2/3ኛው የህወሓት ስልጣን ተቀንሶ ለኦዴፓና አዴፓ መሰጠት አለበት! (ክፍል 6)

የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔር ተደራጅተው የማስተዳደር ስልጣን በጨበጡበት ሀገር ብሔርና ቋንቋ የሁሉም ነገር መስፈርት ይሆናል። የፖለቲካ ስልጣን መያዝና መልቀቅ፣ የህዝብ ጥቅምና ጉዳት፣ የኦኮኖሚ ገቢና ግብር፣ … በአጠቃላይ ሁሉም ነገር በብሔርና ቋንቋ እየተለካ ይሰፈራል፣ ይከፋፈላል፣ ይመዘናል። በህወሓት መሪነት የተዘረጋው ፖለቲካዊ ስርዓት በብሔርና ቋንቋ ላይ የተመሰረተ ነው። ከመንግስት መዋቅር እስከ ተቋማት አደረጃጀት፣ ከበጀት እስከ ስልጣን ክፍፍል በብሔር ላይ ማዕከል ያደረገ ነው። ህወሓት ሁሉንም ነገር በብሔርና ቋንቋ መለኪያ እየመዘነ ካከፋፈለ በኋላ የፖለቲካ ስልጣን ላይ ሲደርስ ግን መስፈርቱን ቀየረ።

ለምሳሌ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች ውስጥ 22ቱን ለአናሳ ብሔሮች በመተው የተቀሩትን መቀመጫዎች ከህዝብ ብዛት አንፃር ለክልሎች አከፋፈለ። በዚህ መሰረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የኦሮሚያ ክልል 178፣ አማራ 138፣ ደቡብ 123፣ ትግራይ 38…ወዘተ መቀመጫዎች እንዲኖራቸው አደረገ። በእርግጥ እያንዳንዱ ክልል ካለው የህዝብ ብዛት አንፃር በተወካዮች ምክር ቤት ውክልና እንዲኖረው ማድረግ አግባብ ነው። ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት በክልልና ብሔር ላይ የተመሰረተ እስከሆነ ድረስ የመወሰን ስልጣንና ኃላፊነትም በተመሳሳይ መልኩ መከፋፈል አለበት።

በህወሓት መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት ሁሉንም ነገር በብሔርና ቋንቋ አከፋፍሎ ከጨረሰ በኋላ የፖለቲካ ስልጣን ላይ ሲደርስ መስፈርቱን ከብዛት ወደ ብቃት ቀየረ። ለምሳሌ የመከላከያ ሰራዊትና ደህንነት ተቋማት በትግራይ ተወላጆች የተሞላበትን ምክንያት ሲጠየቅ “የሙያ ልምድና ብቃት ስላላቸው” እንደሆነ ይጠቅሳል። ኢህአዴግ ውስጥ፤ ከጠቅላላ የሀገሪቱ ህዝብ ውስጥ 5% ብቻ የሚወክለው ህወሓት 35% ህዝብ ከሚወክለው ኦዴፓ እኩል የመወሰን ሰልጣን አለው። ለምሳሌ ዛሬ እየተካሄደ ባለው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ አራቱም አባል ድርጅቶች እያንዳንዳቸው 250 ተወካዮች አሏቸው። በተመሳሳይ እያንዳንዱ አባል ድርጅት በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ 9 ተወካዮች አሉት።

የመንግስት መዋቅር፣ የኢኮኖሚ ሃብት ሆነ የስልጣን ክፍፍሉ፣ እንዲሁም የፓርቲ አደረጃጀቱ ከቡድን ይልቅ በግለሰብ ማንነት ላይ፣ ከብሔርና ቋንቋ ይልቅ በፖለቲካ መርህና መስመር ላይ የተመሰረተ ቢሆን በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የስልጣን ክፍፍል ችግር የለውም። ነገር ግን በህወሓት መሪነት የተዘረጋው አስተዳደራዊ መዋቅር፣ የሃብት ክፍፍል እና የፖለቲካ አደረጃጀት በብሔርና ቋንቋ ላይ የተመሰረተ፣ ከግለሰብ ይልቅ በቡድን ማንነት ላይ ማዕከል ያደረገ ነው።

