ኦሮማራ ክፍል 2፡ አፓርታይድ ከደደቢት እስከ ቤተ-መንግስት

የኦሮማራ ጥምረት መሰረታዊ ዓላማን ለመረዳት በቅድሚያ በህወሓት መሪነት ስለተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት ግልፅ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል። የህወሓትን ዓላማና ግብ ጠንቅቀው ከተረዱ የፖለቲካ ልሂቃን መካከል ደግሞ አቶ ያሬድ ጥበቡ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። የኢህዴን/ብአዴን መስራችና አመራር የነበረው አቶ ያሬድ በአክራሪ ብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተው የህወሓት የፖለቲካ አጀንዳ እንኳን ለተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመጣበት የትግራይ ህዝብ የማይበጅ መሆኑን ቀድሞ ተገንዝቧል። የመሰረተውን ድርጅት ለቅቆ በስደት ወደ አሜሪካ ከመሄዱ በፊት አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ ከአብዛኞቹ የህወሓት አመራሮች ጋር ውይይትና ክርክር አድርጓል።

አቶ ያሬድ በአክራሪ ብሔርተኝነት የሚመራው ህወሓት ኢህዴን/ብአዴንን ብቻ ሳይሆን ከየትኛውም የፖለቲካ ቡድን ጋር በጋራ ዓላማና መርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሊኖረው እንደማይችል ቀድሞ ለመረዳት ችሏል። ህወሓት ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖችን ለራሱ የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ ከማድረግ በዘለለ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትስስር ሊኖረው አይችልም። አቶ ያሬድ ህወሓት ገና በትጥቅ ትግል ጀምሮ የመጨረሻ ግቡ የራሱን የስልጣን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነ በተደጋጋሚ ለመግለፅ ሞክሯል። እነዚህ ፅሁፎች ተሰባስበው “ወጥቼ አልወጣሁም” በሚል ርዕስ በመፅሃፍ መልክ ታትመዋል።

ወጥቼ አልወጣሁም” የሚለውን የአቶ ያሬድ ጥበቡ መፅሃፍ ያነበብኩት ለመፃፉ ምረቃ ንግግር እንዳደርግ በተጋበዝኩበት ወቅት ነው። በመጀመሪያ የተሰማኝ ስሜት “የአቶ ያሬድ መፅሃፍ እንኳንም ከሦስት አመት በፊት አልታተመ” የሚል ነው። ምክንያቱም አቶ ያሬድ ከ20 ዓመት በፊት በህወሓት መሪነት የተዘረጋው ስርዓት ያለበትን መሰረታዊ ችግር ነቅሶ በማውጣት ለማስረዳት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ህወሓት መራሹ መንግስት ግን የአቶ ያሬድን ምክር በቀናነት ተቀብሎ ለውጥና መሻሻል ከማምጣት ይልቅ ፀሃፊውን ለስደትና እንግልት ዳርጎታል።

እኔም በበኩሌ ላለፉት ሦስት አመታት በድረገፅ ላይ ካወጣኋቸው ፅሁፎች አብዛኞቹ በህወሓት መሪነት የተዘረጋው ስርዓት ባለበት ችግር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው። በእርግጠኝነት ለመናገር ከዚያ በፊት የአቶ ያሬድን ፅሁፎች አንብቤ ቢሆን ኖኖ እነዚህን ፅሁፎች ለመፃፍ ተነሳሽነት አይኖረኝም። ምክንያቱም ባለፉት ሁለትና ሦስት አመታት የፃፍኳቸው ፅሁፎች ጭብጥ አቶ ያሬድ ጥበቡ ከዛሬ ሃያና ሰላሳ አመት በፊት ከፃፋቸው ጋር አንድና ተመሳሳይ ናቸው።

አቶ ያሬድ ጥበቡ ደግሞ ገና ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ህወሓት የሚከተለው አቋምና አመለካከት መጨረሻው የራሱን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነ ለማስገንዘብ ጥረት አድርጓል። ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በሀገራችን ለሚታየው ፖለቲካዊ ችግር መሰረታዊ መንስዔውን ለመለየት ባደረኩት ጥረት የደረስኩበት ድምዳሜ አቶ ያሬድ ከሃያና ሰላሳ አመት ከደረሰበት ድምዳሜ ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው።

አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል የማይወክል የፖለቲካ ቡድን በፖለቲካና ኢኮኖሚ ረገድ የበላይነቱን ለማረጋገጥ አብላጫ ድምፅ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በዘር፥ ብሔር፥ ቋንቋ፥ ባህል፥ …ወዘተ መከፋፈል አለበት። ምክንያቱም የአንድ ወገን የበላይነት እንዲቀጥል አብላጫ ድምፅ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ መያዝ እና የተቀናጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ የለባቸውም። በመሆኑም እንደ ህወሓት ያለ የፖለቲካ ቡድን በስልጣን እንዲቆይ የኦሮሞና አማራ ልሂቃን በጋራ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ እንዳያነሱ ማድረግ አለበት።

ላለፉት 25 ዓመታት እንደታየው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት የእኩልነትና ፍትህ ጥያቄ ያነሱ የኦሮሞ ልሂቃንን “ኦነግ”፣ የአማራ ልሂቃንን ደግሞ “ግንቦት7” በማለት በአሸባሪነት በመፈረጅ ብዙዎችን ለእስር፥ ስደትና ሞት መዳረጉ ይታወሳል። በዚህ ረገድ የህወሓት የተግባር መርህ በደቡብ አፍሪካ የነበረው የነጮች አፓርታይድ ሲመራበት ከነበረው ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው። በመሰረቱ የሁለቱም ፖለቲካዊ አስተዳደር አብላጫ ድምፅ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፣ ከአብሮነት ይልቅ መለያየትን በመስበክ፥ በማስረፅና በማስፋት፣ እንዲሁም የእኩልነትና ፍትህ ጥያቄ ያነሱ የፖለቲካ ልሂቃንን በአሸባሪነት በመፈረጅ ለእስር፥ ስደትና ሞት በመዳረግ ላይ የተመሰረተ ነው።

በአጠቃላይ ከሰላሳ ዓመት ገና በትጥቅ ትግል ላይ እያለ የህወሓት መሰረታዊ ዓላማው ዜጎችን በብሔር፥ ቋንቋ፥ ባህል፥ ታሪክና ስነ-ልቦና በመከፋፈል (አፓርታይድ) የራሱን የስልጣን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነበር። ይህ ከሰላሳ አመት በኋላ በተግባር የተረጋገጠ ሃቅ ነው። ባለፉት ሦስት አመታት በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ የተቀሰቀሰው ይህ የአፓርታይድ ስርዓት በዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ላይ በሚፈፅመው ጥሰት ምክንያት ነው። እንዲህ ያለን ጨቋኝ ስርዓት ለማስወገድ በቅድሚያ በብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል መካከል የትብብርና አንድነት መንፈስ መፍጠር ያስፈልጋል።

የኦሮማራ ጥምረት መሰረታዊ ዓላማ በህወሓት መሪነት የተዘረጋውን የአፓርታይድ ስርዓት ለመገርሰስ የሚያስፈልገውን የትብብርና አንድነት መንፈስ መፍጠር ነበር። ይህ ደግሞ ከ2008 ዓ-ም መጨረሻ ጀምሮ በተግባር ተረጋግጧል። የደቡብ አፍሪካ የተለያዩ ጎሳዎች በፀረ-አፓርታይድ ትግል ከመሰረቱት የጋራ ጥምረት ጋር በብዙ መልኩ ተመሳሳይ ነው። በዚህ መሰረት ኦሮማራ በህወሓት መሪነት የተዘረጋውን የአፓርታይድ ስርዓት ለማስወገድ በአማራና አሮሞ ህዝብ መካከል የተፈጠረ ጥምረት ነው። ሁለቱ ሕዝቦች የተጫነባቸውን የጭቆና ቀንበር ለመጣል ካደረጉት ጥረት እንዳለ ሆኖ የኦህዴድና ብአዴን አመራሮች የማይተካ ሚና ተጫውተዋል። ይህን ደግሞ በቀጣዩ ክፍል በዝርዝር እንመለከታለን።