የኦሮማራ ዘመነ መንግስት እና የሽብር ዘመን፡ ከ17ኛው – 21ኛው ክ/ዘመን (ክፍል 4)

1) የኦሮማራ ዘመነ መንግስት

የኦሮማራ ዘመነ መንግስት የተጀመረው በዚህ ዓመት ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። ስለ ኦሮማራ ስርዖ መንግስት ባለማወቃችሁ አይፈረድባችሁም። ምክንያቱም እዚህ ሀገር ትላንትን ዘልለን ዛሬ መኖር የጀመርን ይመስል የጋራ ታሪክ የለንም። ከበጎ ይልቅ አስከፊ የታሪክ ገፅታ በሰረፀበት ማህብረሰብ ዘንድ “ኦሮማራ” የሚባል የሁለት ብሔሮች ጥምር መንግስት መኖሩን ማወቅ በጣም ከባድ ነው። ከአክሱም ስርዖ መንግስት ቀጥሎ የዛግዌ ዘመነ መንግስት፣ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የአማራ ሰለሞናዊ ስርዖ መንግስት እንደመጣ ይታወቃል። ብዙዎቻችን የአማራ ሰለሞናዊ ስርዖ መንግስት ማዕከል ከሸዋ ወደ ጎንደር ከዞረ በኋላም የአማራ ዘመነ መንግስት እንደቀጠለ ሰምተናል፥ ተምረናል ወይም ይመስለናል። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው።

የአክሱም ዘመነ መንግስት የወደቀው በዛግዌ ስርዖ መንግስት ተሸንፎ ነው። የዛግዌ ዘመነ መንግስት የወደቀው በአማራ ስርዖ መንግስት ተሸንፎ ነው። የኦሮማራ ዘመነ መንግስት ግን የመጣው በማሸነፍና በመሸነፍ አይደለም። ይህ ማለት ግን በኦሮሞና አማራ መካከል ጦርነትና ግጭት የለም ማለት አይደለም። ከዚያ ይልቅ በሁለቱ መካከል በተካሄዱት ጦርነቶች አንዱ ወገን አሸናፊ ሆኖ የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት ለመቆጣጠር አልቻለም። በመሆኑም የአማራ ሰለሞናዊ ሰርዖ መንግስት ማዕከሉን ከሸዋ ወደ ጎንደር ካዞረ በኋላ ቢያንስ ለአራት ክፍለ ዘመናት ሀገሪቱን በጥምረት አስተዳድረዋል። ከ17ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ ማዕከሉን ጎንደርና ወሎ በማድረግ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት በዋናነት የጎንደር አማራና የወሎ የጁ ኦሮሞዎች ናቸው። ከ19ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍል ዘመን መጨረሻ ማዕከሉን ሸዋ በማድረግ ኢትዮጵያን ያስተዳደረው ደግሞ በዋናነት የሸዋ አማራዎች እና ኦሮሞዎች ናቸው። ከአፄ ባካፋ እስከ እዮኣስ፣ ከትልቁ ራስ አሊ እስከ ትንሹ ራስ አሊ፣ ከአፄ ሚኒሊክ እስከ ልጅ እያሱ፣ ከአፄ ሃይለስላሴ እስከ አብይ አህመድ፣… ወዘተ ሙሉ በሙሉ፥ በግማሽ፥ በከፊል ኦሮሞና አማራ ናቸው።

ይሁን እንጂ የኦሮማራ ዘመነ መንግስት በሁለቱ ሕዝቦች ትብብርና አንድነት ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም። ኦሮሞና አማራ የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት ለመቆጣጠር በተደጋጋሚ የኃይል ፍጥጫና ሽኩቻ ውስጥ ገብተዋል። በዚህ ምክንያት በተለያየ ግዜና ቦታ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ግጭትና ጦርነት ተቀስቅሷል። ሆኖም ግን አንዳቸውም ሌላው በዘላቂነት ማሸነፍ አልቻሉም። ባለፉት አራት መቶ አመታት በአማራና ኦሮሞ መካከል የሚደረግ የኃይል ሽኩቻ በሀገሪቱ ላይ “የሽብር ዘመን” (Reign of Terror) አስከትሏል። ይህ የሽብር ዘመን ደግሞ ከኦሮሞና አማራ ይልቅ ሌላ ሦስተኛ ኃይል የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት እንዲቆጣጠር ያስችለዋል። በኦሮሞና አማራ የኃይል ሽኩቻ በፈጠረው ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን የሚቆጣጠረው የትግራይ ገዢ መደብ ነው።

