረዋል፡፡ እንዲያውም ይስኀቅ የተቀበረው እዛ ነበር፡፡ ወጅ የሚባለው አውራጃ ከአዲስ አበባ ሆነን ስናየው ከአዋሽ ወዲያ ማዶ የነበረ ወደ ምዕራብ እስከ ጊቤ ወንዝ የተዘረጋ ወደ ደቡብ እስከ ዝዋይ ሀይቅ የዘለቀ በሰሜን የበቾ ወረዳ የሚያዋስነው ነበር፡፡ ባጭሩ በረራ እዚህ ክልል ውስጥ ነበር ማለት ነው፡፡ የሚቀረው ይህንን ትልቅ ከተማ በዚህ ክልል ውስጥ ማፈላለጉ ነው፡፡”
በተጨማሪ ተዓምረ ማርያም ስለ አባ ገብርኤል የሚለውን ተመልከት፡፡
የ “አቢሶ” ወይም “እቢሶ” ወይም “አባሲ” ጉዳይም ገና ነው አቻሜ!
***
የሆነ ሆኖ፣ ማንም ይሁን ማን፣ በማንም ቢሆን ያለአግባብ ከመሬቱ ሲገፋ መቃወም ሰውነት ይመስለኛል፡፡
የፓርቲዎቹን መግለጫ እንዲሁም፣ የኦሮሞ ልጆች ታሪካቸው ላይ የሚያሳዩትን ዳተኝነት በተመለከተ ደግሞ ጊዜ እንደፈቀደ፣ ያለርህራሄ ለመሄስ ዝግጁ ነኝ፡፡ (ሰሎሞን ሥዩም)

2 thoughts on “የታሪካችን “ታሪክ” እና አዲስ አበባ (አቶ አቻምየለህ ታምሩ  ላቀረቡት ሀተታ የተሠጠ ምላሽ)  

  1. “የሆነ ሆኖ፣ ማንም ይሁን ማን፣ በማንም ቢሆን ያለአግባብ ከመሬቱ ሲገፋ መቃወም ሰውነት ይመስለኛል፡” is what everyone should agree on. For the history, except that you make the analysis appear scholarly by convoluting the analysis, your presentation of the history is as biased as who you are trying to respond to, to say the least.

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