ይድረስ ለኦዴፓ፥ አዴፓና ደህዴን አመራሮች፡- “ኦሮማራን የሚቃረን ውሳኔ ለውጡን ሊቀለብስ ይችላል” (ክፍል 7)

የተከበራችሁ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮችና አባላት፣ እንደሚታወቀው ከትላንትናው ዕለት ጀምሮ በሃዋሳ ከተማ የድርጅቱን 11ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ ላይ ናችሁ። በዚህ ጉባኤ የምታሳልፏቸው ውሳኔዎች ከድርጅታችሁ ኢህአዴግ አልፎ የሀገራችንን ቀጣይ እጣ ፈንታ ይወስናል። በመሆኑም ከድርጅታችሁ አባላትና ደጋፊዎች ባለፈ መላው የሀገሪቱ ህዝብ የጉባኤውን አካሄድ በትኩረት በመከታተል ላይ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ ሀገራችን በቀጠናውና በአፍሪካ ካላት ቁልፍ ሚና አንፃር የአፍሪካና ዓለም ሀገራት ጉባኤውን በአንክሮ በመከታተል ላይ እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል። በዚህ ረገድ ትላንት የደቡብ አፍሪካና የታንዛኒያ ገዢ ፓርቲ ተወካዮች በጉባኤው መክፈቻ ላይ ያደረጉትን ንግግር እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። በመሆኑም በ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የምታሳልፏቸው ውሳኔዎች የህዝቡንና የዓለም አቀፉን ማህብረሰብ ፍላጎትና ትኩረት ከግምት ያስገባ፣ ሀገራችን የጀመረችውን ለውጥ ወደፊት የሚያስቀጥል መሆን አለበት። ስለዚህ በጉባኤው የምታሳልፉት ውሳኔ ለውጡ የመጣበትንና ወደፊት የሚቀጥልበትን አግባብ ከግንዛቤ ያስገባ ሊሆን ይገባል።

ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በሀገራችን ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ያላሳለሰ ጥረት ተደርጓል። ሆኖም ግን የዜጎች መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት የተደረጉት ጥረቶች ከሞላ ጎደል ስኬታማ አልሆነም። የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች የጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴ ከታለመለት ግብ ሳይደርስ በአጭሩ ተቀጭቷል። ለዚህ ደግሞ የሀገራችን ልሂቃን የፖለቲካ አቋምና እንቅስቃሴ በአንድነት እና ብሔርተኝነት ጎራ ለይቶ እርስ-በእርስ ከመተባበር ይልቅ በመጠላለፍ ላይ የተመሰረተ መሆኑ እንደ ዋና ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል።

እንደሚታወቀው አብዛኞቹ የአማራና የአዲስ አበባ ልሂቃን፣ እንዲሁም የተወሰኑ የሌላ ብሔር ተወላጆች ሀገራዊ አንድነትና የግለሰብ መብት እንዲከበር ያቀነቅናሉ። በሌላ በኩል አብዛኞቹ የኦሮሞ እና ትግራይ ልሂቃን፣ እንዲሁም የተወሰኑ የሌላ ብሔር ተወላጆች ለብሔር መብትና እኩልነት ቅድሚያ ይሰጣሉ። እነዚህ ወገኖች የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውን አንድ ላይ በማቀናጀት የተደራጀ የፖለቲካ ንቅናቄ መፍጠር አልቻሉም።

ባለፉት አመታት የተቀናጀ የፖለቲካ ንቅናቄ እንዳይፈጠር ዋናው ምክንያት በአማራና ኦሮሞ ልሂቃን መካከል ያለው የአመለካከት ልዩነት ነው። በእርግጥ የሌላ ብሔር ተወላጅ የሆኑ የፖለቲካ ልሂቃን በዚህ ረገድ አሉታዊ ሚና እና አስተዋፅዖ የላቸውም እያልኩ አይደልም። ከዚያ ይልቅ በኦሮሞና አማራ ልሂቃን መካከል የነበረው መከፋፈል ከራሳቸው አልፈው በሌሎች ብሔር ተወላጆች መካከል ትብብርና አንድነት እንዳይፈጠር በማድረጉ ረገድ የነበረውን ጉልህ ሚና ለማሳየት ነው።