የኦሮሞና አማራ ሽኩቻን ተከትሎ የሚከሰተው የሽብር ዘመን በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ክፍተት ይፈጥራል። ይህን ክፍተት በመጠቀም የትግራይ ገዢ መደብ ለአንድና ሁለት አስርት አመታት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን በበላይነት ይቆጣጠራል። በመጨረሻ ግን የኦሮሞና አማራ ልሂቃን በመካከላቸውን ያለውን የኃይል ሽኩቻ ወደ ጎን በመተው የጋራ ጥምረት ይመሰረታሉ። በዚህ መሰረት የትግራዩን ገዢ መደብ ተባብረው ከስልጣን ያስወግዳሉ። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይል ሚዛን የሚወሰነው በኦሮማራ ጥምረት መጥበቅና መላላት ነው። ጉዳዩን በዝርዝር ለማስረዳት ያግዘን ዘንድ ባለፉት አራት ክፍለ ዘመናት በአማራና ኦሮሞ መካከል የተፈጠሩ የኃይል ሽኩቻዎች ያስከተሏቸውን ሦስት የሽብር ዘመኖች እና የትግራይ ገዢ መደብ በኢትዮጵያ ስልጣን የተቆጣጠረባቸውን አጋጣሚዎች በአጭሩ አንመልከት።

2) የሽብር ዘመን

1ኛው የሽብር ዘመን

በ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በጎንደር አማራዎች እና በየጁ ኦሮሞዎች መካከል የተፈጠረውን የኃይል ሽኩቻ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። አፄ እያሱ (እ.አ.አ. ከ1723 – 55) ከዚህ በሞት ሲለይ ልጁ እዮኣስ 1ኛ ንጉስ ሆኖ ተሾመ። ይህን ግዜ በአፄ እያሱ ባለቤት ወለተ በርሳቤ (ዉቢት) እና በእናቱ የአፄ ባካፋ ሚስት እትጌ ምንትዋብ መካከል የጦፈ የስልጣን ሽኩቻ ተፈጠረ። ውቢት የዬጁ ኦሮሞ ስትሆን የቀድሞ ባሏን ዙፋን ለመውረስ ድጋፍ ያደርጉላት ዘንድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር ከወሎ ወደ ጎንደር ከተማ እንዲመጡ አደረገች። በተመሳሳይ እትጌ ምንትዋብ የልጇን ዙፋን ለመውረስ ድጋፍ ያደርጉላት ዘንድ ቋራ ለሚገኙ ወገን ዘመዶቿ ጥሪ በማቅረብ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር ወደ ጎንደር ከተማ እንዲመጣ አደረገች። የጎንደር ከተማ ከወሎና ቋራ በመጡ ወታደሮች ተጥለቀለቀች። በዚህ መሃል አፄ እዮኣስ ድጋፉን ለእናቱ ውቢት ሲሰጥ፣ እትጌ ምንትዋብ በበኩላቸው የልጃቸው ልዕልት አስቴር ባል ራስ ሚካኤል ስሁል ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ። ይህን መነሻ በማድረግ የትግራይ ገዢ የነበረው ራስ ሚካኤል ስሁል ከ20ሺህ የሚበልጥ ሰራዊት አስከትሎ ጎንደር ከተማ ገባ። በዚህ መልኩ የፖለቲካ ስልጣኑን የተቆጣጠረው ራስ ሚካኤል ስሁል አፄ እዮኣስን ካስገደለ በኋላ በአጭር ግዜ ውስጥ ሁለት ንጉሶች ሾመ። በኦሮማራ ዘመነ መንግስት ይህ ወቅት የመጀመሪያው “የሽብር ዘመን” (Reign of Terror) ነበር። በመጨረሻ ገላጋይ መስሎ የገባው የትግራይ ንጉስ አማራዎችና ኦሮሞዎች ተባብረው በጦርነት ከጎንደር እንዲወጣ አደረጉት።