በመሆኑም በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ያለው የስልጣን ክፍፍል የሚታየው ከፓርቲዎቹ ደንብና መመሪያ አንፃር ሳይሆን ከሚወክሉት ህዝብ ብዛት አንፃር ነው። አባል ድርጅቶች በኢህአዴግ ጉባኤ ወይም የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ያሏቸው ተወካዮች ብዛት የሚመዘነው ፓርቲው ከሚወክለው ህዝብ ብዛት አንፃር ነው። በተመሳሳይ በጉባኤና ኮሚቴ ውስጥ ያላቸው የመወሰን ስልጣን የሚታየው ከተወካዮቹ የግል ማንነትና የአመራር ብቃት ይልቅ በቡድን ማንነታቸው ነው።

ስለዚህ የፖለቲካ አደረጃጀቱ በብሔር/ቡድን ማንነት ላይ የተመሰረተ እስከሆነ ድረስ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እኩል የመወሰን ስልጣን ሊኖራቸው አይገባም። ከዚያ ይልቅ እያንዳንዱ አባል ድርጅት በጠቅላላ ጉባኤ፥ ማዕከላዊና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ የሚኖረው ውክልና ወይም የመወሰን ስልጣን ከሚወክለው ብሔር ወይም ህዝብ ብዛት አንፃር የተቃኘ መሆን አለበት። ይህ ሲሆን አባል ድርጅቶች ከሚመሩት ክልል ወይም ከሚወክሉት ህዝብ ብዛት አንፃር ፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል ይኖራቸዋል።

አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የሚያስተዳድሩት ክልል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለው የመቀመጫ ብዛት ከክልሉ ህዝብ ብዛት አንፃር የተቃኘ ነው። በመሆኑም አራቱም ክልሎች በተወካዮች ምክር ቤት ያላቸው ውክልና ወይም ፍትሃዊ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። አራቱ አባል ድርጅቶች ኢህአዴግ ውስጥ ያላቸውን የመወሰን ስልጣን ከሚወክሉት ህዝብ ብዛት አንፃር ስንመለከት ችግሩ በግልፅ ይታያል።

ከላይ በምስሉ ላይ እንደሚታየው እየተካሄደ ባለው የኢህአዴግ ጉባኤ ህወሓት ከሚገባው በላይ የመወሰን ስልጣን ተሰጥቶታል። በኢህአዴግ ጉባኤ ፍትሃዊ የሆነ የስልጣን ክፍፍል እንዲኖር ከተፈለገ ህወሓት አሁን ካሉት 250 ተወካዮች ውስጥ 170ዎቹ መቀነስ አለባቸው። ከተቀነሰው የ170 አባላት ውክልና ውስጥ 123ቱ ለኦዴፓ፣ 39 ለአዴፓ፣ እንዲሁም 8ቱ ለደህዴን መሰጠት አለበት። በተመሳሳይ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ህወሓት ያለው ውክልና ኢፍትሃዊ ነው። በመሆኑም አሁን ካሉት 9 የሥራ አስፈፃሚ አባላት ውስጥ የሚገባው 3 ብቻ ሲሆን ከተቀረው ውስጥ 4ቱ ለኦዴፓ፣ 1 ለአዴፓ፣ እንዲሁም 1 የስራ አስፈፃሚ አባል ደግሞ እንደ ሁኔታው ለኦዴፓ ወይም አዴፓ ይሰጣል።

ህወሓት የኢህአዴግ አባል ሆኖ መቀጠል ካለበት የስልጣን ክፍፍሉ ፍትሃዊ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ህወሓት በኢህአዴግ ጉባኤ ውስጥ ያሉት ተወካዮች ብዛት ከ250 ወደ 170 (በ68%) መቀነስ አለበት። በተመሳሳይ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ያሉት አባላት ከ9 ወደ 3 (በ66.7%) መቀነስ አለበት። በአጠቃላይ ህወሓት የኢህአዴግ አባል ድርጅት ሆኖ ለመቀጠል በኢህአዴግ ጉባኤና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ያለው ውክልና በአማካይ በ67% መቀነስ አለበት።

One thought on “2/3ኛው የህወሓት ስልጣን ተቀንሶ ለኦዴፓና አዴፓ መሰጠት አለበት! (ክፍል 6)

  1. I am not a political science student but i think parties don’t represent the whole ethnic group.
    TPLF is not the whole of Tigray people.
    In addition parties can choose with which party to form a coalition. Historically EPRDF came by the lion share initiative of TPLF. But now since all the parties in the coalition/Front start to feel free and independent, they can choose with whom to form a Front.

    But once they agreed to form a front, it’s not fair/acceptable to distribute representation or power based on the number of people where the parties based.

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