ኦሮማራ ክፍል 1፡ ከዋሽንግተን እስከ ባህር ዳር

አቶ ናሁሰናይ በላይ የተባሉ ግለሰብ፤ በህወሓት ሽንፈትና ባይተዋርነት ተቆጭተው እና በጠ/ሚ አብይ አመራር ክፉኛ ተበሳጭተው በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ያወጡትን ረጅም ፅሁፍ አነበብኩት። ፅሁፉ የጠ/ሚ አብይ አመራር ወደ ስልጣን የመጣው ከእኩልነትና አንድነት ይልቅ የኦሮሞን የበላይነት ለማረጋገጥ እንደሆነ ያትታል። “ኦሮማራ” የሚለው የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን ጥምረት ለዚህ ዓላማ የተነደፈ ስልት እንደሆነ ይገልፃሉ። እንደ ፀኃፊው አገላለፅ፣ የኦህዴዶች ግብ የረጅም ግዜ ሲሆን እሱም የሀገሪቱን የፖለቲካ ስልጣን በበላይነት መቆጣጠር ነው። በሌላ በኩል የብአዴኖች ግብ የአጭር ግዜ ሲሆን እሱም ህወሓትን ከኢህአዴግ ብሎም ከማዕከላዊ መንግስቱ ውስጥ ማስወጣት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የኦሮማራ ጥምረት በአማራና ትግራይ ልሂቃን መካከል “ጥምረትና ትብብር” ለመፍጠር የነበረውን ውጥን ማጨናገፉን ገልፀዋል። በአጠቃላይ የአቶ ናሁሰናይ ፅሁፉ “የኦሮማራ ጥምረት የመጨረሻ ዓላማ የኦሮሞን የስልጣን የበላይነት ማረጋገጥ እንደሆነና ብአዴንን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ከደጋፊነት፥ አገልጋይነት ወይም መጠቀሚያነት የዘለለ ሚና አይኖራቸውም” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም፣ እንደ እሳቸው አገላለፅ፣ የኦሮማራ ጥምረት መርህ-አልባና አግላይ ከመሆኑም በላይ የአንድ ወገን የበላይነትን የሚያረጋግጥ ነው።

በእርግጥ ይህ አመለካከት በህወሓት አመራሮችና ደጋፊዎች ዘንድ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከዚያ ይልቅ አክራሪ የብሔርተኝነት አጀንዳ የሚያራምዱ የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን በኦሮማራ ጥምረት ላይ ትችትና ነቀፌታ ሲሰነዝሩ ይስተዋላል። የአማራ ልሂቃን በአብዛኛው ኦሮማራ የኦሮሞን የስልጣን የበላይነትና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ይገልፃሉ። የኦሮሞ ልሂቃን ደግሞ የኦሮማራ ጥምረት ታሪካዊ ዳራ የሌለውና በመርህ ላይ የተመሰረተ አይደለም የሚል አቋም ያንፀባርቃሉ። ከዚህ በተጨማሪ፣ የብሔርተኝነት ሆነ አንድነት አጀንዳ የሚያራምዱ የደቡብ፥ ሶማሌ፥ አፋር፥ ጋምቤላ፥ አዲስ አበባ… ወዘተ ልሂቃን ለኦሮማራ ጥምረት በጎ አመለካከት የላቸውም። በዚህ ረገድ እነዚህ ልሂቃን የኦሮማራ ጥምረት መርህ-አልባ፣ አግላይ እና የኦሮሞ እና/ወይም አማራ የበላይነትን ለማረጋገጥ ያለመ ነው በሚል ከህወሓት ጋር ተመሳሳይ አቋም ያንፀባርቃሉ።

