በቀጣዩ የኢህአዴግ ጉባኤ የኦሮማራ ጥምረት የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት መቆጣጠር አለበት! (ክፍል 5)

እኔ ልንገርህ ወዳጄ! የህወሓት የጭቆና ቀንበር የተገረሰሰው በኦሮማራ ጥምረት ነው። የኦሮማራ ጥምረት ማለት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አብላጫ (majority) ያላቸው የኦሮሞና አማራ ሕዝቦች የትብብር መድረክ ነው። ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት ላለፉት አመታት የዘረጋው ፖለቲካዊ ስርዓት የአናሳ (minority) ፖለቲካ ነው። የአናሳ ድምፆች ፖለቲካ አብላጫ ድምጽ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች እርስ-በእርስ በመከፋፈልና በመነጣጠል ላይ የተመሰረተ ነው። የኦሮማራ ጥምረት ግን አብላጫ ድምፅ ያላቸውን አንድ ላይ በማጣመር ላይ የተመሰረተ ነው። ኢትዮጲያ ውስጥ ኦሮሞ አብላጫ ቁጥር አለው። ነገር ግን ኦሮሞ አብላጫ ድምፅ (majority vote) የለውም። ኦሮሞና አማራ አንድ ላይ ሲጣመሩ ግን ከ60% በላይ የሀገሪቱን ሕዝብ ይወክላሉ። ስለዚህ ኦሮማራ ማለት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አብላጫ ድምፅ (majority vote) ያለው የፖለቲካ ቡድን ነው።

ከዴሞክራሲያ መርሆች አንዱ “አብላጫ ድምፅ ያላቸው የፖለቲካ ስልጣን ይይዛሉ፣ አናሳ ድምፅ ያላቸውን መብት ያስከብራሉ” (Majority rule minority right) የሚል ነው። አብላጫ ድምፅ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የፖለቲካ ስልጣኑን ይዘው የአናሳዎችን መብት ማስከበር ከተሳናቸው የፖለቲካ ስልጣናቸው ቀጣይነት ሊኖረው አይችልም። በተመሳሳይ አናሳ ድምፅ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የፖለቲካ ስልጣን ቢይዙ የማይገባቸውን ስልጣን ስለያዙ በብዙሃኑ ዘንድ ቅቡልነት (legitimacy) ሊኖራቸው አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በተናጠል አብላጫ ድምፅ ያለው የህብረተሰብ ክፍል የለም። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አብላጫ ድምፅ ያለውና ሊኖረው የሚችለው “ኦሮማራ” ብቻ ነው። የኦሮማራ ጥምረት ከ60% በላይ የሚሆነውን የህብረተሰብ ክፍል የሚወክል እንደመሆኑ መጠን የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት ሊቆጣጠር ይገባል። ይህ የፖለቲካ ስልጣን ተቀባይነት የሚኖረው ግን አናሳ ድምፅ ያላቸውን፤ ለምሳሌ፣ የትግራይ፥ ሶማሌ፥ አፋር፥ ደቡብ፥ ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፥ ጋምቤላ፥ ሀረሪ፥ እንዲሁም አዲስ አበባና ሀረሪ ነዋሪዎችን መብትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲችል ነው።

በዚህ መሰረት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ትጉረም ያለው ለውጥ ለማምጣት በቅድሚያ የፖለቲካ ስልጣኑ በኦሮማራ ቁጥጥር ስር መዋል አለበት። ኦሮሞ ወይም አማራ ብቻውን ሆነ ከሌሎች ብሔሮች ጋር በጋራ በመሆን የፖለቲካ ስልጣኑን ለመቆጣጠር መሞከር አዋጭ አይደለም። ምክንያቱም ኦሮሞ ወይም አማራ አንዱ ከሌላው ተለይቶ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ ከፈለገ ከብዙ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ጥምረት መመስረት አለበት። በዚህ መልኩ የተመሰረተ ጥምረት ደግሞ ከሁለቱ በአንዳቸው የመፍረስ እድሉ በጣም አናሳ ነው። ከዚህ በተጫማሪ ኦሮሞ ወይም አማራ በተናጠል የመሰረቱት ጥምረት በሌላቸው ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

ኦሮሞና አማራ በትብብር የመሰረቱት ጥምረት ግን አንደኛ፡- አብላጫ ድምፅ ባለው የኦሮሞና አማራ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል፣ ሁለተኛ፡- አናሳ ድምጽ ያላቸውን ብሔሮችና ብሔረሰቦች መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት ያደርጋል። ነገር ግን ኦሮሞ ከሶማሌ፥ ትግራይ ወይም ደቡብ ብሔር፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር የሚፈጥረው ጥምረት አንደኛ፡- በአማራዎች ዘንድ ተቀባይነት አያገኝም፣ ሁለተኛ፡- አማራዎች በሚወስዱት የአፀፋ መልስ ኦሮሞ ከሌሎች ጋር የፈጠረው ጥምረት ይፈርሳል ወይም በተፈለገው ልክ ስኬታማ ሳይሆን ይቀራል። በአጠቃላይ ኦሮሞና አማራ በተናጠል ወይም ከሌሎች ብሔሮች ጋር በመሆን የሚፈጥሩት ጥምረት ዘላቂ ለውጥና መሻሻል ማምጣት ወይም የተረጋጋ ፖለቲካዊ ስርዓት ለመዘርጋት አያስችልም።

በዚህ መሰረት የኦሮሞና አማራ ልሂቃን ያላቸው ብቸኛ አማራጭ የጋራ ጥምረት በመፍጠር የፖለቲካ ስልጣኑን መቆጣጠር እና ከራሳቸው አልፎ የሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጥቅምና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። ይህን ማድረግ ከተሳናቸው ግን እንኳንስ ለሌሎች ለራሳቸውም ሕዝብ የሚበጅ ስራ መስራት አይችልም። ኦሮሞ ከሌሎች ጋር ጥምረት ከመሰረት ከእሱ ቀጥሎ ከፍተኛ ድምፅ ባለው የአማራ ሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት ሊኖረው አይችልም። አማራ ከሌሎች ጋር ጥምረት ቢመሰርት አብላጫ ድምጽ ባለው የኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ በቀጣዩ የኢህአዴግ ጉባኤ የኦሮማራ ጥምረት የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት ይቆጣጠራል። ይህ ሲሆን የኦሮሞና አማራ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን የሌሎች አናሳ ብሔሮችን መብትና ተጠቃሚነት ያረጋግጣል።