2ኛው የሽብር ዘመን

በዘመነ መሳፍንት ማብቂያ የ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ኦሮሞች እና አማራዎች የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ በመግባታቸው የሀገሪቱ አንድነት አደጋ ላይ ወደቀ። ይህን ተከትሎ የቋራው ካሳ የየጁውን ራስ አሊ ከስልጣን በማስወገድ ራሱን አፄ ቴዎድሮስ ብሎ ነገሰ። የየጁ ኦሮሞዎችን በማሸነፍ ዙፋኑን ከወረሰ በኋላ የወሎ ኦሮሞችን፣ የሸዋ እና ጎጃም አማራዎችን፣ እንዲሁም ትግራይን አንድ ላይ ጠቅልሎ ለመግዛት በሁሉም አቅጣጫ ጦርነት ከፈተ። በዚህ ምክንያት በኦሮማራ ዘመነ መንግስት ሁለተኛው የሽብር ዘመን ተከሰተ። ይህን ሁኔታ እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የትግራዩ ካሳ ምርጫ የእንግሊዝን ጦር መቅደላ ድረስ እየመራ መጣ። አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ወደቀ። በድጋሜ ከአንድ መቶ አመት በኋላ የትግራይ ገዢ የኦሮሞና አማራ የኃይል ሽኩቻን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ስልጣን ተቆጣጠረ። የሸዋ አማራዎች ለአፄ ዮሃንስ አንገዛም ሲሉ፣ ቀድሞ ከአፄ ዮሃንስ ጭፍጨፋ ለመትረፍ ወደ ሱዳን የተሰደዱት የወሎ ሙስሊም (ኦሮሞዎች) የድርቡሾችን ጦር እየመሩ መተማ ድረስ ሲመጡ። በዚህ ጦርነት አፄ ዮሃንስ ተገደሉ።

3ኛው የሽብር ዘመን

በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ አብዛኛው የኦሮሞና አማራ ወጣቶች በመጀመሪያ በተማሪዎች ንቅናቄ፣ ቀጥሎ በኢህአፓ እና መኢሶን ስር ተደራጅተው የፊውዳሉን ስርዓት ካስወገዱ በኋላ የፖለቲካ ስልጣኑን ለመያዝ ከመተባበር ይልቅ መጠላለፍ ጀመሩ። በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ወታደራዊ ደርግ ስልጣን ተቆጣጠረ። በመጀመሪያ ከመኢሶን ጋር በመሆን ኢህአፓን ደብዛውን ካጠፋ በኋላ በመቀጠል የመኢሶን ደብዛ አጠፋ። በኦሮማራ ዘመነ መንግስት አብዛኛውን የፖለቲካ ልሂቃን ለእልቂት የዳረገው ሦስተኛው የሽብር ዘመን (ቀይ ሽብር) ተከሰተ። የኦሮሞና አማራ ልሂቃን ጎራ ለይተው እርስ በእርስ መጠላለፍና መገዳደላቸው የፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣኑን ተቆጣጠረ። ትግራይን ነፃ ለማውጣት የትጥቅ ትግል የጀመረው ትህነግ/ህወሓት በመጨረሻ የፖለቲካ ስልጣኑንና ኢኮኖሚውን በበላይነት ተቆጣጠረ። ስለ ሀገር አንድነት ወይም ስለ ኦሮሞና አማራ ህዝብ መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ያነሱትን የፖለቲካ ልሂቃን በአሸባሪነት በመፈረጅ ለእስር፥ ስደትና ሞት ዳረገ። ዛሬ ላይ የኦሮማራ ጥምረት ሦስተኛውን የሽብር ዘመን መልዕክተኛ ላለፉት አመታት በበላይነት ተቆጣጥሮት የነበረው ስልጣን ሙሉ በሙሉ ፈልቅቆ ለመውሰድ ከጫፍ ደርሷል።

የኦሮማራ ጥምረት ከትግራይ ገዢ መደብ በተጓዳኝ ከሌሎች ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ያለውን ቁርኝት፣ ከሀገር አንድነትና እኩልነት፣ እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር ያለውን አንድምታ በቀጣዩ ክፍል በዝርዝር እንመለከታለን።