ስለዚህ የኦሮማራ ጥምረት ዓላማና ፋይዳ ምንድነው? ከላይ በተገለፀው መሰረት መርህ-አልባ፣ አግላይና የአንድ ወገን የበላይነትን ለሚያረጋግጥ የሚያስችል ነው? ወይስ በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተና ሀገራዊ አንድነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለሚያረጋገጥ የሚያስችል ነው? በዚህ የመጀመሪያ ክፍል ፀፅሁፍ “ኦሮማራ” የሚለውን ቃል አመጣጥ እና ከሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር ያለውን ቁርኝት በአጭሩ እንመለከታለን።

በእርግጥ “ኦሮማራ” የሚለው ቃል የኦሮሞና አማራን ትብብር የሚያሳይ እንደሆነ በማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት መገለፅ የጀመረው ከሁለት አመት በፊት እ.አ.አ በ2016 ነው። ይሁን እንጂ በወቅቱ “ኦሮማራ” የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ግዜ የተጠቀመው ማንና ለምን እንደሆነ ብዙም ግልፅ አልነበረም። ቃሉ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መጠቀስ የጀመረው ባለፈው አመት የኦሮሚያ ክልል ፕረዜዳንት ኦቦ ለማ መገርሳ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጣ ልዑካን ቡድንን በመምራት ወደ ባህር ዳር ከተማ የሄዱ ሰሞን ነው። በወቅቱ “ኦሮማራ” በሚል መሪ ቃል የተለያዩ ፅሁፎችን በፌስቡክና በድረገፅ ላይ አውጥቼያለሁ።

ነገር ግን “ኦሮማራ” የሚለው ቃል የመጣው ከሁለት አመት በፊት አይደለም። ለምሳሌ የOMN ዋና ስራ አስኪያጅ ጃዋር መሃመድ ባለፈው አመት በፌስቡክ ገፁ ባወጣው ፅሁፍ “’ኦሮማራ’ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ግዜ የሰማው እ.አ.አ. በ2009 ዓ.ም አሜሪካ ዋሽንግተን ከተማ “በሰላማዊ ትግል” ዙሪያ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ የቀድሞ የኢህዴን/ብአዴን መስራችና አመራር አቶ ያሬድ ጥበቡ ሲናገር ነው” በማለት ገልጿል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔም “ኦሮማራ” የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ መጠቀም የጀመርኩት ባለፈው አመት አሜሪካ ዋሽንግተን ከተማ “በሰላማዊ ትግል” ዙሪያ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ተሳትፌ ከተመለስኩ በኋላ ነው።

ነገሩ እንዲህ ነው፤ ባለፈው አመት በአሜሪካ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ የሲቪል ማህበራት ተወካዮችና የመብት አቀንቃኞች በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ ትንታኔ ከሰጡት አሜሪካዊ ምሁራን አንዱ ሰላማዊ ትግል 3% የሀገሪቱን ህዝብ በሚገባ ማነቃነቅና ማሳተፍ ከቻለ መንግስታዊ ስርዓቱን መቀየር እንደሚችል ይገልፃሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ ተቃውሞ እንዳለ በመግለፅ፣ “3% ቀርቶ 30% የሚሆነው ህዝብ ቢሳተፍ ኢትዮጵያ ውስጥ የስርዓት ለውጥ አይመጣም!” የሚል ሃሳብ ሰነዘርኩ።አሜሪካዊው ምሁር ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት እንደሚከታተል ከገለፀልኝ በኋላ በህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ላይ ለውጥ እንዳይመጣ ዋናው እንቅፋት የኦሮሞና አማራ ልሂቃን እርስ-በእርስ መጠላለፍ እንደሆነ በዝርዝር አስረዱኝ። በመሆኑም ኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የኦሮሞና አማራ ልሂቃን ከመጠላለፍ ይልቅ መተባበር እንዳለባቸው ተገነዘብኩ። ከአሜሪካ ከተመለስኩ በኋላ “ኦሮማራ” እያልኩ ማቀንቀን ጀመርኩ። ከባህር ዳሩ የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነት በመቀጠል የኦሮሞና አማራ ምሁራን መድረክ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን በዚህ መድረክ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ አቀረብኩ።