የኦሮሞና አማራ ህዝብ ከጠቅላላ የሀገሪቱ ህዝብ ውስጥ 60% የሚሆነውን ይሸፍናል። በሌላ በኩል ፖለቲካ የሚመራው በብዙሃን አመለካከት ነው። የብዙሃኑን አመለካከት ከፊት ሆነው የሚመሩት ደግሞ የፖለቲካ ልሂቃን ናቸው። የኦሮሞና አማራ ልሂቃን በብሔርተኝነትና አንድነት ጎራ ለይተው እርስ-በእርስ በሚጠላለፉበት ወቅት ብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል አለመተማመንና ግራ-መጋባት ውስጥ ይወድቃል። ይህ ለጨቋኞችና ጭቆና ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም በላይ የተቀናጀ የፖለቲካ ንቅናቄ እንዳይኖር ያደርጋል።

ከላይ የተጠቀሰውን ችግር መቅረፍ የተቻለው በኦሮማራ ትምረት አማካኝነት ነው። የኦሮማራ ጥምረት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያና አማራ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ ንቅናቄ የጋራ ዓላማና ግብ እንዲኖረው እና ትግሉ የተቀናጀ እንዲሆን የማይተካ ሚና ተጫውቷል። በዚህ መልኩ በኦሮሞና አማራ የፖለቲካ መሪዎችና ልሂቃን ዘንድ የተፈጠረው የትብብርና ቅንጅት መንፈስ ህዝባዊ ንቅናቄው ስኬታማ እንዲሆን አስችሎታል።

በአጠቃላይ አሁን በሀገራችን የታየው ለውጥ መሰረቱ የኦሮማራ ጥምረት ነው። ምክንያቱም የኦሮማራ ጥምረት፡-

  • 1ኛ፡- በሀገራችን አብላጫ ድምፅ ያላቸውን የኦሮሞና አማራ ህዝቦች የጋራ ዓላማ ለማሳካት በትብብር መንፈስ አስተሳስሯል።
  • 2ኛ፡- በአንድነትና ብሔርተኝነት ጎራ ለይተው እርስ በእርስ ሲጠላለፉ የነበሩ የፖለቲካ ልሂቃን በጋራ ጉዳዮች ላይ እንዲተባበሩ አስችሏል።
  • 3ኛ፡- በአማራ ኦሮሞ ተወላጆች መካከል የነበረውን የእርስ-በእርስ ግጭት አደጋ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።
  • 4ኛ፡- በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው የለውጥ ንቅናቄ ወደ ሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲያድግ አድርጓል።
  • 5ኛ፡- የሕዝቡን የለውጥ ጥያቄ ተቀብሎ ለማስተናገድ ቁርጠኛ በነበሩ የኦዴፓ (ኦህዴድ) እና አዴፓ (ብአዴን) አመራሮች መካከል ጠንካራ ጥምረት ፈጥሯል።
  • 6ኛ፡- ከ1-5 የተዘረዘሩትን ለውጦች መሰረት በማድረግ ኢህአዴግ ውስጥ የአመራር ለውጥ ለማምጣት አስችሏል።

በእርግጥ “የተጀመረውን ለውጥ ስኬትና የወደፊት ቀጣይነት በኦሮማራ ጥምረት ላይ የተመሰረተ ነው” ማለት ለብዙዎች ማጋነን ሊመስል ይችላል። ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። የመጀመሪያው የኦሮማራ ጥምረት ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተመሰረተ እንደመሆኑ ለለውጡ ስኬትና ቀጣይነት ቁልፍ ሊሆን አይችልም የሚል ነው። ሌላው ደግሞ አንዳንድ ቡድኖች በለውጡ ሂደትና ቀጣይነት ውስጥ ያበረከቱትን አስተዋፅዖ ማሳነስ፣ በአንፃሩ የኦሮማራ ጥምረትን ያለቅጥ ማወደስ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ሆኖም ግን እኔ የማንንም አስተዋፅዖ የማሳነስ ሆነ የማወደስ ዓላማ የለኝም። ከዚያ ይልቅ፣ የእኔ ፍላጎት የተጀመረው ለውጥ ስኬትና ቀጣይነት የኦሮማራ ጥምረትን በማጠናከር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ማሳየት ነው።

በአጠቃላይ በሃዋሳ እየተካሄደ ባለው ስብሰባ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮችና አባላት የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች ከዚህ አንፃር የተቃኙ ሊሆን ይገባል። ከላይ በዝርዝር ለመግለጽ እንደተሞከረው የኦሮማራ ጥምረት በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ ለመጣው ለውጥና መሻሻል ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። በተመሳሳይ የተጀመረውን ለውጥ ወደፊት ለማስቀጠል የኦሮማራ ጥምረትን አጠናክሮ መቀጠል ምርጫና አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። በኦሮማራ ጥምረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ የሚችል ማንኛውም ዓይነት ነገር ለውጥን ከማጓተት ጀምሮ እስከ መቀልበስ የሚያደርስ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።