ኦሮማራ ክፍል 3፡ ኦህዴድ እና ብአዴን፤ ከታች እሳት፥ ከላይ ህወሓት

በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በሂደት ወደ አማራ ክልል እና አንዳንድ የደቡብ አከባቢዎች መስፋፋቱ ይታወሳል። በተለይ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ የተጠናከረባቸው የኦሮሚያና አማራ ክልል መስተዳደሮች የህዝቡን ጥያቄ ተቀብለው ለማስተናገድ ጥረት የማድረግ አዝማሚያ አሳዩ። ነገር ግን ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በተደጋጋሚ “ጥልቅ ተሃድሶ” በማድረግ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ መዘጋጀቱን ቢገልፅም ተጨባጭ የሆነ ለውጥና መሻሻል ማምጣት ተሳነው። በዚህ ምክንያት በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋና ይፋ እየወጣ መጣ።

በመሰረቱ ኦህዴድና ብአዴን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደመሆናቸው መጠን አሁን በሀገሪቱ ለተከሰተው ችግር በቀጥታ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም ድርጅቶች በስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ከሚወክሉት ህዝብ ጎን አለመቆማቸው ያስወቅሳቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ዘግይቶም ቢሆን ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መሞከራቸው እንደ በጎ ጅምር ሊወሰድ ይችላል። በዚህ ረገድ የህወሃት አቋምና አመለካከት ከኦህዴድና ብአዴን ፍፁም የተለየ ነበር።

በተለያዩ አጋጣሚዎች በተግባር እንደታየው ህወሓት በፖለቲካ ስርዓቱ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ አይሻም። ይህ ብቻ ሳይሆን ብአዴን እና ኦህዴድ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት ለማደናቀፍ ያላሳለሰ ጥረት አድርጓል። በመሰረቱ በህወሃቶች ዘንድ “ተሃድሶ” ማለት የሚወክሉትን ህዝብ ጥያቄ የመቀበል ወይም የድጋፍ አዝማሚያ ያሳዩትን የብአዴንንና ኦህዴድ አመራሮችን መምታት ነው፡፡ ስለዚህ ህወሃት በራሱ ፀረ-ለውጥ ከመሆኑም በላይ ለሌሎች ድርጅቶች ለውጥና መሻሻል እንዳያመጡ እንቅፋት ነው። በመሆኑም ህወሓት የኢህአዴግ መስራች ድርጅት ብቻ ሳይሆን ለግንባሩ ሆነ የተቀሩት አባል ድርጅቶች ለውጥና መሻሻል ማነቆ ነው፡፡

በዚህ መሰረት ብአዴን እና ኦህዴድ የህዝቡን ጥያቄ ተቀብለው ምላሽ ለመስጠት በቅድሚያ ራሳቸውን ከህወሓት ተፅዕኖ ማላቀቅ ነበረባቸው። ህወሓት ደግሞ ለውጡን ለማደናቀፍ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚንቀሳቀሱትን የኦህዴድና ብአዴን አመራሮች ከአመራርነት ለማውረድ የተግባር ዕቅድ ነድፎ መንቀሳቀስ ጀምረ። ለዚህ ደግሞ ህወሓት በ1993 እና 2008 ዓ.ም ያደረገው ተሃድሶ ስህተት መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይ ኢህአዴግን ለመታደግ ምን ማድረግ እንዳለበት አንድ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር በጥቅምት 2010 ዓ.ም መቐለ ላይ በተካሄደው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ያቀረቡትን የተግባር እቅድ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል፡-

“በሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች የተሰገሰጉ ጠባቦች፣ ትምክህተኞችና ጐጠኞች የኢህአዴግ መርህ እየሸረሸሩት ኢህአዴግ ማሸነፍ ኢህአዴግ ሆኖ ነው የሚል ተግባር እየፈፀሙ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ አሁን ባለበት ሁኔታ ኢህአዴግ በማዕከል እየተመራ አይደለም ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ ተሸርሽሮ እየፈረሰ ነው ያለው፡፡ በግልፅ ቋንቋ ለመናገር በመቶ-ሺዎች መስዋእትነት የከፈለ የትግራይ ህዝብ በፀረ-ዲሞክራሲና በፀረ-ኢህአዴግ አካሄድ እየተደቆሰ ነው ያለው፡፡ የአማራ ህዝብ በትምክህተኛና ኪራይ-ሰብሳቢ አመራር እየተደቆሰ ነው ያለው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ በትግሉ የጠፋው የኦነግ አስተሳሰብና ተግባር ተመልሶ ሊውጠው ተነስቷል፡፡ … በኢህአዴግ በሚደረጉ ግምገማዎች ከልብ የሆኑና ከብሄራዊ ድርጅት አጥር የወጡ የአገርና የህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በግልፅ ኦነግ ከሆነ “ኦነግ”፣ ግንቦት_ሰባት ከሆነ “ግንቦት ሰባት ነህ” ነው መባል ያለበት፡፡ በእንደዚህ መልኩ በግልፅ ግምገማ ከተገማገሙ በየብሄራዊ ድርጅቱ የማጥራት ስራ ማስቀጠል፡፡” aigaforum.com(Pdf)

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ ኦህዴድና ብአዴን፤ ከታች ህዝቡ የሚያነሳው የመብትና ዴሞክራሲ ጥያቄ፣ ከላይ ደግሞ የህዝቡን ጥያቄ በኃይል ለማፈንና ለማዳፈን ጥረት በሚያደርገው ህወሓት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ከትቷቸው ነበር። የህዝቡን ጥያቄ አለመመለስ ሆነ ለመመለስ መሞከር በሁለቱም ድርጅቶች ላይ የህልውና አደጋ ጋርጧል። በአንድ በኩል የህዝቡ ጥያቄ ካልተመለሰ በአመፅና ተቃውሞ ከስልጣን የሚወገዱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በሌላ በኩል ህወሓት የህዝቡን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ጥረት የሚያደርጉ የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችን ለመምታት የተግባር ዕቅድ አዘጋጅቷል። ለዚህ ደግሞ በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ውስጥ የነበረው የበላይነት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለታል።

ስለዚህ የኦህዴድና ብአዴን አመራሮች፤ አንደኛ፡- የህዝባቸውን ጥያቄ በመመለስ ህልውናቸውን ለመታደግ፣ ሁለተኛ፡- ከህወሓት የሚቃጣባቸውን ጥቃት በጋራ ለመከላከል ጥምረትና ትብብር መሰረቱ። ይህ ጥምረትና ትብብር በአጭሩ “ኦሮማራ” ይባላል። በአጠቃላይ “ኦሮማራ” ማለት የኦሮሞና አማራ ሕዝብ ለእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያደርገው ትግል የወለደው የትብብር መድረክ ነው። ይህ በሁለቱ ህዝቦች እና አመራሮች መካከል የተፈጠረው ጥምረት ከሌሎች ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትና ተጠቃሚነት አንፃር እንዴት ይታያል? “ኦሮማራ” ወቅታዊ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት የተፈጠረ ወይስ ታሪካዊ ዳራ ያለው ጥምረት ነው? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በቀጣይ ክፍል በዝርዝር እንመለከታለን።